1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 25 2014

በጎርጎሮሳዊው 2021 በዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ በ24 የአፍሪካ አገሮች የፖሊዮ ወረርሽኝ እንደተከሰተ አስታውቋል። የወረርሽኙ ብዛት ከቀደመው ዓመት በአራት ከፍ ያለ ነው። ፖሊዮ በተባለ ቫይረስ ሳቢያ የሚከሰተውን የልጅነት ልምሻ በሽታ ለመከላከል ኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከአምስት በታች ለሆኑ ሕጻናት ክትባት ስትሰጥ ቆይታለች።

https://p.dw.com/p/4Akrs
Äthiopien Polio Impfung in der Amhara Region
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ጤና እና አካባቢ፦ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ

ፖሊዮ (ፖሊዮሚለትስ)  ተብሎ የሚጠራው የልጅነት ልምሻ በሽታ በ1800 አከባቢ እንደተከሰተ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡ የልጅነት ልምሻ በዋናነት የሚያጠቃው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ሲሆን ከሰው ወደ ሰው በንክኪ፣ በቫይረሱ በተበከለ ምግብ እና ውሀ አማካኝነት ወደ ሰውነት ሲገባ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በሽታው ዓይነት 1 ዓይነት 2 እና ዓይነት 3 በሚባል ይታወቃል፡፡በሽታው በዘላቂነት የሰውን የአካል ቅርፅ በመቀየር ለአካል ጉዳት የሚዳርግ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያስረዱት በሽታው ለሞትም ያደርሳል፡፡

እንደ የዓለም ድርጅት ሪፖርት ፖሊዮ በ1900 በወረርሽኝ መልክ በኢኮኖሚ አደጉ በተባሉ አገሮች ተከስቷል። በሽታው በህክምና የማይድን መሆኑን የተረዳው የዓለም የጤና ድርጅት በ1988 እ ኤ አ በሽታውን በክትባት መከላከል የሚያስችል ስልት በመቀየሱና ተግባራዊ በማድረጉ በወቅቱ የልጅነት ልምሻ በነበረባቸው 125 አገራት በየዓመቱ  ይመዘገብ የነበረው 350ሺ የልጅነት ልምሻ በሽታ  በዓመት ወደ 175 መውረድ ችሏል፡፡

ኢትዮጵያም የልጅነት ልምሻን በክትባት ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ዓባይነህ ተናግረዋል፡፡“በአስመዘገበቸው ውጤትም ኢትዮጵያ ከፖሊዮ ነፃ ተብላ የምስክር ወረቀት አግኝታ ነበር” ሲሉ ነው ያመለከቱት፡፡ ኢትዮጵያ ብቻም ሳሆን አፍሪካም ከበሽታው ነፃ ተብላ የነበረ ቢሆን በሶማሌ ክልል የፖሊዮ ቫይረስ ያለበት ግለሰብ በመገኘቱ ክትባቱ እንደገና እንዲጀመር ምክንያት መሆኑን ነው አቶ አስቻለው የገልፀዋል፡፡

በሽታውን ለመከላከል ክትባት ዋናው መፍትሔ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ናቸው፡፡ ጥቅምት 2014 ዓ ም በተደረገ የመጀመሪያ ዙር ክትባት ከ2 ሚሊዮን በላይ ህፃናት መከተባቸውን አስረድተዋል፡፡

Äthiopien Polio Impfung in der Amhara Region
ፖሊዮ በተባለ ቫይረስ ሳቢያ የሚከሰተውን የልጅነት ልምሻ በሽታ ለመከላከል ኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከአምስት በታች ለሆኑ ሕጻናት ክትባት ስትሰጥ ቆይታለች። ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በነበረው ጦርነት ምክንያት ክትባቶችን ያልወሰዱ አካባቢዎች እንደነበሩ የገለፁት አቶ በላይ በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና በደሴ ከተማ ሁለቱንም ዙር ክትባቶች ለመስጠት ታቅዷል ብለዋል፡፡በመጀመሪያው የክትባት ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ16 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህፃናት ክትባት መሰጠቱንም አቶ አስቻለው አመልክተዋል፡፡

በቅርቡ ሁለተኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት የተሰጠ ሲሆን በአማራ ክልል 2 ሚሊዮን 379ሺህ 935 ህፃናትን ለመከተብ ታቅዶ፣ 2 ሚሊዮን 463ሺህ 616 (103%) ህፃናትን መከተብ መቻሉን ደግሞ በአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፍቅረማሪያም ዮሴፍ ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡

ክትባቱ ከተሰጠባቸው ጤና ጣቢያዎች መካከል በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የሀን ጤና ጣቢያ አንዱ ነው። የጤና ጣቢያው የህክምና ባለሙያ አቶ ጌታቸው ዘለቀ ህብረተሰቡ በመርፌ ከሚሰጥ ክትባት ይልቅ በአፍ የሚወሰድ ክትባት አማራጩ በመሆኑ 5ሺህ 300 ታቅዶ 6ሺህ 200 ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል በሁሉም ክትባቱ በተሰጠባቸው አካባቢዎች የተሻለ ውጤት መመዝገብ የተቻለው ከክትባት በፊት በተሰጠው ስልጠና፣ በክትባት ወቅት በተደረገ ጠንካራ ክትትልና የሐይማኖት አባቶች ጭምር ስለክትባት ጠቃሚነት በአደረጉት ቅስቀሳ  እንደነበር የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት አመልክቷል፡፡

ከሚያዝያ 7-10/2014 በተሰጠው ሁለተኛ ዙር አገር አቀፍ ክትባት ከ16 ሚሊዮን በላይ ህፃናትን ለመከተብ ታቀደ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ክልሎች ሪፖርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ማዕከል ባለመላካቸው በሁተኛው ዙር በአገር አቀፍ ደረጃ የተከተቡት የህፃናት ቁጥር በዚህ ፕሮግራም ማካተት አልተቻለም፡፡

ዓለምነው መኮንን