1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕላስቲክ ብክለት መዘዞች

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 5 2012

አሁን የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎችን ያሳሰበው የፕላስቲክ ውዳቂዎች ክምችት ብቻ ሳይሆን በለውጥ ሂደቱ በአፈርም ሆነ በውኃ አካላት ላይ የሚያስከትሉት ብክለት ነው። በቅርቡ በደቡብ ኢትዮጵያ ቦረና ዞን ውስጥ ከብቶች የሚጣሉ ላስቲኮችን ከምግብ ጋር አብረው እየበሉ ለጤና እክልና ለሞት መዳረጋቸውን ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

https://p.dw.com/p/3gnzz
Äthiopien 50 kg Plastik aus dem Magen einer Kuh entfernt
ምስል Dr. Firaol Wako

«ቦሮና ዞን 50 ኪሎ ፕላስቲክ ከከብት ሆድ ወጥቷል»

በየቦታው የሚጣሉ ያገለገሉ ፕላስቲኮች የመላው ዓለም ችግር ከሆኑ ውለው አደሩ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የእነዚህ ፕላስቲኮች በምን ያህል ጊዜ ተበጣጥሰው በመበስበስ ወደአፈርነት ይቀየራሉ የሚለው ዛሬም ትልቅ ጥያቄ ነው። ምክንያቱም ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሂደቱ በመቶዎችና በሺህዎች በሚገመቱ ዓመታት ሊወስድ ይችላል። አሁን የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎችን ያሳሰበው የእነዚህ ፕላስቲኮች ክምችት ብቻ ሳይሆን በለውጥ ሂደቱ በአፈርም ሆነ በውኃ አካላት ላይ የሚያስከትሉት ብክለት ነው። በቅርቡ በደቡብ ኢትዮጵያ ቦረና ዞን ውስጥ ከብቶች የሚጣሉ ላስቲኮችን ከምግብ ጋር አብረው እየበሉ ለጤና እክልና ለሞት መዳረጋቸውን ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል። ዶክተር ፍራኦል ዋቆ በቦረና ዞን ዳስ ወረዳ የእንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ባልደረባ ናቸው። ከሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በሰኔ ወር ከአንዲት ጊደር ሆድ 20 ኪሎ የሚመዝን ፌስታል ያወጡ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ 50 ኪሎ የሚመዝን ፕላስቲክ ከከብት ሆድ በቀዶ ጥገና አውጥተዋል። የእንስሳት ህክምና ባለሙያው ለዚህ ዋናው ችግር ደግሞ ሰዎች ፕላስቲክ ቆሻሻን የሚያስወግዱበት ግዴለሽነት የተሞላው በመሆኑ ነው ይላሉ። የፕላስቲክ ቆሻሻ አወጋገድ በእንስሳት ብቻ ሳይሆን በሰው ጤናም ሆነ በአፈር ላይ የከፋ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑም መንግሥት አጠቃቀምና አወጋገድን የሚመለከት ደንብ ቢያወጣ እንደሚበጅም መክረዋል። በዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ የማይቻል ከሆነ ግን እንደሌሎች ሃገራት ፕላስቲክ ወደሀገር እንዳይገባ ማገዱ ይበጃልም ባይ ናቸው።

ቀዶ ህክምናውን ያካሄዱት ባለሙያዎች
ምስል Dr. Firaol Wako

ኢትዮጵያ የከብት ሃብት አላቸው ከሚባሉ ግንባር ቀደም ሃገራት ተርታ የምትሰለፍ መሆኗ ይታወቃል። ግን ደግሞ የእንስሳቱን ጤና በተመለከተ ያን ያህል ትኩረት እንዳልተሰጠ ከባለሙያው ለመረዳት ችለናል። አቶ አሬሮ ተሪ ከብቶቻቸውን በፕላስቲክ መዘዝ አጥተዋል፤ በቀዶ ህክምናም ከሆዳቸው ፕላስቲክ የወጣላቸውም አሉ። ከወራት በፊት ነበር ከብቶቻቸው ውኃ ለመጠጣት ከሄዱበት አካባቢ መመለስ ሳይችሉ ቀርተው በዚያው የሞቱት። ሲታረዱም ከሆድ ዕቃቸው ውስጥ በርካታ ላስቲክ መከማቸቱ ታወቀ። በዚህ ጊዜ ወደእንስሳት ሃኪሞች ዘንድ ለመውሰድ ወሰኑ። የእሳቸው ጊደር በቀዶ ህክምናው መዳኗን በማረጋገጣቸውም ሌሎች የአካባቢው አርብቶ አደሮች ይህን ርዳታ መፈለጋቸው የማይቀር ነው። ዶክተር ፍራኦል በቦረና ዞን አንድም እንኳ የረባ የእንስሳት ህክምና መስጫ እንደሌለ ነው የገለፁት። ለሁለቱ ከብቶች ቀዶ ህክምናውን ከሰው የጤና ባለሙያዎች በተገኘ ማደንዘዣ መሥራታቸውን ነግረውናል። ኢትዮጵያ እንዳላት የከብት ብዛት ለዘርፉ ትኩረት መሰጠት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከሆዷ ፕላስቲክ የወጣላት ጊደር
ምስል Dr. Firaol Wako

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ