1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን እና የአዲስ አበባው የሰላም ድርድር

ቅዳሜ፣ ግንቦት 11 2010

በደቡብ ሱዳን የተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ በምህጻሩ አንሚስ ወጥረት ወደቀጠለበት የዩኒቲ ግዛት 150 ሰላም አስከባሪ ወታደሮች እንደሚልክ አስታውቋል። የወታደሮቹ ተልዕኮ በመንግሥቱ ጦር እና በዓማፅያን መካከል የሚካሄደው ውጊያ ዒላማ ያደረገው የአካባቢው ሲቭል ሕዝብ ጉዳት እንዳይደርስበት መከላከል እንደሆነ አንሚስ አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/2xxkR
Karte Südsudan Provinz Jonglei Englisch
ምስል DW

«ተፋላሚዎቹ ወገኖች ሲቭሉን ሕዝብ የጥቃት ዒላማ ማድረጋቸው በፍጹም ተቀባይነት የለውም።» ማርክ ሎውኮክ

በደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ከስልጣን ባባረሩዋቸው የቀድሞ ምክትላቸው ሪየክ ማቸር ደጋፊዎች መካከል በጎርጎሪዮሳዊው ታህሳስ 2013 ዓም በተነሳው ውጊያ ወደ 1,7 ሚልዮን ሕዝብ ከመኖሪያ አካባቢው ተፈናቅሏል። ተቀናቃኞቹ ወገኖች በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን፣ በምህጻሩ በኢጋድ ሽምግልና በተለያዩ ጊዚያት የፈረሙዋቸው የሰላም ስምምነቶች ሁሉ የጣሱ ሲሆን፣ ጓዱ ባወጣው መግለጫ መሰረት፣ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ንጣፍ በሚገኝበት የዩኒቲ ግዛት ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ ውጊያው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የአንሚስ ኃላፊ ዴቪድ ሺረር ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በዩኒቲ ግዛት ሆን ተብሎ በርካታ ሲቭሎች ሲገደሉ፣ ወሲባዊ ጥቃት ሲፈጸምባቸው እና ሴቶች እና ሕፃናትም ሲታገቱ ታይቷል፣  ተፋላሚዎቹ ወገኖች በኮህ አካባቢ  ቢያንስ በ30 መንደሮች ላይ የጣሉትን ጥቃት ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ ሌር አካባቢ ሸሽተዋል።  ከነዚሁ መካከል፣ በብዛትም ሕፃናት ባካባቢው በሚገኘው የተመድ ሰፈር ከለላ እና ርዳታ መሻታቸውን ዴቪድ ሺረር አስታውቀው፣ ሕግን በመጣስ ሲቭሎችን  የሚያጠቁ ሁሉ በኃላፊነት ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል።

Südsudan Flüchtlinge UNO
ምስል picture alliance/AP Photo/B. Mategwa

የደቡብ ሱዳንን ውዝግብ ለማብቃት የሚቻልበትን መንገድ የሚያፈላልግ  ያካባቢ ሀገራት፣ እንዲሁም፣ ዩኤስ አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ኖርዌይ የተጠቃለሉበት ቡድን፣ የሀይማኖት መሪዎች እና የመብት ተሟጋቾች ጭምር  የተሳተፉበት የሰላም ውይይት ከሁለት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ ሊጀመር ጥቂት ቀናት ሲቀሩት የተመድ የሰብዓዊ ርዳታ ጉዳዮች ክፍል ምክትል ዋና ጸሀፊ ማርክ ሎዎኮክ በደቡብ ሱዳን በመዘዋወር  ወቅታዊውን ሁኔታ ተመልክተዋል። ስለአሳሳቢው ሁኔታም ከተቃዋሚ ቡድኖች መሪዎች እና ከመንግሥት ተወካዮች፣ እንዲሁም፣ በወዝግቡ አብዝተው ከተጎዱት ተፈናቃዮች ጋር ተወያይተዋል።

ሎውኮክ በማዕከላይ ኢኳቶርያ ግዛት ያነጋገሯቸው የተቃዋሚው ኤስፒኤልኤ አይ ኦ ተጠባባቂ መሪ ፒተር ሊዦ ጆሴፍ ለሕዝብ መቆሙን አረጋግጠውላቸዋል። «የሰላሙ ድርድር የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ ጥቅም እንዲያስቀድም እንፈልጋለን። ሕዝቡ የድርድሩ ማዕከል በሚሆንበትም ጊዜ በሀገሪቱ ሰላም እንደሚወርድ እርግጠኞች ነን።»  

በአምስት ቀኑ የአዲስ አበባ የሰላም ውይይት ላይ የተገኙት ያካባቢ እና ዓለም አቀፍ መሪዎች የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች ውዝግቡን ማብቃት ባለመቻላቸው ወቀሳ አቅርበዋል።  የተመድ የሰብዓዊ ርዳታ ጉዳዮች ክፍል ምክትል ዋና ጸሀፊ ማርክ ሎዎኮክ በዬይ ግዛት ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ተወካዮች ጋር በተገናኙበት ጊዜ ሲቭሉ ሕዝብ የጥቃት ዒላማ መሆኑ በፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል።«የተራው ሰው ስቃይ ከምታስበው በላይ ነው። የሰላሙ ሂደት እስካሁን ያስገኘው ፋይዳ የለም። የኃይል ተግባር ቆሟል መባሉ የፈጠራ ወሬ ነው። የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ወድሟል። ተፋላሚዎቹ የሽምቅ ውጊያ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። የነፍስ ግድያ እና ክብረ ንፅህና መድፈርን እንደ ጦር መሳሪያ የጠቀሙባቸዋል።  እነዚህ ሁሉ ዓለም አቀፍ ሕጎችን የጣሱ ግዙፍ ወንጀሎች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ሰባት ሚልዮን ሕዝብ የሰብዓዊ ርዳታ ያስፈልገዋል፣ ሁኔታዎችም እየከፉ በመሄድ ላይ ናቸው። »

USA David Shearer
ምስል picture alliance/ZUMAPRESS/A. Lohr-Jones

የደቡብ ሱዳንን ሲቭል ሕዝብ ለመርዳታ የሚንቀሳቀሱት  የርዳታ ድርጅቶች ሰራተኞች  ስራቸውን እንዳይሰሩ የሚያጋጥማቸው ጥቃት፣ ግድያ እና መሰል ድርጊት አሳዛን እና አሳፋሪ መሆኑን ዴቪድ ሺሬር አክለው አስታውቀዋል። በመሆኑም፣ ውዝግቡ የሚመለከታቸው ሁሉ ሰላም ለማውረድ እንዲጥሩ  ዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ባለስልጣን ማርክ ሎዎኮክ ተማፅነዋል።

«በሀገሪቱ የሚታየውን ሰብዓዊ ስቃይ ለመቀነስ የኃይሉን ተግባር ማብቃት የመጀመሪያው እና ብቸኛው ዋነኛ ጉዳይ ይሆናል። ይሁንና፣ የኃይሉ ተግባር ብቻ አይደለም እየጨመረ የመጣው፣ የሰብዓዊ ርዳታ ወኪሎችም በሀገሪቱ ሕይወት ለማዳን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ያረፈባቸው   ገደብም በስራቸው ላይ ተጨማሪ እንቅፋት እየሆነ ተገኝቷል። ስለዚህ ፣ የሚያስፈልገን ወደ ርዳታ ፈላጊው ሕዝብ መድረስ የምንችልበት ፈጣን፣ አስተማማኝ እና ገደብ ያላረፈበት መንገድ ነው። »

በአዲስ አበባ የሰላም ድርድር የአፍሪቃ ህብረትን በመወከል የተሳተፉት የህብረቱ ምክትል ሊቀ መንበር ክዌይ ክዋቲ ደቡብ ሱዳን ባደረገችው ንዑስ ጥረት ህብረቱ በጣም ቅር መሰኘቱን  ገልጸዋል።

IGAD Logo

«የአፍሪቃ ህብረት በየቀኑ ሲብሎችን የሚገድሉትን ወይም ሲብሎች ለሚገደሉበት ድርጊት ድርሻ የሚያበረክቱትን ለመቅጣት በሚወስደውን ርምጃ አንጻር መቆም ለማንም ቢሆን ትክክለኛ አይደለም።  የአፍሪቃ ህብረት ከኢጋድእና ከሌሎች አጋሮች ጋር ባንድነት በመሆን  ሰላም ለማውረድ የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉትን ለመቅጣት ሳያመነታ እና ሳያሰልስ መስራቱን ይቀጥላል።»

ድርድሩን በሸምጋይነት እየመራ ያለው ኢጋድ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች የፈረሟቸውን የሰላም ስምምነቶች እንዲያከብሩ ጥረት ቢያደርግም፣ እስካሁን አልተሳካለትም። ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን በያዘው ድርድር ላይ ተቀናቃኞቹ ወገኖች በተለይ አካራካሪ በሆኑት ቁልፍ ጉዳዮች፣ ማለትም፣ በስልጣን ክፍፍሉ እና በፀጥታ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ አስማሚ ገላጋይ ሀሰብ ላይ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ  በአዲስ አበባው ውይይት የሲቭሉን ማህበረሰብ በመወከል ከተሳተፉት መካከል አንዱ የሆኑት ሳይሞን አኩዴንግ ለዶይቸ ቤለ ገልጸዋል።

«ገላጋይ ሀሳብ ላይ ይደረስባቸዋል ተብለው ተስፋ  ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል  በመንግሥቱ ውስጥ የስራ አስፈፃሚው መዋቅር፣ ማለትም፣ የፕሬዚደንቱ ፣ የምክትል ፕሬዚደንቱ ጽህፈት ቤት እና  የሌሎቹ መያዝ ያለባቸው ከፍተኛ ስልጣኖች መልክ ምን ይመስላል?  እንዲሁም፣ ሌላው ደግሞ የስልጣን ክፍፍሉ ተመጣጣኝነት፣ ብሎም፣ የካቢኔው አደላደል፣ ሶስተኛው፣ በሀገሪቱ የሚኖሩት ግዛቶች ቁጥር ይጠቀሳሉ። ምን ያህል ግዛቶች ሊኖሩ ይገባል የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ አንዳንዶች 10 ሲሉ ፣ መንግሥት 32 ብሏል፣ ይህ ጉዳይ መፍትሔ ሊገኝለት ይገባል።  አራተኛው ጉዳይ ደግሞ የሕግ አውጪውን አካል የሚመለከት ነው።»

ሌላው የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞችን እያወዛገበ የሚገኘው ጉዳይ የፀጥታውን ጥያቄ ይመለከታል። የሀገሪቱ መንግሥት ዓማፅያን ቡድኖች በብሔራዊው ጦር ውስጥ እንዲዋኃዱ ሲጠይቅ፣ ተቃዋሚዎች የመንግሥቱ የኤስፒኤል ጦር ተበትኖ አዲስ ጦር እንዲቋቋም ነው የሚፈልጉት። 

Südsudan Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo/J. Lynch

በድርድሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ሱዳን አንግሊካን ቤተ ክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ጃስቲን ባዲአራማ ተቀናቃኞቹ ወገኖች ልዩነታቸውን በማስወገድ ውዝግቡን ባፋጣን እንዲያበቁ አሳስበዋል።«በዓለም ታሪክ እንደታየው፣ ሁሉም ጦርነቶች የሚያበቁት በውይይት ነው። በወታደራዊ ርምጃ የሚገኝ ድል አይደለም ጦርነትን የሚያበቃው። እና ሕዝባቸውን የሚወዱ ከሆነ፣ ሕዝቡ ከመጥፋቱ በፊት፣ የሕዝቡን ፍላጎት በማድመጥ ሰላምን መቀበል አለባቸው።»

የሽግግሩ መንግሥት ዘመን በዚህ በተያዘው የግንቦት ወር ከማብቃቱ በፊት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከተቀናቃኞቹ ወገኖች ጋር አንድ የሰላም ስምምነት እንዲደርስ ዓለም አቀፍ ግፊት ተጠናክሮበታል። 

አርያም ተክሌ

ተስፋለም ወልደየስ