1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያንዣበበው ረሀብ፤ H.R. 6600፤ የዩክሬን ጦርነትና ኔቶ

ዓርብ፣ መጋቢት 16 2014

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችን በኢትዮጵያና የምሥራቅ አፍሪቃ ስላንዣበበው የረሀብ አደጋ፤ ስለ H.R. 6600 ረቂቅ ሕግ ላይ እንዲሁም የዩክሬን ጦርነት እና የሩስያ ኔቶ ፍጥጫ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል። አስተያየቶቹ ከታች በድምፅም በጽሑፍም በዝርዝር ቀርበዋል። 

https://p.dw.com/p/490Cv
Belgien | Nato-Sondergipfel zum Ukraine-Konflikt
ምስል Eric Lalmand/BELGA/dpa/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅት በድምፅ

«ኢትዮጵያ የመረጋጋት፤ የሠላም እና የዴሞክራሲ ጥረቶችን ለመደገፍ» በሚል ርእስ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ዕየታየ ያለው ረቂቅ ሕግ ሰሞኑን ኢትዮጵያውያንን እሁለት ጎራ ከፍሎ እያነጋገረ ነው። አሜሪካ እጃችንን ልትጠመዝዝ፤ ያልፈለግነውንም ኃይል ዳግም ልትጭንብን ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን ያሰሙ በርካቶች ናቸው። ከዚህ የባሰ ግፍ እና መከራ ሀገራችን ላይ አይደርስም፤ ይህን ማስተካከል ያልቻለው መንግሥት ሊቀጣ ይገባል ስለዚህ ሕጉ መጽደቅ አለበት የሚሉም ብዙዎች ናቸው። ኦክስፋም፦ በአፍሪቃ ቀንድ 13 ሚሊዮን ሕዝብ ላይ የተደቀነው ረሀብ ትኩረት ካልተሰጠው «የከፋ እልቂት ያስከትላል» ሲል አስጠንቅቋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰውነት ውጪ የሆኑ፤ በአጥንት ቆዳቸው የቀሩ ሕጻናት ምስሎች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች እየተዘዋወሩ ነው። ሩስያ የዩክሬን ድብደባዋን ቀጥላለች። ኃያላኑ እነ ኔቶ በኃያሊቱ ግራ ተጋብተው ተደጋጋሚ ስብሰባ ይዘዋል።

በኢትዮጵያ ያንዣበበው ረሀብ

ኢትዮጵያ ውስጥ በረሀብ እጅግ የተጎዱ ህጻናት አስደንጋጭ ምስሎች ሰሞኑን በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች እየተዘዋወሩ ነው። በተለይ በርካታ ምስሎቹ የሚያሳዩት ዋግ ሕምራ ውስጥ ያለውን አሰቃቂ የሰብአዊ ሁኔታ ነው።

Äthiopien Tigray Hilfe Symbolbild
ምስል AP Photo/picture alliance

ሠናይት አማረ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ዋግ፤ ከረሀብ ጦርነት ይሻላል። ጦርነትና ረሀብ በአንድ ላይ ግን መራር ሰቆቃ ነዉ» ሲሉ ጽፈዋል። «ሕዝባችን ረፍት እንዳያገኝ ለምን ተፈረደበት ሲሉ የሚጠይቁት ደግሞ የመነን እናት የተባሉ ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው። «ዋግ በርሀብ እያለቀ ነው። ጦርነት፤ ረሀብ በስንቱ ነው ይህ ህዝብ መከራውን የሚያየው መቼ ነው የሚያባራው ይጠይቃሉ።

«ወገኔ ስንቱን ይቻለውከጦርነትና ከመታረድ አመለጥኩ ሲል…» ብለው ጽሑፋቸውን የሚያንደረድሩት ልዩ ፍቅር የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው። «ሰው ሠራሽ» ያሉትን «ረሀብ እና ቸነፈር ደግሞ አዘጋጁለት» ሲሉም አክለዋል። «አንዱ በቅንጦት ሲሽቆጠቆጥ ሌላው የሚቀምሰው ጠፍቶ አጥንቱ እየተቆጠረ የሚኖርባት ሀገር» ሲሉም ምሬታቸውን አንጸባርቀዋል።  «ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል ከሚል ርእስ ስር እጅግ በጣም ቆዳቸው ከአጥንታቸው ጋር የተጣበቁ የተለያዩ ሕጻናት ፎቶግራፎች የሚታዩበት ምስልም ከጽሑፍ መልእክታቸው ጋር አያይዘዋል።

በአማራ ክልል በሕወሓት ቁጥጥር ስር ከሚገኙ የዋግ ሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የዝቋላ ወረዳ አንዳንድ ቀበሌዎች የሚፈናቀሉ ሕፃናት በከፍተኛ ምግብ እጥረት የተጋለጡ መሆናቸውን የዝቋላ ወረዳ ጤና ጽ/ቤትም በዚሁ ሳምንት ለዶይቸ ቬለ ዐስታውቋል።

አብድራኅማን ሞሐመድ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «አፍሪቃ ስትረገዝም፣ ስትወለድም፣ ስትኖርም፣ ስትሞትም ረሀብ ነው» ሲሉ ጽፈዋል። በምሥራቅ አፍሪቃ የተደቀነው መጠነ ሰፊ ረሀብ አፋጣኝ ምላሽ ካላገኘ ወደ «ብርቱ እልቂት» ሊቀየር እንደሚችል ኦክስፋም ማስጠንቀቁን በዚሁ ሳምንት ዘግበናል። ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያንና ኬንያን በመታዉ ድርቅ ለረሀብ የተጋለጠው ሕዝብ 13 ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት መርኃ ግብር(WFP) ካሳወቀ ሁለት ወር ሊደፍን ነዉ።

H.R. 6600 ረቂቅ ሕግ

ረቡዕ ዕለት በአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት/ ሴኔት የቀረበው S3199 የተባለው እና H.R. 6600 የተሰኘው ረቂቅ ሕግጋት ላይ በርካታ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። በአሜሪካ ምክር ቤትና ሕግ መወሠኛ ምክር ቤት(ሴኔት)ኢትዮጵያን አስመልክቶ በቅርቡ የቀረቡት ረቂቅ ሕግጋት በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በአንድ ወገን ተቃውሞ በሌላው ደግሞ ድጋፍ እየቀረበባቸው ነው።

USA Kapitol Washington
ምስል J. Scott Applewhite/AP/picture alliance

እነዚህን ሕግጋት በተመለከተ ከተሰጡ የድጋፍ መልእክቶች መካከል መቲ ፋንታ በፌስቡክ በአጭሩ ቀጣዩን ብለዋል። «ፈጣሪ ረድቶን ቶሎ በፀደቀ።»  ሌላኛው የፌስቡክ ተጠቃሚ «አፍጥኝው አሜሪካ» ይላሉ እሳቸውም፤ የነገን ማን ያቃል በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው። አንዱዓለም ዘወይንሸት በፌስቡክ መልእክታቸው፦ «እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ነዉ ነገሩ። እንዴት ሰዉ በእናት ሀገሩ ላይ ማእቀብ እንዲጣል ይመኛል በማለት ሕግጋቱ ተግባራዊ እንዳይሆኑ ጠይቀዋል። «የኢትዮጵያን ሠላም እየነሳች ያለችው ራሷ አሜረካ ናት» ሲሉ ተቃውሟቸውን ያሰሙት ደግሞ ዘማች አምቦ ናቸው። «S3199 እና H.R. 6600 እደግፋለሁ። ሊጸድቁ ይገባል» መልእክቱ የሐቃ ቢያ ነው።«HR6600 ከፀደቀ በብሄር ለይቶ አይደለም የሚጎዳህ። መላ ኢትዮጵያዉያንን ነዉ የሚጎዳው» ይላሉ ዳንኤል አስፋው።  «አሁን ያለው የኑሮ ዉድነት በእጥፍ እጥፍ ነዉ የሚጨምረው። ስለዚህ እንዳይፀድቅ ድምፅህን ብታሰማ ነዉ የሚሻልህ። ለመንግሥት ስትል ሳይሆን ለራስህ ስትል» ሲሉም ያክላሉ።

H.R. 6600 ረቂቅ ሕግ ለምን እንደተዘጋጀ በረቂቁ በአንቀጽ 2 የፖሊሲ ማብራሪያ ቁጥር 1 ላይ እንዲህ ተዘርዝሯል። «በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነትን እና ግጭቶችን ለማስቆም፤ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኙ የሰብአዊ መብቶች ላይ የደረሱ መጠነ ሰፊ ጥሰቶችን፤ የጦር ወንጀሎችን፣ በሰብአዊነት ላይ የደረሱ ወንጀሎችን፣ የዘር ማጥፋቶችን እና ሌሎች ጥሰቶችን ለማብቃት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ» ረቂቅ ሕጉ መዘጋጀን አርቃቂዎቹ ይጠቅሳሉ።  ቁጥር 2 ላይ፦ «ኢትዮጵያ ውስጥ ኹከቶችን አስወግዶ መረጋጋት እንዲኖር ሁሉንም የዲፕሎማሲ፤ የልማት እና ሕጋዊ መሣሪያዎችን ለመጠቀም» ይላል። በቁጥር 3 ደግሞ፦ በተራ ቁጥር 1 የተዘረዘሩ ወንጀሎች ፈጻሚዎችን «ተጠያቂ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ነው» ይላል። 4ኛ ቁጥር፦ «ሠላማዊ፤ ዴሞራሲያዊ እና አንዲት ኢትዮጵያን ለማምጣት ይቻል ዘንድ ሁሉን አሳታፊ ብሔራዊ ውይይትን ለማበረታታት» እንደሆነ ይጠቅሳል። ቀሪው ረቂቅ ሕጉ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ሊወሰዱ ስለታቀዱ ርምጃዎች የተጠቀሱበት ዝርዝር ነው።

Äthiopien Botschafter Dina Mufti
ምስል Press Office Ambassador Dina Mufti

የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ረቡዕ ዕለት በሰጠው ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሁለቱንም ረቂቅ ሕግጋት አጣጥሏቸዋል። «የዳቦ ስም የተሰጣቸው» ያላቸውን እነዚህን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተዘጋጁ ሁለት ረቂቅ ሕግጋት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፦ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ደኅንነት ጥገኛ የሚያደርጉ ብሏቸዋል። ሕግጋቱ በአሜሪካ መንግሥት የሚፀድቁ ከሆነ የሁለቱን አገራት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ክፉኛ ይጎዳሉ ሲሉ ምክትልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ መናገራቸውም በሐሙስ፤ የመጋቢት 15 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ መግለጫ ተጠቅሷል።

ፉዓድ ሙስጠፋ ዓሊ ትግራይ ውስጥ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዩናይትድ ስቴትስ ሕወሓትን በመደገፍ ላይ መሆኗን ገልጠው በትዊተር መልእክታቸው ጽፈዋል። ረቂቅ ሕጉንም እንዲህ ተቃውመዋል። «የሕወሓት ዳግም ሥልጣን የመያዝ ግቡን ለመደገፍ ስትል አሜሪካ ኢትዮጵያን መስማት ትታ ሕወሓትን ለመርዳት ማንኛውንም ነገር እያደረገች ነው። እናም አሁን ፕሬዚደንት ባይደን የመጨረሻ ካርዳቸውን HR6600 መዝዘዋል» ሲሉ የአሜሪካ መንግስትን ወቅሰዋል።

«እኔ በበኩሌ እደግፈዋለሁ። ሰው እየነደደ፤ ፍትህ ጠፍቶ ሰው ወጥቶ እየቀረ ባለበት ሀገር ፍትህ ያስፈልጋል ለህዝቤ። ስለዚህ ይህን ሕግ እደግፈዋለሁ። HR6600 ይፅደቅ» ይላሉ ገብረመስቀል ካሳው በፌስቡክ ገጻቸው። «እንደ አንድ ደሀ ይፅደቅ ባይ ነኝ።» አስተያየቱ የጌትነት ገብረ መድኅን ገብረ ሥላሴ ነው። «ዩክሬን ተወራ የለ በሩስያ። አሜሪካን ለምን ለሰው ልጅ ተቆርቋሪ ከሆነች ለዩክሬን አልደረሰች ሲሉ ይጠይቃሉ፤ ሰለሞን የማነ በፌስቡክ። በዚሁ የዩክሬን ጦርነት እና የምዕራባውያን አጸፌታ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ወደሚቃኘው ቀጣዩ ርእሰ ጉዳይ እንሻገር።

የዩክሬን ቀውስና ኔቶ

Ukraine | zerstörte Russische Militärfahrzeuge in Bucha
ምስል Serhii Nuzhnenko/AP/picture alliance

ዩክሬን ውስጥ የገባሁት ለ«ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮ» ነው በማለት ሩስያ ዩክሬንን በጦር ሠራዊቷ ወርራ መደብደብ ከጀመረች አራት ሳምንታት ተቆጥረዋል። በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል፤ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አውሮጳ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል። ሩስያ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO)መስፋፋቱን ቀጥሎ አፍንጫዬ ስር ደርሷል፤ ይህም ለደኅንነቴ ስጋት ነው ስትል ጦርነቱን መጀመሯን ትገልጣለች።

ምዕራባውያን ሃገራት እና ኔቶ ሩስያ ያለትንኮሳ ኢፍትኃዊ ጦርነት ጀምራለች ሲሉ ሩስያን ከመኮነን ባሻገር የተለያዩ ማዕቀቦችን እየጣሉባት ነው። በቀጥታ በጦርነቱ መሳተፉን ቢሰጉም የዩክሬን መንግሥት ግን መታገሉን እንዲቀጥል የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ናቸው። ይህንኑ ድጋፋቸውን ለማጠናከርም የኔቶ አባላት ሐሙስ ዕለት ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገዋል። ኔቶ፣ የአውሮጳ ኅብረት እና የቡድን 7 አባል ሃገራት ባካኼዱት ስብሰባም የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲንን አውግዘዋል። በምሥራቅ አውሮጳ ሃገራትም ኔቶ ጦሩን ለማጠናከር ወስኗል። ከ1,000 እስከ 1,500 የሚደርሱ የኔቶ አባል ሃገራት ወታደሮችን ከሩስያ በቅርብ ርቀት በሚገኙት ስሎቫኪያ፣ ሐንጋሪ፣ ሮማኒያ እና ቡልጋሪያ ለማስፈር የኔቶ አባላት ተስማምተዋል። ቀደም ሲልም የኔቶ ጦር በአራቱ የባልቲክ ሃገራት እና ፖላንድ ውስጥ ይገኛል። ኔቶ ይህንን እና ሌሎች ርምጃዎችን ቢወስድም ዋነኛ ፍልሚያውን ግን ዩክሬናውያን ራሳቸው እንዲወጡት ትቶታል።

Belgien | Nato-Sondergipfel zum Ukraine-Konflikt
ምስል Markus Schreiber/AP Photo/picture alliance

«የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም ኔቶ ማለት እንደዚያ ነው» ይላሉ አምባቸው ደጀኔ ኔቶ በሩስያ ዙሪያ ከመሽከርከር ውጪ ዩክሬናውያንን ደግፎ በቀጥታ በጦርነቱ ተሳታፊ ባለመሆኑ። የኔቶ እና ምዕራባውያን ርምጃን በተመለከተ «ለምን ሲሉ ይጠይቃሉ ፋንታዬ ታደሰ።  ይቀጥላሉ፦ «ሌሎች ሀገሮች የኅልውና ችግር ሲገጥማቸው ለምን ይከላከላሉ እያሉ መአቀብ እየጣሉና አሸባሪዎችን እየረዱ ለራሳቸው ግን ይህን ይላሉ» ሲሉም አክለዋል። ውልጫፎ ነጋሽ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ የዩክሬን ሩስያ ጦርነት ዳፋው ሌላ ቦታ መድረሱን በተመለከተ፦ «ለኢትዮጵያም ተፅዕኖ አለው» ብለዋል። «ለመላው የሰው ልጆች ሁሉ ሰላም» ያሉት ደግሞ ገነት አብርሃም ናቸው። «ጦርነትን አቁሙ።» የዳኒ ዓሊ አጭር መልእክት ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

አዜብ ታደሰ