1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፋራንሲስ የኮንጎ እና የደቡብ ሱዳን ጉብኝት

ሰኞ፣ ጥር 29 2015

የ86 ዓመቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ይህን ጉዞዋቸዉን ለማድረግ ያቀዱት ከስድስት ወራት በፊት ቢሆንም በአደረባቸዉ የጤና እክል ምክንያት ከእቅዳቸዉ ግማሽ ዓመት ዘግይተዉ ነዉ፤ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ ኪንሻሳ የደረሱት። ወደ አንድ ሚሊዮን ነዋሪ እንደሚገኝባት በሚገመተዉ መዲና የኪንሻሳ፤ ፍራንሲስን ለመቀበል በነቂስ ወጥቶም ነበር።

https://p.dw.com/p/4N5YY
Südsudan Besuch des Papst Franziskus
ምስል Vatican Media/REUTERS

ጉብኝቱ በጦርነት ክፉኛ ለተመሰቃቀሉት ኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን ለመፀለይ ነዉ

የአፍሪቃ ጉብኝታቸዉን ባለፈዉ ማክሰኞ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የጀመሩት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ከሮም ከመነሳታቸዉ በፊት ከርዕሰ-መንበራቸዉ ቫቲካን የወጣዉ መግለጫ እንዳመለከተዉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁለቱን በጦርነትና ግጭት ክፉኛ የተመሰቃቀሉትን ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን እና ደቡብ ሱዳንን የመጎበኙት ለሰላምና ለሕዝብ ደሕንነት ለመጸለይ ነዉ ሲል ገልፆ ነበር። የ86 ዓመቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ይህን ጉዞዋቸዉን ለማድረግ ያቀዱት ከስድስት ወራት በፊት ቢሆንም በአደረባቸዉ የጤና እክል ምክንያት ከእቅዳቸዉ ግማሽ ዓመት ዘግይተዉ ነዉ ባለፈዉ ማክሰኞ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ ኪንሻሳ የደረሱት። ወደ አንድ ሚሊዮን ነዋሪ እንደሚገኝባት በሚገመተዉ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መዲና የኪንሻሳ፤ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን ለመቀበል በነቂስ ወጥቶም ነበር። በርካታ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የኮንጎ ዜጎች ፍራንሲስ መዲና ኪንሻሳ ከመግባታቸው በፊት በመዲናዋ በሚገኘዉ ዓለም አቀፍ የንዶሎ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘት በፓርኮች እና በአደባባዮች ሲዘምሩ እና ሲጨፍሩም ታይቷል። ወደ 105 ሚሊዮን ከሚደርሰው የኮንጎ ሕዝብ ገሚሱ የካቶሎክ እምነት ተከታይ ነዉ።

Vatikan Papst-Reise in die Demokratische Republik Kongo
ፍራንሲስ እና ፊሊክስ ችሴኬዲምስል Arsene MPIANA/AFP

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ጸሎትና ቡራኬ ለመቀበል ከርዕሰ ከተማይቱ ከኪንሻሳ ነዋሪ በተጨማሪ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የኮንጎ ነዋሪ ከያለበት ወደ መዲና ኪንሻሳ ሲጎርፍ ነበር የሰነበተዉ። ለአስርት ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ዉስጥ በምትገኘዉ ኮንጎ መዲና ኪንሻ ዉስጥ ባለፈዉ ረቡዕ ዕለት በተካሄደዉ ሰፊ የፀሎት ሥነ-ስርዓት ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ፣ ሕዝቡ አሳልፈው የሰጡትን ሰዎች ይቅር እንዳለው እንደ እየሱስ ክርስቶስ፣ ልቡን ለይቅርታ ክፍት እንዲያደርግ ተማጽነዋል። ሚሊዮኖችን ከቀያቸው ያፈናቀለውን የምሥራቅ ኮንጎን ግጭት በማስታወስ ይቅር ማለት መጥፎ ነገር እንዳልተፈጸመ ማስመሰል ሳይሆን ይቅር የምንለው ልባችንን ከቁጣ ጸጸት ቂምና ጥላቻ ለማጽዳት ነው ሲሉ ነበር የተናገሩት።  
«በግጭትና በጦርነት ተስፋ በቆረጠው ዓለም ክርስቲያኖች እንደ እየሱስ መሆን አለባቸው። እየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሰላም ለናንተ ይሁን ብሏቸዋል። እኛ ክርስቲያኖች የግጭትን አዙሪት ለመስበር የጥላቻን ሴራ ለመበጣጠስ ከሁሉም ጋር መተባበር እንዳለብን ማመን አለባችሁ።» በኮንጎ የካቶሊክ ቤተክርስትያን የቫቲካን ተወካይ ኤቶር ባሌስትሮ  ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ኮንጎን ለጉብኝት ከማቅናታቸዉ ጥቂት ቀደም ብለዉ እንደተናገሩት ፍራንሲስ ወደ ኮንጎ የሚጓዙት የሰላም መልክትን ይዘዉ ነዉ ብለዉ ነበር። «ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለዓመታት ብዙ ሥቃይ የደረሰባቸውን የኮንጎ ነዋሪዎችን ማጽናናት ይፈልጋሉ ፤ ሃዘናቸዉ እና ስብራታቸዉ እንዲሽርም ይፈልጋሉ። ለፈሰሰውና ለሚፈስሰው ደም አምላክ ይቅር እንዲል ይፈልጋሉ።» 
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በዚሁ ሳምንት ሃሙስ በኪንሻሳ የሰማዕታት ስታዲዮም በተካሄደዉ የፀሎት ሥነ-ስርዓት ላይ ከ65ሺህ በላይ ወጣቶችን አግኝተዉ ስለ ይቅርባይነት ነዉ የተናገሩት። የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ወጣቶች፤ በብሔር መከፋፈልና መጋጨታቸዉን  አቁመዉ የጋራ ሕዝባቸዉንና ሐገራቸዉን እንዲገነቡ ነዉ ፍራንሲስ ወጣቶቹን የመከሩት።  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጎሳ ላይ የተመሰረተ ግጭት እና ሙስና በብዙ የአፍሪቃ ሐገራት ዉስጥ ደም አፋሳሽ ጦርነት፤ ዉዝግብ ማስከተሉን አጽኖት ሰጥተዋልም። የኮንጎ ወጣቶች በጎሳ ወይም በሌላ ምክንያት በተለዩ ወገኖች ላይ ጣትን ከመቀሰር፣ከመጠቋቆምና ከማግለል እንዲታቀቡም አደራ ብለዋል። «እነግራችኋለሁ፣ እሷ ወይም እሱ የተለዩ በመሆናቸዉ ለማግለል በሌሎች ላይ ጣት ለመቀሰር ከመዳዳት ታቀቡ።ከአካባቢያዊነት፣ ከጎሰኝነት ወይም በራሳችሁ ቡድን ዉስጥ ብቻ ስትሆኑ ደሕንነት ከሚሰማችሁ ስሜት መቆጠብን ተገንጠቡ።»
በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዉስጥ ለአስርተ ዓመታት በዘለቀ ፖለቲካ አዘል የጎሳ ግጭት በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ አልቋል። በኮንጎም ሆኑ በሌሎች የበርካታ የአፍሪቃ ሐገራት መንግስታት ባለስልጣናት በሙስና የተተበተቡ መሆናቸዉ በየጊዜዉ መዘገቡ ይታወቃል። የመንግሥታቱ ድርጅት ይፋ ባደረገዉ መግለጫ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክን ጨምሮ የአፍሪቃ ባለስልጣናትና ተባባሪዎቻቸዉ በየዓመቱ 150 ቢሊዮን ዶላር ከደሃ አፍሪቃዉያን ህዝባቸዉ ይዘርፋሉ። ለሦስት ቀናት በኪንሻሳ ጉብኝት አድርገዉ በርካታ የካቶሎክ ምዕመናንን ያገኙት የሮማዉ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ፤ የኮንጎ ወጣቶች ሙስናን እንዲርቁ ብሎም እንዲያወግዙ ጠይቀዋል። «በሙስና የተዘፈቁ ሰዎች፣ ቅን ናቸዉ ወይስ አይደሉም? ጥያቄ ነዉ፣ ቅን ናቸዉ ወይስ አይደሉም? ሙስና መኖር የለበትም።እስኪ ሁላችሁም በሉ!!! ሙስና ይጥፋ!!!»
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በኮንጎ የሚያደርጉትን ጉብኝት ዛሬ አጠናቅቀዉ ነገ ወደ ደቡብ ሱዳን ይጓዛሉ።አንድ የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን ሲጎበኝ ከ38 ዓመት ወዲሕ ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ።
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግጭት ጦርነት በምትናጠዉ እና የተፈጥሮ ኃብት በታደለችዉ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መጎብኘታቸዉ አብዛኛዉን የሃገሪቱን ዜጋ አስደስቷል፤ ብዙዎችንም በሃገሪቱ ሰላም ያሰፍናል የሚል ተስፋን አሰንቋል። በኪንሻሳ ኤድዋርድ ኢሶንግ የተባሉ የአንድ የካቶሊክ ቤተክርስትያን አባት ይህሄዉ ተስፋ እንዳላቸዉ ተናግረዋል። 
« ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሕዝቡን አንድ ያደርጋሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ። እንደምታውቀው በአሁኑ ጊዜ መላው ዓለም በኮንጎ ምን እየተከናወነ እንዳለ እየተመለከተ ነው ። በምሥራቅ ኮንጎ እየሆነ ስላለዉ ነገር  እየተናገሩ ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እዚህ መገኘታቸው ሰዎች በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ምን እየተከናወነ እንዳለ እንዲገነዘቡ እና ይህም ለሰላም መነሻ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ።»
ትናንት አርብ ከሰዓት በኋላ የኮንጎ ጉብኝታቸዉን አጠናቀዉ ደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ የገቡት ፋራንሲስ ከሮም አንድ የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ደቡብ ሱዳንን ሲጎበኝ  የመጀመሪያዉ ናቸዉ።  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በዋና ከተማዋ ከመድረሳቸዉ ከቀናት ጀምሮ የጁባ ከተማ ምክር ቤት ባለስልጣን የጽዳት ሰራተኞች ጎዳናዎችን ሲጠርጉ ፤ መነሃርያ እና አደባባዮች የእንኳን ደህና መጡ ባነሮችን ብሎም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱን በርካታ ፎቶዎችን ሲሰቅሉ ሲያሳምሩ ነዉ የሰነበቱት። ፍራንሲስ በጁባ የሦስት ቀናት ጉብኝታቸዉ ወቅት በመዲናዋ የሚገኙ የሌሊት መዝናኛዎች በሙሉ እንዲዘጉ መንግስት ትዕዛዝ አስተላልፏል።  የደቡብ ሱዳን ኮሚኒኬሽን ሚንስትር ማይክል ማኩኢ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ጉብኝት ደቡብ ሱዳንን ወደ አዲስ የሰላም ጉዳና የሚያራምዳት ነዉ ሲሉ ታሪካዊነቱን ገልፀዋል።   
«ይህ የሰላምና የጥሩ መንፈስ ተልዕኮ ነው። ይህ የማስታረቅ እና የመፈወስ ተልዕኮ ነው። ይህ ተልእኮ የይቅር ባይነት ነዉ። ስለዚህም  ደቡብ ሱዳን በሠላምና በጥሩ መንፈስ እንደምትዘልቅ ብሎም እኛ በዚህ ተመርቀን  ተጠቃሚ እንደምንሆን ተስፋ እናደርጋለን።» በደቡብ ሱዳን የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች በጋራ በሚያደርጊት ጥሪ የሱዳን ፖለቲከኞች ልዩነቶቻቸዉን ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው ለህዝቡ ጥቅም እንዲሰሩ የጋራ ጥሪ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የደቡብ ሱዳኖቹ ሁለት ተፋላሚ መሪዎች ማለትም ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን እና ምክትላቸው ሪየክ ማቻርን በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ 2019 ቫቲካን ዉስጥ ሲያስተናግዱ በገቡት ቃል መሰረት ወደ ደቡብ ሱዳን ለጉብኝት መምጣታቸዉ ይታወቃል። 

Pope Francis visits South Sudan
ፍራንሲስ እና ሳልቫኪርምስል Vatican Media/REUTERS
Südsudan Besuch des Papst Franziskus
ፍራንሲስ በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ ምስል Vatican Media/REUTERS
DR Kongo | Papst Franziskus in Kinshasa
የሮማዉ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በኮንጎ ምስል Arsene Mpiana/AFP/Getty Images
DR Kongo | Papst Franziskus in Kinshasa
የኪንሻሳ ህዝብ ከፍራንሲስ ጋር ፀሎትምስል Moses Sawasawa/AP Photo/picture alliance

አዜብ ታደሰ 


ማንተጋፍቶት ስለሺ