1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን የቀዉስና እርቅ ምድር

ሰኞ፣ የካቲት 16 2012

ሳልቫ ኪር እና ማቻር በገጡሙት የስልጣን ሽኩቻ ሰበብ የተጫረዉ ጦርነት አዲሲቱን ሐገር ያነድዳት፣ ያወድማት ገባ። በ2016 ሁለቱ መሪዎች ጦርነቱን እናቆማለን ብለዉ፣ ብሔራዊ ተጣማሪ መንግሥት ለመመስረት ቃል ገብተዉም ነበር። ወዲያዉ ግን ርዕሠ ከተማ ጁባ ሳይቀር ሰላማዊ ሰዎችን አስገድለዉ ረጅም ጊዜ እንደኖሩበት በጦርነቱ ቀጠሉ።

https://p.dw.com/p/3YLGe
Südsudan Salva Kiir und Riek Machar | Entscheidigung für  Einheitsregierung
ምስል AFP/M. Kuany

የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ታረቁ፤ ዳር ይዘልቅ ይሆን

የጁባ ፖለቲከኞች አጭር ታሪክ።ጥር 1 1956 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሱዳን ከአንግሎ-ግብፅ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ወጣች።ደቡብ ሱዳኖች አመፁ (አኝያኚያ Anyanya)። 1.5 ሚሊዮን ሕዝብ አለቀ። በ1972 ከካርቱሞች ጋር ታረቁ።በ11ኛ ዓመቱ እንደገና አመፁ።ከካርቱሞች ጋር ሲዋጉ፣ሲታረቁ፣እርስ በርስ ሲጋጩ፣ ሲከዳዱ 2.5 ሚሊዮን የተገመተ ሕዝብ ገደሉ ወይም አስገደሉ። ጥር 2005። ናይቫሻ-ኬንያ። «በዚሕ ስምምነት ረጂሙን የአፍሪቃ ጦርነት አስቁመናል።»

ጆን ጋራግ።ጦርነቱ ቆመ።ደቡብ ሱዳንም ነፃ ወጣች።2011።ከሁለት ዓመት በኋላ ግን ነፃ አዉጪዎቹ እርስ በርስ ይዋጉ ገቡ።የጋራንግ ሕልም ቅዠት፣የሕዝባቸዉ ምኞት መርገምት ሆነ።400 ሺሕ ሕዝብ ረገፈ።በቀደም ቅዳሜ ጁባዎች እንደገና ታረቅን ብለዋል።ካንጀት ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

እነሱ።የአንድ ሐገር-የሁለት ጎሳ፣ የአንድ ዘመን-የተቃራኒ ቤተ-ሰብ ዉልዶች ናቸዉ።ላንድ ሕዝብ ነፃነት አንድ «ጠላትን» ሲወጉ-እንኳን በሁለት ቡድን ተሰልፈዉ ወይም እየመሩ ነበር።

እሳቸዉ። ሰፊ፣ ትልቅ ባለከፈፍ ባርኔጣቸዉን አድርገዉ ብቅ ሲሉ ሺ የሚያሳልቡ፣ ሺ የሚያረቡ፣ ሰንጋ ፈረስ የሚጋልቡ ከብት አስጠባቂ እንጂ-ፖለቲከኛ አይመስሉም።ኮስታራ፣ጨፍግግ ፊታቸዉ ግን የጦር አለቃ እንጂ የእረኞች አዛዥ አያስመስላቸዉም።ሳላቫ ኪር ማያርዲት።ሰወስቱንም ናቸዉ።

የትልቁ የደቡብ ሱዳን ጎሳ የዲንካ አባል ናቸዉ።በልጅነታቸዉ እንዳባታቸዉ ከብት አርቢ ነበሩ።በወጣትነታቸዉ የነፃነት ተዋጊ ሆኑ።በ1972 የሱዳን ወታደር።ዶክተር ኮሎኔል ጆን ጋራግ የሚመሩት  የሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ጦር (SPLA) የጦር ክንፍ አዛዥ ሲሆኑ እንደ ጄኔራል፣ የፖለቲካ ክንፉ (SPLM) ምክትል ኃላፊ ሆነዉ ደግሞ፣ የአማፂዉን ቡድን እንደ ፖለቲከኛ ዘዉረዋል።

Symbolbild Stammeskämpfen im Sudan
ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/G. Julius

አለቃቸዉ ጆንግ ጋራንግ ድገንት በሄሊኮብተር አደጋ ከሞቱ ከ2005 በኋላም የቀድሞዉን የነፃነት ተዋጊ ድርጅት በሊቀመንበርነት፣ አዲሲቱን አፍሪቃዊት ሐገር በፕሬዝደንትነት እየመሩ ነዉ።ይሁንና ደቡብ ሱዳኖች በነፃነት ደስታ፣ ፌስታ፣ተስፋ ፈንድቀዉ ሳያበቁ ነባር የፖለቲካ ተቀናቃኛቸዉን ግን ምክትላቸዉን ሪያክ ማቻርን ከስልጣን ማስወገዳቸዉ ወትሮም የሚያጠያይቀዉን የፖለቲካ ብቃታቸዉን እንጭጭነት በአደባባይ ያፈጋ መስሏል።ሰዉዬዉ ግን ሌላ ምክንያት ነበራቸዉ።

«ልዩነቱ የተፈጠረዉ በSPLM የፖለቲካ መሪዎች መካከል ነዉ።በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተሰጠዉ ድምፅ የተሸነፉት፣ በስተመጨረሻ የጠመንጃ ዉጊያ ጀመሩ።»

እኚሕኛዉ። መለያቸዉ ፍንጭታቸዉ ነዉ።የናጠጠ ቱጃር፣ አለያም የተመቸዉ የባንክ ገዢ እንጂ ፖለቲከኛ አይመስሉም።እንደ ኪር የከብት አርቢ ሳይሆን የባላባት፣የዲንካ ጎሳ ሳይሆን የኙዌር ጎሳ ዉልድ ናቸዉ።የባላባት ልጅ መሆናቸዉ ከወታደር ወይም ከአማፂ ቡድን አባልነት በፊት የመማሩን ዕድል በሰፊዉ ከፍቶላቸዋል።ካርቱም ጀምረዉ፣ ብሪታንያ ተሻግረዉ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ተማሩ።

Südsudan Überschwemmungen Hütten
ምስል Getty Images/AFP/P. Louis

በ1984 ጆን ጋራንግ የሚመሩትን የሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ (SPLM) ሲቀላቀሉ የአማፂዉን ቡድን መሪዎች የጎሳ ክፍፍል ለማጥበብ እንደ ጥሩ አብነት ታይተዉ ነበር።ግን 7 ዓመት አልቆዩም።በ1991 የዲንቃ ጎሳ ያልሆኑ የSPLM ፖለቲከኞችን አስከትለዉ በጆንግ ጋራንግ አመራር ላይ አመፁ።

የጋራንግና የማቻር ልዩነት የስትራቴጂ ነዉ ተብሎ ነበር።እርግጥ ነዉ አንጋፋዉ የነፃነት ተዋጊ ጋራንግ ደቡብ ሱዳኖች እራስን በራስ የማስተዳደር ሰፊ ነፃነት ካገኙ፣ ከሱዳን መገንጠል አያስፈልጋቸዉም የሚል አቋም  ነበራቸዉ።

ማቻር ግን ከነፃነት በመለስ ሌላዉን አልቀበልም ባይ ናቸዉ።ይሕ አቋማቸዉ ከጋራንግ ይልቅ «አንድም ነፃነት አለያም ባርነት» የሚል አቋም ያራምዱ ከነበሩት ከሳልቫ ኪር ጋር ያመሳስላቸዋል።አዲስ የመሰረቱትን አማፂ ቡድንም የደቡብ ሱዳን ነፃነት ንቅናቄ ወይም ጦር (በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ SSIM/A) ብለዉት ነበር።

ይሁንና ማቻር ከSPLM ሲያፈነግጡ ተመሳሳይ አቋም የነበራቸዉን እነ ኪር ሳይሆን፣ በጎሳ ኙዌርና ዲንቃ ያልሆኑ እንደ ላም አኮል እና ጎርደን ኮንግ የመሳሰሉ ፖለቲከኞችን አስከትለዉ ነበር።

ማቻር በ1997 ከሱዳን መንግስት ጋር መታረቃቸዉ በጆንጋራግ ተከታዮች ዘንድ «ከሒዲ» እየተባሉ አስወግዟቸዋል።ለደቡብ ሱዳን ከነፃነት በመለስ ያለዉን «አልቀበልም» የሚል አቋማቸዉም ያጠያይቅ ያዘ።ከሳልቫ ኪር ጋር ከጎሳ፣ አስተዳደግ ጀምሮ የነበራቸዉ ልዩነት የፖለቲካ ጠብና ክፍፍል መልክ የተላበሰዉም ያኔ ነዉ።

በ2000 ግን ከሱዳን መንግስት ጋር በመስማማታቸዉ ያገኙትን የደቡባዊ ሱዳን አገረገዢነት እና የሱዳን ፕሬዝደንት አማካሪነት ስልጣንን ለቀዉ እንደገና አመፁ፣እንደገና ሌላ አማፂ ቡድን መሰረቱ፣ እንደገና ከጆንግ ጋራንግ ጋር ታርቀዉ የአንጋፋዉን አማፂ ቡድን የፖለቲካ ክንፍ የተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርነት ስልጣን ያዙ።

Uganda Friedensgespräche in Entebbe
ምስል Presidential Press Unit of Uganda

አማፂዉ ቡድን ለረጅም ጊዜ ከካርቱም መንግስት ጋር ያደረገዉ ድርድር ለ2005ቱ ስምነት እንዲበቃ በዉጤቱም ተጨማሪ ደም ሳይፈስ ደቡብ ሱዳን ነፀነት እንድታዉጅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸዉ በሰፊዉ ይነገራል።

«እንኳን ደስ አላችሁ።ንቅናቄያችሁ SPLM/SPLA የብሔራዊ ኮንግረስ መንግስት፣ ዛሬ የተፈራረምነዉን አጠቃላይ የሰላም ስምምነት አቅርቦላችኋል።ፍትሐዊና የተከበረ የሰላም ስምምነት።-----በዚሕ ስምምነት መሠረት ከእንግዲሕ በየዋሕ ሕፃናትና ሴቶች ላይ ከሰማይ የሚወርድ ቦምብ አይኖርም።ከእንግዲሕ ሰላም ይሰፍናል።የሕፃናትን ቡረቃ፤ደስታ የምናይበት፣ ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የተደሰቱ ሱቶችን እልልታና ዜማ የምንሰማበት ሰላም ይሰርፃል።»

ጆን ጋራግ። ጥር 2005።እሳቸዉ ዉሉ በተፈረመ በመንፈቁ ሞቱ።ሳልቫ ኪር ተተኩ።ሰላምም ሰፈነ።ደቡብ ሱዳንም ነፃ ወጣች።2011።ከጦርነት፣ እልቂት፣ ስደት ሌላ፣ ሌላ ለማያዉቀዉ ደቡብ ሱዳናዊ በርግጥ እፎይታ፣ ታላቅ ደስታ፣ተስፋም ነበር።

                                        

ሰላምና ፍቅር ተዘመረ።መሪዎቹ ግን የሚያዘምሩትን አይደለም የሚገቡትንም ቃል አልጠበቁም።ነፃነት ባወጁ በሁለተኛ ዓመታቸዉ ተከፋፈሉ።2013።ያንን ከረጅም ጊዜ ጦርነት በቅጡ ያላገገመ፣ ደሐ፣ማይም፣ መከረኛ ሕዝብ ይፈጁ፣ ያፋጁት ያዙ።

ሳልቫ ኪር እና ማቻር በገጡሙት የስልጣን ሽኩቻ ሰበብ የተጫረዉ ጦርነት አዲሲቱን ሐገር ያነድዳት፣ ያወድማት ገባ።በ2016 ሁለቱ መሪዎች ጦርነቱን እናቆማለን ብለዉ፣ ብሔራዊ ተጣማሪ መንግሥት ለመመስረት ቃል ገብተዉም ነበር።ወዲያዉ ግን ርዕሠ ከተማ ጁባ ሳይቀር ሰላማዊ ሰዎችን አስገድለዉ ረጅም ጊዜ እንደኖሩበት በጦርነቱ ቀጠሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ከ2013 እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በቀጠለዉ ጦርነት ከ400ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።ከ2.5 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ተሰድዷል።የተፋላሚ ኃላት መሪዎች የመጨረሻዉን የሰላም ስምምነት ካርቱም ላይ ከተፈራረሙ ከመስከረም 2018 በኋላ እንኳን ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ አልቆመም።

ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርና የእስከ ቅዳሜዉ የአማፂ ቡድን መሪ ሪያክ ማቸር ስምምነቱን ከፈረሙበት ከ2018 እስከ 2019 ማብቂያ ድረስ የደቡብ ሱዳንን እዉነታ ያጠነዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ኮሚሽን እንደሚለዉ የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች የገዛ ሕዝባቸዉን ያስርባሉ።

እንደ አስተዳደግ አስተሳሰባቸዉ፣ እንደ ጎሳ ልዩነታቸዉ ሁሉ ጠባይ-ኃይማኖታቸዉ የሚለያየዉ የደቡብ ሱዳን አንጋፋ ፖለቲከኞች ለስልጣን ይሆን-ለሐብት፣ ለስም-ዝና ይሁን ለታሪክ 400 ሺሕ ሕዝብ ያስፈጁበትን ጦርነት ማቆማቸዉን አዉጀዋል።

በስምምነታቸዉ መሰረት ብሔራዊ ተጣማሪ መንግስት ለመመስረት የያዙትን ቀጠሮ-በሌላ ቀጠሮ ሲቀይሩ-ዓመት ከመንፈቅ ቆይተዉ ባለፈዉ ቅዳሜ ተጣማሪ መንግስት መመስረታቸዉን አዉጀዋል።ተሿሹመዋልም።የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንትነቱን ስልጣን ዳግም የያዙት ሪያክ ማቸር ሕዝባቸዉን ለመካስ ቃል ገብተዋል።

«በመጀመሪያ ደረጃ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ሕዝብን እንኳን ደስ አለሕ ለማለት እፈልጋለሁ።የረጅም ጊዜ ስቃያችሁን ለማስወገድ በጋራ እንደምን ጥር ቃል እገባለሁ።»

አዲስ ቃል፣ አዲስ መሐላ፣ ደግሞ ሌላ ተስፋ።ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ለአዲሲቱ አፍሪቃዊት ሐገር አዲስ ብርሐን ፈነጠቀ አሉ።

Sudan Malaria-Patienten in Udier
ምስል Getty Images/AFP/S. Maina

«ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንቱና  ምክትል ፕሬዝደንቶቹ ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ አይታችኋል።ብዙዎቻችሁ ይሕ ነገር ጨርሶ አይሆንም ብላችሁ ስታስቡ ነበር።እርምጃዉ ጦርነቱ በይፋ መቆሙን ያረጋግጣል።ለደቡብ ሱዳን አዲስ ጎሕ ቀደደ ማለት እንችላለን»

ደቡብ ሱዳን ከዓለም እጅግ የደየች ሐገር ናት።አዲስ።ወደብ የላትም።በአስር ግዛቶች ተከፋፍላላ,ች።60 ጎሳ አላት።ሕዝቧን በትክክል የቆጠረዉ የለም።ገማቾች ከ7 እስከ 10 ሚሊዮን ያደርሱታል።በ2005 ነፃ ከወጣች ወዲሕ፣ አብዬ በተባለዉ ግዛት ይገባኛል ሰበብ ከሱዳን ጋር ተዋግታለች።ደቡብ ሱዳኖችን ለማስታረቅ የደረሰላቸዉ ግን በአብዬም ሆነ በረጅም ዘመኑ የነፃነት ጦርነት አማፂያኑን ያስታጠቁ፣ ያደራጁ፣ ካርቱሞችን የቀጡ፣ያወገዙ፣ ያገለሉት አይደለም።ራሳቸዉ ካርቱሞች እንጂ።በቅዳሜዉ የሹመት እርቅ ሥርዓት ላይ ከተገኙት እንግዶች ቢያንስ አንዱ የሱዳን ጄኔራል ናቸዉ።

በየአራት፣ አምስት ዓመቱ እየተጣሉ ሕዝብ የሚያጫርሱት የጁባ ፖለቲከኞች ለእስካሁን ጥፋታቸዉ ተጠያቂ የሚያደርጋቸዉ ዓለም አለመኖሩ፣ የዓለምን ፍትሕ እንዴትነት የሚያጠያይቅ ነዉ። የሹማምንቱ ቃል-ገቢር መሆኑም አጠራጣሪ።

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ