1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዝዳንቱ እና የአማጽያኑን መሪ ለፍርድ ይቅረቡ - ስደተኞች

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 19 2010

በደቡብ ሱዳን መንግስት እና በአማጽያኑ ጦር መካከል በላሱ ከተማ ዳግም ያገረሸው ግጭት በሰላም ድርድሩ ስኬት ላይ ጥርጣሬን ማስከተሉ ተገለጸ። ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ አጎራባች ሃገራት የሚሰደዱ ደቡብ ሱዳናውያንም በተለይም በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጦር ከፍተኛ ስቃይ እና በደል እንደሚፈጽምባቸው ታውቋል።

https://p.dw.com/p/2q47l
Kongo Flüchtlinge aus dem Südsudan
ምስል Simona Foltyn

ፕሬዝዳንቱ እና የአማጽያኑን መሪ ለፍርድ ይቅረቡ - ስደተኞች

በደቡብ ሱዳን መንግስት እና በአማጽያኑ መካከል በላሱ ከተማ ዳግም የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በርካታ ደቡብ ሱዳናውያን ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ አጎራባች ሃገራት፤ ዲሞክሪቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ መፍለሳቸው ታውቋል። ይሁንና በተለይም በድንበር አካባቢ የሰፈረው የኮንጎ ወታደራዊ ጦር ወደ ሃገሩ ዘልቀው እንዳይገቡ ከፍተኛ ግፍ፣ ስቃይ እና የሃይል እርምጃ እየፈጸመባቸው እንደሆነ ነው ስደተኞቹ የሚገልጹት።

በደቡብ ሱዳን መንግስት እና በአማጽያኑ ቡድን መካከል ድርድር እና አዲስ የተኩስ አቁም ውል ከተፈረመ ከሰዓታት በኋላ ያገረሸው ይኸው ግጭት በሰላም ድርድሩ ላይ ደመናን አጥልቶበታል። ለረጅም ጊዜ የተካሄደው የሰላም ውይይት አመርቂ ውጤት ባለማምጣቱም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ስምምነቱ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ አስፈላጊውን ጫና ሁሉ እንዲያሳድር የላሱ ከተማ ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

Die aus dem Südsudan geflüchtete Jenty Jendia
ምስል Simona Foltyn

ጄኒት ጄንድያ፤ ኮንጎ ድንበር አቅራቢያ፣ አባ ከተማ በሚገኘው የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከሚኖሩት ስደተኞች አንዷ ናት። በትውልድ መንደሯ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከአካባቢው ሸሽታ የተሰደደችው ጄኒት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ውል ወረቀት ላይ ከመስፈሩ ውጭ ተግባራዊ አለመሆኑ እንዳሳዘናት እና በገሃድ ዕውን ሆኖ የማየት ምኞት እንዳላት ትናገራለች። «አንድ ሰዎችን የሚያስማማን ነገር አለ። የሰላም ስምምነት ውሉ በወረቀት ላይ ተፈርሟል። ይሁን እንጂ ከወረቀት አልፎ ውይይት እና ድርድሩ በተግባር ተፈጽሞ ማየት የዘወትር ምኞቴ ነው» ብላለች ጄኒት።

ሪቻርድ ሞይ ሌላው በቅርቡ በላሱ የተቀሰቀሰውን ግጭት ሸሽቶ የተሰደደ የደቡብ ሱዳን ዜጋ ነው። ለብዙዎች ሞት እና ስደት ተጠያቂ የሆኑት የአማጽያኑ መሪ እና የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ የብዙዎች ምኞት መሆኑን ያስረዳል። «የሰላም ድርድሩ አዲስ አበባ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ ቆይቷል። ሆኖም እስካሁን የረባ ውጤት አላመጣም። በሃገሪቱ የነገሰው ደም አፋሳሽ ብጥብጥ ያበቃ ዘንድ እንደ አሜሪካ ያሉ ሃያል ሃገራት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን እና የአማጽያኑን መሪ ሪየክ ማቻርን ለፍርድ ሊያቀርቧቸው ይገባል» ብሏል። 

በደቡብ ሱዳን መንግስት እና አማጽያኑ ጦር መካከል ዳግም በተቀሰቀሰው ግጭት የመንግስት ጦር የአማጽያኑ ጠንካራ ዋና ይዞታ የሆነውን የላሱን ከተማ መቆጣጠሩ ታውቋል። በአባ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መጠለያ ሃላፊ ሊዋ ሞሪስ የላሱ አካባቢ ነዋሪዎች ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በሃገሪቱ መንግስት ጦር እጅ እስካለ ድረስ ወደ ትውልድ ቀያቸው የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራሉ። 

Flüchtlingslager im Kongo nahe Aba
ምስል Simona Foltyn

«ቀደም ሲል የላሱ ከተማ በአማጽያኑ ይዞታ ስር ነበረች ። የሃገሪቱ ሰራዊት አካባቢውን መቆጣጠሩ ስጋት የፈጠረባቸው የመንደሩ ነዋሪዎች ከቦታው ሸሽተዋል። በአሁኑ ወቅት አያሌ ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ይገኛሉ» ሲሉ በስደተኞች ጣቢያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል። በደቡብ ሱዳን ዳግም ላገረሸው ግጭት መንግስት እና አማጽያኑ እርስ በእርስ መወነጃጀላቸውን ቀጥለዋል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ነጋሽ መሐመድ