1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፓሪሱ ጭፍጨፋ 60ኛ ዓመት

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 6 2014

የታሪክ አዋቂዎች እንደሚሉ፤ በአሁኑ ወቅት፤ ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ፤በፈረንሳይ የሚኖሩ ዜጎች፤ ከአልጀርያ ጋር ከባድ ቁርኝት እንዳላቸዉ ያምናሉ። እነዚህ ዜጎች አልጀርያ ከቅኝ ግዛት ስትላቀቅ አልጀርያን ጥለዉ ወደ ፈረንሳይ የመጡ ዜጎች ሊሆኑ፤ አልያም ከአልጀርያ ተሰደዉ የፈረንሳይ ዜግነትን የጠየቁ ዜጎች ሊሆኑ ይችላሉ።

https://p.dw.com/p/41keq
Frankreich Eiffelturm wegen Streiks weiter geschlossen
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Euler

ከ 30 ሺህ በላይ አልጀርያዉያን ለነፃነት ሰልፍ አካሂደዋል

በፓሪስ ላይ በአልጀርያዉያን ላይ የተፈፀመዉን ጭፍጨፋ 60 ኛ ዓመት መታሰብያ በተመለከተ በፈረንሣይ ቴሌቪዥን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

« በዚያን ጊዜ ፖሊሶች ባገኙት ነገር ሁሉ በመጠቀም ከፍተኛ የደም መፋሰስን ፈፅመዋል። እጃቸዉ ላይ ባገኙት ነገር ሁሉ፤ በብረት ዘንግ፤ አሎሎ መሰል ነገር ሁሉ ሳይቀራቸዉ ተጠቅመዋል» ሲል አልጀርያዊዉ ሳዓድ ኧዜን ያስታዉሳሉ። በጎርጎረሳዉያኑ ጥቅምት 17 ቀን፤ 1961 ዓ.ም በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ ላይ ወደ 30,000 የሚቆጠሩ አልጃሪያዉያን የነፃነት ንቅናቄ ሰላማዊ የተቃዉሞ ሰልፍ አድርገዉ ነበር። አልጀርያዉያኑ በፓሪስ ይህን ከፍተኛ የነፃነት ንቅናቄ ሰልፍ ከማድረጋቸዉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ፤ በፓሪስ ፖሊስ የፈረንሳይ ሙስሊሞች፤ ለሊት መንቀሳቀስ እንዳይችሉ የሚያግድ የሰዓት እላፊ አዋጅን ደንግጎ ነበር። የፈረንሳይ ፖሊሶች እና የፀጥታ አስከባሪዎች፤ ወደ ሠላሳ ሺህ የሚቆጠሩትን አልጀርያዉያን የነጻነት የተቃዉሞ ሰልፈኞች የጀመሩትን ሰልፍ በተኩስና በግድያ አስቆሙት። የዓይን እማኞች እንደሚናገሩት በ 1961 በፓሪስ ጎዳና ላይ የተካሄደዉ አስከፊ ጭፍጨፋ በመቶዎች የሚቆጠሩ አልጀርያዉያን ተገድለዋል፤ ተደብድበዋል፤ አልያም ፓሪስን ለሁለት ከፍሎ በሚፈሰዉ «ሴን» በተባለዉ ወንዝ ዉስጥ የዉኃ ሲሳይ እንዲሆኑ ተደርጎአል። ከዚህ ሌላ  በሽዎች የሚቆጠሩ አልጀርያዉያን ለቀናቶች ለእስር ተዳርገዉም ነበር።

የፈረንሳይ ፖሊሶች ለነፃነት በሚታገሉ አልጀርያዉያን ላይ የፈፀሙት የግፍ ጭፍጨፋ፤ ፍትህ እንዳይገኝ ለአስርተ ዓመታት በመንግሥት ባለስልጣናት ተደብቆ ቆይቶአል። መርማሪዎች እና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተከራካሪዎች፤ ምርመራን እንዳያደርጉ ታግደዉ ነበር። የፈረንሳይ የብዙኃን መገናኛዎች ጥቅምት 17 ቀን፤ 1961 ዓ.ም በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ ላይ በተካሄደዉ ሰልፍ ላይ ሦስት ሰዎች ሞተዋል ሲል ዘግቦ ነበር። ቆየት ብሎ ደግሞ ስድስት ሰዎች ብቻ መሞታቸዉ ተዘግቦ ነበር። ይሁን እና እዉነታዉ ይህ  አልነበረም። የ 78 ዓመቱ የታሪክ ምሁር እና የታሪክ ስብስቦች ተመራማሪዉ ኤቲን ፍራንሷ እንደሚሉት፤ በዝያን ወቅት በፓሪስ ጎዳና ላይ ስለተካሄደዉ የአደባባይ ጭፍጨፋ ምንም አልሰማሁም ነበር ሲሉ ያስታዉሳሉ። በዝያን ወቅት በሰሜናዊ ምስራቅ ፈረንሳይ ኔንሲ ከተማ ዉስጥ የከፍተኛ ትምህርት ላይ የነበሩት የዛሬዉ የታሪክ ተመራማሪ፤ ቆየት ብሎ ስለነበረዉ ጭፍጨፋ ከብዙኃን መገናኛዎች ሳይሆን በዩንቨርስቲ ከሚያስተምሩ አንድ መምህር መስማታቸዉን ተናግረዋል።

«ከአልጄሪያዉ ጦርነት በአልጄሪያ ያለው ሁኔታ በጣም ጭካኔ የተሞላበት እና ከባድ እንደነበር እናዉቅ ነበር። ግን ይህ ሁሉ ሁኔታ ከአልጀርያ አልፎ እስከፈረንሳይ ዋና መዲና ፓሪስ ሊደርስ ይችላል ብለን የዛን ጊዜ በፍፁም አላሰብንም ነበር።» 

በፓሪስ ስለነበረዉ አስከፊ ጭፍጨፋ ከፈረንሳይ ባለስልጣናት በኩል ማንም ለተጠያቂነት አልቀረበም። በአንጻሩ ተጠያቂ ናቸዉ ተብለዉ ይታሙ የነበሩ ግለሰቦች በስልጣን በስልጣን ላይ ያገኙ ጀመር። በዚያን ወቅት የፈረንሳይ የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር የነበሩት ሮጀር ፍሬይ፤ የሕገ -መንግስታዊ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነዉ ሹመትን አገኙ። የፓሪስ የፖሊስ የበላይ ተጠሪ የነበሩት ደግሞ በወቅቱ በነበሩት ፕሬዚዳንት፤ የሃገሪቱ የበጀት ሚኒስትር ሆነዉ ተሾሙ።  

የአልጀርያ ጦርነት ሲባል የሚታወቀዉ ጦርነት ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ለመዉጣት አልጀርያዉያን ከጎርጎረሳዉያን ህዳር 1 ቀን 1954 ዓ.ም እስከ መጋቢት  19 ቀን 1962 ዓ.ም ድረስ የተካሄደ ጦርነት ነዉ።

እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር በ 1962 ዓ.ም አልጄሪያ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች በኋላ በፈረንሣይ ኅብረተሰብ ውስጥ “በአልጄሪያን ጦርነት የነበረዉን አስከፊ ታሪክ” የመርሳት ፍላጎት ነበር ሲሉ ታዋቂዉ የታሪክ ምሁሩ ፋብሪስ ሪሲፑቲ ይናገራሉ። በፈረንሳይ ስለየአልጄሪያዉ ጦርነት እና ከ 1830 ጀምሮ አገሪቱን በጭካኔ የወረረዉ የፈረንሳይ  ኃይል ጉዳይ የሚነገር ታሪክ አልነበረም። ከዛሬ 20 ዓመታት ወዲህ ግን ጉዳዩ በፈረንሳይ ትምህርት ቤቶች የሚነሳ ርዕስ ሆንዋል።  

ፋብሪስ ሪሲፑቲ  የአልጄሪያን ጦርነት አጠቃላይ ማህበራዊ ዳሰሳ ለማድረግ በሚታገሉ የፈረንሳይ የሳይንስ ምሁራን፤ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች የተካተቱበት ቡድን ዉስጥ አባል ናቸዉ።  ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ በፓሪስ በጥቅምት 17 ቱ እልቂት፤ የመንግስት ወንጀል ሲባል መጥራት አለበት ሲሉም  ይጠይቃሉ።  

«እኔ በግሌ እንዲህ ዓይነቱ ምደባ ትርጉም ያለው ይመስለኛል ምክንያቱም ከዚህ  ጭፍጨፋ እውነታ ጋር ይዛመዳልና ነዉ።» 

በእርግጥ የፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ዘመን ታሪክን በተመለከተ ፕሬዚዳንት ማክሮ ከሳቸዉ በፊት ከተሾመ ማናቸዉም የፈረንሳይ ፕሬዚዳንቶች ሁሉ በበለጠ ሁኔታ ተችተዋል፤ ነቅፈዋልም። ማክሮ በፈረንሳይ በጎርጎረሳዉያኑ 2017 ዓ.ም በተደረገዉ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ በእጩነት ሲቀርቡ በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት ፤ በሰው ልጅ ላይ ወንጀል የተፈፀመበት የቅኝ ገዥነትን ዘመን ሲሉ የምረጡኝ ዘመቻ ነጥባቸዉ አድርገዉትም ነበር።  በርግጥ ርዕሱ እስካሁን ያስገኘላቸዉ ነገር ባይኖርም፤ ከጥቂት ግዚያት በፊት ፕሬዚዳንት ማርኮ ፈረንሳይ ዉስጥ ከወጣቶች ጋር ስለ አልጀርያዉ ጦርነት እና ስለ ጥቅምት 17ቱ የፈረንሳይ ታሪክን በተመለከተ ንግግር ካደረጉ በኋላ በአልጀርያ እና በፈረንሳይ መካከል ያለዉ ግንኙነት ሻክሮአል።     

ፕሬዚዳንት ማክሮ በዉይይታቸዉ ወቅት፤ ስለአልጀርያዉ ታሪክ እዉነት ላይ ሳይሆን ሁኔታዉን በፈረንሳይ ላይ የተመሰረተ ጥላቻ ብለዉ በመናገራቸዉ በአልጀርያ መንግሥት በኩል ትልቅ ቁጣን ቀስቅሶአል።  የአልጀርያ መንግሥት የፕሬዚዳንት ማክሮን ንግግር ተከትሎ፤ ፓሪስ የሚገኘዉን አምባሳደር ጠርታለች። ከዚህ ሌላ አልጀርያ ፈረንሳይ ለወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ትጠቀምበት የነበረዉን የአልጀርያ የበረራ አየር ክልልም ዘግታባታለች። በዚህም ፈረንሳይ በማሊ ለሰፈሩ ወታደሮችዋ የምታጓጉዘዉ ቁሳቁስ  በበረራ መስመር ማጣት እና መዛወር ምክንያት ዘግይቶባት ነበር።   

የአልጀርያዉ ጦርነት ከተጠናቀቀ ከ 15 ዓመታት በኋላ የተወለዱት የዛሬዉ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ማክሮን በአልጄሪያ ጦርነት የነበረዉን አሳዛኝ ወቅት እና የአልጄሪያ በፈረንሳይ የ 132 ዓመታት የቅኝ ግዛት ዘመንን በተመለከተ፤ ቅሬታዎችን ሊመልሱ፤ የሚነሱ አለመግባባቶችን ሊያለዝቡ ብሎም አስፈላጊዉን መልስ ለመስጠት የመጀመሪያው የፈረንሣይ ፕሬዝዳንት መሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የታሪክ አዋቂዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ በአሁኑ ወቅት፤ ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ ፤በፈረንሳይ የሚኖሩ ፈረንሳዉያን፤ ከአልጀርያ ጋር ከባድ ቁርኝት እንዳላቸዉ ያምናሉ። እነዚህ ዜጎች አልጀርያ ከቅኝ ግዛት ስትላቀቅ አልጀርያን ጥለዉ ወደ ፈረንሳይ የመጡ ዜጎች ሊሆኑ፤ አልያም ከአልጀርያ ተሰደዉ የፈረንሳይ ዜግነትን የጠየቁ ዜጎች ሊሆኑ ይችላሉ።

በቅኝ ገዝቼ ነበር ብላ ከማታዉቀዋ ፈረንሣይ በበኩልዋ፤  አልጀርያን የራሷ ብሔራዊ ግዛት አካል እንደሆነች ነዉ የምታምነዉ የሚሉት የታሪክ ተመራማሪዉ ፈረንሳዊዉ ኤቲን ፍራንሷ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ እንኳ  ፈረንሳይ እና አልጀርያ መግባባት ላይ መድረስ አለባቸዉ ሲሉ ይናገራሉ።

«በአልጄሪያ እና በፈረንሣይ ያለፈው እና አሁን ያለው እርስ በእርስ ግንኙነት በጣም ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ ሁለቱ አገራት ሙሉ በሙሉ የተለዩ እና የተለዩ ናቸው ማለት አይቻልም።» 

ፕሬዚዳንት ማክሮ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር፤  በ 1954 እና በ 1962 መካከል ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን የአልጄሪያን ጦርነት“ትክክለኛ  ዝርዝር እና መረጃ ” እንዲጽፍ ታዋቂውን የታሪክ ጸሐፊ ቤንጃሚን ስቶራን መድበዋል።

ቤንጃሚን ስቶራን እስካሁን ለሰበሰብዋቸዉን የመረጃዎች ክምችት ፕሬዚዳንት ማክሮን ምላሽ ሲሰጡ፤ በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ ወንጀሎች “ምሳሌያዊ ድርጊቶች” ሲሉ በመዝገብ ለመቀበል ቃል ገብተዋል።  ግን ለተፈፀመዉ ድርጊት ይቅርታ ወይም ፀፀት አይኖርም ሲሉ ነዉ ፕሬዝዳንት ማክሮ የተናገሩት። የታሪክ ምሁሩ ቤንጃሚን ስቶራም የይቅርታ ጊዜ ስለመድረሱ ጥርጣሪ አላቸዉ።  እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር  በ 1962 ዓመት የአልጄሪያ አይሁዳዊ የሆኑት እና ወደ ፈረንሳይ የተሰደዱት ቤንጃሚን ስቶራ እንደሚሉት አሁን ገና ታሪክ በመሰብሰቡ ሂደት ጅማሪ ላይ ነን፤ በስራዉ መጨረሻ ላይ ከፈረንሳይ ምላሽ ሊመጣ ይችላል እና ትእግስት አይነት ብጤ ሲሉ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን የፓሪሱን ጭፍጨፋን ለማሰብ የነበረዉ እቅድ ለአስርተ ዓመታት በመንግስት ተስተጓጉሎ የነበረ ቢሆንም ፣ ዛሬ ፈረንሳይ ዉስጥ ጥቅምት 17 ቀንን ለመዘከር ከ 50 በላይ ከተሞች ውስጥ የመታሰቢያ ሐውልቶች ቆመዋል። ከፕሬዚዳንት ማክሮ ቀደም ብለዉ ፈረንሳይን ያስተዳደሩት ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የፓሪሱን ጭፍጨፋ ቢያምኑም፤ መንግስት ሃላፊነት ስለመዉሰዱ ግን ዝምታን መርጠዋል። ፕሬዚዳንቱ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፃፉት ማስታወሻ “ጥቅምት 17 ቀን 1961 ዓ.ም የነፃነት መብታቸውን ፓሪስ ጎዳና ላይ የጠየቁ አልጄሪያዊያን ተገድለዋል። ፈረንሳይ እነዚህን እውነታዎች ትገነዘባለች። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ከ 51ዓመታት በኋላ ዛሬ ለተጎጂዎች መታሰቢያ ይሰራል፤ ይታወሳሉ ”ሲሉ ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ በይፋዊ መግለጫ ላይ ጽፈዉ ነበር። በዚህም ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ  ቀጣዩን እርምጃ ተተኪዉ ትዉልድ እንዲረከብ  ወይም ምላሽ እንዲሰጥ ትተዉለታል።

አዜብ ታደሰ