1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍንዳታው ምርመራ፣ የባለስልጣኑ ደብዳቤ፣ የአብይ ስልጠና

ዓርብ፣ ሰኔ 22 2010

በመስቀል አደባባይ የደረሰው ቦምብ ፍንዳታ እና ምርመራው እንደዚሁም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት ግጭቶች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መወያያ ነበሩ። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለሁለት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ጻፈው የተባለው ደብዳቤ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለጥበብ ሰዎች የሰጡት ስልጠናም እንዲሁ አነጋግሯል።

https://p.dw.com/p/30ZQf
Äthiopien Demonstration Untersützung für Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa
ምስል picture-alliance/Anadolu Agency/M. Wondimu Hailu

የፍንዳታው ምርመራ፣ የባለስልጣኑ ደብዳቤ፣ የአብይ ስልጠና

በኢትዮጵያ በፍጥነት የሚቀያየሩት የፖለቲካ ሁነቶች በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎችን በቀን ውስጥ ለብዙ ጊዜያት ድረገጾችን በተደጋጋሚ እንዲጎበኙ አስገድዷቸዋል። የነገሮች በላይ በላይ መደራረብ ከፍተኛ የተባሉ ጉዳዮች መነጋገሪያነታቸው ቀናትን እንዳይሻገሩ አድርጓል።

ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የደረሰው የቦምብ ፍንዳታ እንኳ በቀጣይ ቀናት በተከሰቱ ዐበይት ክንውኖች ምክንያት ደብዝዞ ተስተውሏል። ባለፉት ሳምንታት እንደነበረው ሁሉ በዚህ ሳምንት የቀጠለው የመንግሥት እና የፓርቲ ሹማምንት ሹም ሽርም በሌሎች ሁነቶች ተሸፍኗል። ለብዙ ዓመታት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያ ነዳጅ የማምረት ጉዳይ ድፍድፍ ነዳጅ በማምረት ተጀመረ መባሉም ከዜና ባለፈ እምብዛም ቀልብ ገዢ አልሆነም።

በሳምንቱ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ሲነጻጸር በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ትኩረት ያገኘው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ለመደገፍ ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ ም በመስቀል አደባባይ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ የደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ነበር። ብዙዎች የማኅበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች ፍንዳታውን አምርረው አውግዘዋል። አደጋው በደረሰበት ቦታ የተነሱ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎችን በመጠቀም ጥቃቱን አደረሱ የተባሉ ወገኖችን ለማጋለጥም የአውጫጪኝ አካሄድ የተጠቀሙም ነበሩ። የፍንዳታው ምርመራ በአሜሪካው የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ. ቢ. አይ) ባለሙያዎች ይታገዛል መባሉም አወዛግቧል። 

Äthiopien Kundgebung Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Explosion
ምስል Oromo Media Network

ዘጸአት ሴቭአድና አናንያ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ «ከFBI መምጣት ጋር ተያይዞ የሀገሪቷ መፃኢ ከመቼው ጊዜ በበለጠ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል» ሲሉ ስጋታቸውን አስነብበዋል።  “CIA እና FBI ባለፉት 50 ዓመታት በኢራቅ ፣ ሊብያ ፣ ሶርያ ፣ የመን እና ሌሎች 70 የሚጠጉ ሃገራት መንግሥታት አፍርሰዋል፣ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሐን እንዲያልቁ ምክንያት ሆነዋል። ባለፉት 50 አመታት በማንም የውጭ ሐይል ቁጥጥር ስር ገብታ የማታውቅ ሀገር ዘንድሮ በግላጭ በአሜሪካ ሞግዚትነት ልትተዳደር ይመስላል። የአሜሪካኖቹ በዚሁ ምርመራ መሳተፍ አራት ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያስገድደናል፦
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን እየተከናወነ ያለው ምርመራ ውጤቱ እርሳቸው እንዲሆን ወደማይመኙት አቅጣጫ እያመራባቸው ይሆን?
- አሜሪካኖቹ የደረሱት ድራማ የማይፈልጉት ውጤት እንዳያመጣባቸው ፈርተው ውጤቱን መቆጣጠር ፈልገው ይሆን? 
- አሜሪካኖቹ አዲሱ የኢትዮጵያ ሞግዚትነታቸው ለወዳጅም ለጠላትም ማሳየት ፈልገው ይሆን? 
- አሜሪካንና የFBI ውጤት መሳርያ/ሽፋን በማድረግ ሊመታ የተወሰነበት አካል ይኖር ይሆን?"
እንደ እውነቱ፥ የFBI የምርመራ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል በጣም ተገማች ነው- ጉዳዩ ከቦምብ ፍንዳታ በላይ ነውና” ሲሉ ጸሀፊው አስተያየታቸውን ደምድመዋል።

በላይነው ኤ. ምትኩ «ገለልተኝነት የሚያስፈልገው ለዳኝነት እንጂ ለምርመራ ሥራ አይደለም» ሲሉ በFBI መርማሪዎች ተሳትፎ ያልተደሰቱ ላሏቸው ወገኖች የሚሆን ምላሽ በፌስ ቡክ ሰጥተዋል። “በመጀመሪያ ነገር አሜሪካ ገለልተኛ አቋም የላትም ለማለት መሠረቱ ምንድን ነው? አሜሪካ በድርጊቱ ተሳትፎ አላት ለማለት ነው? አሜሪካ የምታደላለት አካል አለ ለማለት ነው? ወይስ ምን? በርግጥ እነዚህን ጥያቄዎች መደርደር ለዚህ ጉዳይ ምንም ጥቅም የላቸውም።ሁለተኛውና ዋናው ነገር አንድን የተፈጸመ ድርጊት መመርመር ማለት ድርጊቱ እንዴት እንደተፈጸመ፣ ማን እንደፈጸመው፣ ለምን እንደተፈጸመ፣ ድርጊቱ በምን ሁኔታ እንደተፈጸመ፣ የድርጊቱ ዓላማ፣ ከድርጊቱ ጀርባ እነማን ተሳትፎ እንደነበራቸው፣ ወዘተ ለማጣራት የሚደረግ ሥራ ነው። ይህ ሥራ በዋናነት የፖሊስ ሥራ ሲሆን ፖሊስ ለህዝብና ለመንግሥት ጥቅም የሚሠራው የዘወትር ተግባሩ ነው።

Äthiopien Addis Abeba Reaktionen nach Bombenexplosion
ምስል Reuters/Stringer

ፖሊስ በቦምቡ ፍንዳታ ምርመራ የሚረዱትን አካላት ድጋፍ መጠየቁም የዘወትር ግብሩ መሆኑ እየታወቀ ገለልተኝነቱን መጠየቅ ዓላማው ምን እንደሆነም አይታወቅም። ወይስ የምርመራ ሥራውን እኛ እንሥራው ለማለት ነው? የፖሊስነትን፣ የዐቃቤ ሕግነትን፣ የማረሚያ ቤትንና የዳኝነትን ሥራ አጣምሮ በአንድ እጅ መያዝ የኖርንበት አስከፊ ሥርአት ነበር። ያ ሥርአት አሁን መወገድ አለበት። ይች የአሜሪካ ገለልተኝነት ጉዳይ አሁን የተነሳችው የምርመራው ውጤት ወደ ጠያቂዎቹ ያጋደለ እንደሆነ፣ በኋላ ላይ ʻምርመራው በገለልተኛ አካል አልተደረገምʼ የሚል መከራከሪያ ለመሳብ ነው። ነገር ግን፣ ገለልተኝነት የሚነሳው (መነሳትም ያለበት) በዳኝነት ላይ እንጅ በምርመራ ላይ አይደለም። ምክንያቱም በምርመራ ላይ የሚፈጸሙ ስህተቶች ቢኖሩ እንኳ ገለልተኛ ዳኝነት ካለ የምርመራውን ስህተቶች ሁሉ ውድቅ ማድረግ የሚያስችል ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን ስላለው ነው” ሲሉ ተከራክረዋል።

በዶይቼ ቬለ የፌስ ቡክ አድራሻ እና ድረ ገጽ ትዝብቱን ማካፈል የጀመረው ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ «ኤፍ. ቢ. አይ በመስቀል አደባባይ በፈነዳው ቦምብ የማጣራት ጉዳይ መሳተፉ አግባብ ነውን?» ሲል በፌስ ቡክ ገጹ ላይ የህዝብ ድምጽ መለኪያ አሰባስቦ ነበር። አንድ ሺህ ሰዎች ገደማ በተሳተፉበት በዚህ የድምጽ መለኪያ ዘጠኝ በመቶው ብቻ ናቸው አግባብ አይደለም ሲሉ የመለሱት። 

ከቅዳሜው የመስቀል አደባባይ ሰልፍ ጋር በተያየዘ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጻፈው የተባለው ደብዳቤ ሌላው የሳምንቱ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር። ባለስልጣኑ ኢ. ኤን. ኤን ለተሰኘው የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ የላከው ነው ተብሎ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ሲዘዋወር የነበረው ደብዳቤ የጣቢያው ዋና ሥራ አስኪያጅ  ለቅዳሜው የድጋፍ ሰልፍ የስርጭት ሽፋን ያልሰጡበትን ዝርዝር ምክንያት በመያዝ በመሥሪያ ቤቱ ለውይይት እንዲገኙ ይጠይቃል። ባለስልጣኑ በተመሳሳይ በትግራይ ክልል ስር ላለው የትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጻፈ በተባለው ደብዳቤም ጣቢያው ለምን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንዳልሰጠ ማብራሪያ ጠይቋል። ሁለቱ ደብዳቤዎች ሁለት ጎራ ከፍለው አከራክረዋል። 

አዲስ መኮንን የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ «አንድ ሚዲያ የፈለገውን የመዘገብ ያልፈለገውን ደግሞ ያለመዘገብ መብት አለው» ሲሉ የባለስልጣኑን ደብዳቤ ይዘት ተቃውመዋል። ጸሐፊው አክለውም «ኢ. ኤን. ኤን ሰው ለማፋጀት ሲሽቀዳደም [እንዳልነበር] የቅዳሜውን ሰልፍ ባላየ ማለፉ የሚያስተቸውና የሚያስጠረጥረው ቢሆንም ማብራሪያ ስጥ ተብሎ ግን ሊገደድ አይገባም። ይልቅ ይህንን ደብዳቤ ዶ/ር ዐብይ አህመድ እንዳያዩት። ከእርሳቸው በነፃነት የመኖር መርህ ጋር አይሄድም። ስለ ነፃነት እያወራን እና እየዘመርን ይህንን ልናደርግ አይገባም። እንደ ባለፈው ሕዝብን የሚጎዳ ዘገባ ሲሰራ ብቻ ነው ለማብራሪያ ብሎም ለቅጣት መጠራት ያለበት። ብትችሉ ያንን አጣርታችሁ እርምጃ ውሰዱ።» ሲሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን መክረዋል። እንድርያስ ተካልኝ ሽፈራው በዚያው በፌስ ቡክ ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። ለሁለቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተጻፈውን ደብዳቤ የሚቃወሙት «በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ላይ የተቃጣ» በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻሉ። «እኔ በሚድያ ነፃነት አምናለሁ። ዶ/ር ዐብይም ይህንኑ የሚፈልግ ይመስለኛል። አለበለዛማ «ኢሳትን ማየት ክልክል ነው፣ ዲሽ እናነሳለን» ከሚለው የቀድሞው አካሄድ በምን ተለየ? ስለዚህ ENN እና ትግራይ ቲቪ የመስቀል አደባባዩን ሰልፍ ዘገቡ አልዘገቡ የሚድያ ነፃነት ለማክበር ተዘጋጅቻለሁ ለሚል መንግሥት ምኑም ሊሆን አይገባም። አለበለዚያ የምናየውን ሲወስንልን ከነበረው የቀድሞው የኢህዴግ ስርዓት አዲሱ የኢህአዴግ ስርዓት ምንም ለውጥ የለውም ባይ ነኝ» ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለዋል።

Äthiopien Addis Abeba  Verletzte nach Bombenexplosion
ምስል Ahmed

በከፊል የአቶ እንድርያስን ሀሳብ የሚጋሩት አብዮት ሙላቱ ተከታዩን በፌስ ቡክ ገጻቸው አስፍረዋል «የብሮድካስት ባለስልጣን ሥራ በሕግ አግባብ ፍቃድ መስጠትና በሕግ አግባብ ፍቃድ መሰረዝ እንጂ ሰልፍ ለማስተላለፍ በውል ግዴታ ጥሎባቸው ካልሆነ በቀር ለትግራይ ቲቪ እና ENN የፃፈው ደብዳቤ ተቋሙ ዐብይ አህመድ ላይ አለመደመሩን ከማሳየት የዘለለ ትርጉም የለውም። የታገልነው ለሕግ የበላይነት እንጂ ለባለ ጊዜ ለማጎብደድ አይደለም። ዐብይን ለመደገፍ ከዐብይ መርህ ማፈንገጥ ዐብይን እንደማሰናከል ነው የሚቆጠረው።  ስሜታዊ መሆን ነው ሕጋዊነትን የሚያጠፋው» ብለዋል። 

በመጨረሻ ወደ ምንመለከተው ርዕሰ ጉዳይ ተሻግረናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 20 የኪነጥበብ ባለሙያዎችን በጽህፈት ቤታቸው ባለ አዳራሽ ሰብስበው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኪነጥበብ ሰዎች ጋር የነበራቸው ቆይታ ከጥሪው እና ስያሜው ጀምሮ ትችት አስተናግዷል። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አማካኝነት ለባለሙያዎቹ በተበተነው የጥሪ ደብዳቤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ «ስልጠና ይሰጣሉ» መባሉ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተከታታዮች ተችተውታል። በስብሰባው የተሳተፉ እና እንዳይገኙ የተደረጉ ባለሙያዎች ጉዳይም አነጋግሯል። 

ቱሉ ሊበን ጉዳዩን ነቅፈው ከጻፉት መካከል አንዱ ናቸው። «ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ሰዓት ዋናው የፖለቲካ ቁንጮ ናቸው። ኪነትን በፖለቲካ ዓይን ሊቀርፁ ነው ወይስ ርዕዮተ ዓለም ሊያስተምሩ ነው ስልጠና የሚሰጡት? እንደኔ እንደኔ የኪነት ባለሙያዎች በራሳቸው እይታ፣ በራሳቸው ፈቃድ፣ በራሳቸው መንገድ መመራትና መራመድ አለባቸው። ሲፈልጉ ለፖለቲካው ይወግኑ ሲፈልጉ ፖለቲካውን ይተቹ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ምን አገባቸው? ምርጫው የባለሙያዎቹ ብቻ መሆን አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኪነት ባለሙያዎቹ ግብዣ በሆነ ዝግጅታቸው መገኘት ቢችሉና አነቃቂ ንግግር ቢያደርጉ ችግር የለውም። የኪነጥበብ ባለሙያዎቹን አሰለጥናችኋለሁ ብለው መጥራታቸው ግን ተገቢ አይመስለኝም » ብለዋል።

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Demonstration mit Anhängern
ምስል Reuters

ኒሞና ቦርቶላም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በፌስ ቡክ ገጻቸው አካፍለዋል። «ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ አንድ ሁለት ምራቃቸውን የዋጡ በሳል አማካሪዎች ያሰፈልጓቸዋል። ከፓርቲም ከመንግሥትም ሥራ ገለልተኛ የሆኑ ሰዎች። የአገርና የሕዝብ ፍቅር ያላቸው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርግጥ ነው የስነ-ጽሁፍና የኪነ ጥበብ ፍቅር እንዳላቸው ሰምተናል። ሆኖም ዛሬ የመቶ ሚልዮን ሕዝብ መሪ ናቸው፡፡ ወቅቱም የሽግግር ግዜ ነው ያውም ፈታኝ ወቅት። በዚህ ሰአት አንገብጋቢና አገራዊ ጉዳይ ባለሆነ መልኩ ከኪነት ባለሙያዎች ጋር ያደረጉት ስልጠና ነው ውይይት ምንም አልተዋጠልኝም» ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። 

ተስፋዬ ደጉ ዘጃንሜዳ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሚጠቀሙ ግለሰብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይልቅ «ሹመትና ሱረት ካለበት የማይጠፉ» ያሏቸው የኪነጥበብ ባለሙያዎች ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል። «በአቶ መለስ ዘመን የቤተ መንግሥቱ አጋፋሪ የነበሩ በአቶ ኃይለ ማርያም አገዛዝም ሲያጋፍሩ ኖረዋል ። እየገረመኝ የመጣው ነገር አሁን በዶክተር ዐብይ ጊዜም አጋፋሪነታቸውን ለመቀጠል መዳዳታቸው ነው ። አለማፈራቸው እየገረመኝ እቆዝማለሁ። በዘመነ ዶክተር ዐብይና ከዚያም በኋላ ሁላችንም የምንፈልገው ሹመቱም ሱረቱም ያለ አድሎ ፣ ብቃትን መሰረት ባደረገ መስፈርት ለሁላችንም እንደ እውቀታችንና ችሎታችን እንዲዳረስ ነው ። እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሂደትን የምንፈልገው ለእኩልነት እንጂ ከውስጥና ከልብ ሳይቀየሩ ሹመትና ሱረት የሚያሸቱ፣ እንደ እባብ ቆዳ እየገፈፉ ለሚመጡ የኪነጥበብ አጋፋሪዎች ሰልፍ ማስተካከያ እንዲሆን አይደለም» ሲሉ ጽፈዋል። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ሸዋዬ ለገሠ