1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀረ-ዘረኝነት ተቃዉሞና የጆርጅ ፍሎይድ የሐዝን ሥነ ስርዓት

ዓርብ፣ ግንቦት 28 2012

ታዋቂዉ የሰብዓዊ መብቶች አቀንቃኝ ኧል ሻርፕቶን አሜሪካ ዉስጥ በፖሊሶች በግፍ በተገደለዉ ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፎሎይድ ሃዘን ሥነ-ስዓት ላይ ተገኝቶ ዘረንነት በመቃወም ሰልፍ እንዲደረግ ጥሪ አቀርበ ። ሚኒያፖሊስ ዉስጥ በተካሄደዉ የሃዘን ሥነ-ስርዓት ላይ የሟች ቤተሰብና  ጓደኞች ታዋቂ ፖለቲከኞች እና የማኅበረሰብ ዓባላት ተገኝተዋል።

https://p.dw.com/p/3dKAJ
USA Protest nach dem Tod von George Floyd | Al Sharpton
ምስል picture-alliance/dpa/C. Gonzalez

ታዋቂዉ ጥቁር አሜሪካዊ የሰብዓዊ መብቶች አቀንቃኝ ኧል ሻርፕቶን ከሳምንት በፊት አሜሪካ ዉስጥ በፖሊሶች በግፍ በተገደለዉ ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፎሎይድ ሃዘን ሥነ-ስዓት ላይ ተገኝቶ ዘረንነት በመቃወም ሰልፍ እንዲደረግ ጥሪ አቀርበ ። ሚኒያፖሊስ  ኖርዝ ሴንትራል ዩንቨርስቲ አዳራሽ ዉስጥ በተካሄደዉ የሃዘን ሥነ-ስርዓት ላይ የሟች ቤተሰብና  ጓደኞች ታዋቂ ፖለቲከኞች እና የማኅበረሰብ ዓባላት ተገኝተዋል። በአዳራሹ በወርቅማ ሳጥን የሟች አስክሬን እንደነበረም ከቦታዉ የደረሰዉ ዘገባ ያሳያል። የሟች ቤተሰብ ጠበቃ የሆኑት የ 46 ዓመቱ ቤን ክራምፕ፤  ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ በግፍ ተገደለ እንጂ በኮሮና ታሞ አልሞተም ብለዋል። ታዋቂዉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኧል ሻርፕቶን በበኩላቸዉ የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በዩናይትድ ስቴትስ ለዘመናት የዘለቀዉን ዘረኝነት እና የጥቁር ጭቆናን የሚያሳይ ነዉ ብለዋል። ነጮች ሁሌም ቢሆን በጉልበታቸዉ አንገታችን ላይ እንደቆሙ ነዉ ። አሁን ከጆርጅ ፍሎይድ ሞት በኃላ በጋራ ተነስተን ጉልበታችሁን ከአንገታችን ላይ አንሱ የምንልበት ጊዜ ነዉ ሲሉ ዘረኝነትን መታገል አለብን ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኧል ሻርፕቶን በዚሁ ሃዘን ሥነ-ስርዓት ላይ በጎርጎረሳዉያኑ 1963 ነሐሴ 28 ፤ ታዋቂዉ የአሜሪካ የጥቁሮች መብት ተሟጋች ዶክተር ማርቲን ሉተርኪንግ ጥቁሮች ከነጮች እኩል ነፃነት እና ስራ የማግኘት መብት አለባቸዉ ሲል ዋሽንግተን ላይ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ባደረገበት ዓመታዊ እለት ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ጥሪ አድርገዋል። ማርቲን ሉተርኪንግ በጎርጎረሳዉያኑ 1963 ነሐሴ 28 «I Have a Dream» ህልም አለኝ ሲል 250 ሺህ ሕዝብ በወጣበት የአደባባይ ሰልፍ ላይ ታሪካዊ ንግግር ማድረጉ የሚታወስ ነዉ። ሚኒያፖሊስ ዉስጥ ለሟቹ ጆርጅ ፍሎይድ በተካሄደዉ የሃዘን ሥነ ስርዓት ላይ ሃዘንተኞች የስምንት ደቂቃ 46 ሰከንድ የሕሊና ፀሎት ማድረጋቸዉም ተያይዞ ተዘግቦአል።

Gendenkfeier für George Floyd
ምስል Getty Images/AFP/K. Yucel

 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ