1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጦርነት ጉሰማ፤ የጄኔራሉ መታፈንና የፍራንክፉርት ድል

ዓርብ፣ ግንቦት 12 2014

በሰሜን ኢትዮጵያ ያንዣበበው የጦርነት ሥጋታ፤ የአማራ ክልል የልዩ ኃይል የቀድሞው ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ ታፍኖ መሰወር እና መታሰር፤ እንዲሁም የአይንትራኅት ፍራንክፉርት የአውሮጳ ሊግ የዋንጫ ድልን በተመለከተ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

https://p.dw.com/p/4BauB
Äthiopien Tigray-Krise | Armee
ምስል Ben Curtis/AP/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት አስተያየት

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፦ የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል። ሚሊዮኖችን ከቀዬ መንደራቸው አፈናቅሎ ለስደት ዳርጓል።  ብዙዎችን ለአካል እና የስነ ልቦና ጉዳት አጋልጧል። ጦርነቱ ፋታ ወስዶ፤ ጊዜ ሰጥቶ ግን በለየለት መልኩ ዳግም ሊያገረሽ ነው የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ አጭሯል። በርካቶች በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ስጋታቸውን እየገለጡ ነው። የአማራ ክልል የልዩ ኃይል የቀድሞው ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ አዲስ አበባ ውስጥ ከቤታቸው እንደወጡ ታፍነው ከተሰወሩ በኋላ ባህር ዳር እስር ቤት እንደሚገኙ ባለቤታቸው እና ጠበቃቸው ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። የጀርመኑ «አይንትራኅት ፍራንክፉርት» የእግር ኳስ ቡድን ከ42 ዓመታት በኋላ የአውሮጳ ሊግ ዋንጫን ሐሙስ ማታ ሴቪያ ውስጥ በእጁ አስገብቷል። በዚህም ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያንዣበበው የጦርነት ሥጋታ

ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው፤ ሚሊዮኖችንን ያፈናቀለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳግም ሊከሰት ነው ሲሉ ብዙዎች ስጋታቸውን እየገለጡ ነው። ከተፋላሚ ኃይላት በኩል የሚሰነዘሩ የቃላት ውርወራዎች እና ዛቻዎች ይህንኑ ያመላክታሉ። ከሕወሓትም፣ ከኤርትራም፤ ከአማራ ክልልም ሆነ ከፌዴራል መንግስት በኩል የሚሰሙት የጦርነት ጉሰማዎች እና ዝግጅቶችን በመጥቀስ ጦርነት ዳግም ሊነሳ እንደሚችል አመላካች ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

«ጦርነት ይብቃ» በሚል የፌስቡክ ስም ተጠቃሚ፦ «የሁሉም መብት ይከበር። ሁሉም ግዴታውን ይወጣ» ይላሉ። «ጦርነት ለማሸነፍ ብቻ፤ ለመምት ሳይሆን፤ ለመግደል ብቻ ቢሆን እንኳን አንገሽግሾናል» ሲሉም የጦርነትን አስከፊነት አጉልተው ይገልጣሉ። «የትግራይ ክልል ሕዝብ ወያኔን መቃወም አለበት። የሌላው ክልል ህዝብ ደግሞ የፌዴራል መንግስትን መቃወም አለበት። የሕዝባችን ሕይወት የእነሱ የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ኪኒን አይደለም» በማለት ጽሑፋቸውን አሳርገዋል።

Äthiopien | Bürgerkrieg | Tigray | Universität in Dessie
ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

ሰዒድ መሐመድ ደግሞ በፌስቡክ ጽሑፋቸው፦ «ፈጣሪ ልቦና ይስጣቸው» ይላሉ የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚዎጡን። ይቀጥላሉ፦ «ዳግም እልቂት ዳግም መፍናቀል። ብቻ ያማል። ምን አለ ለሠላም ቢሮጡ ለጦርነት ከመሮጥ» ሲሉም ይጠይቃሉ።

«ኢትዮጵያ ከመቼዉም ጊዜ በአሁኑ ሰአት ሰው ያስፈልጋታል ያውም የእውነት ሰው» ያሉት ደግሞ ደጀኔ ከበደ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው። ይቀጥላሉ። «ይህን የመከራ ጊዜ ተጠቅሞ ታላቅነቱን የሚያስመሰክር፤ አገሪቷንም ከአስከፊ ጦርነት የሚታደግ፤ ኢኮኖሚውን ከውድቀት፤ ህፃናትን ከእልቂት የሚታደግ ሰው፣ ሰው፣ ሰው፣ ሰው...» ሲሉም ድምፃቸውን ያስተጋባሉ።

«አላሙዲን» በሚል ስም ሌላኛው የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ፦ «ከዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ በኋላም ስለ ጦርነት የሚያወሩ ጦርነትን የሚሰብኩ ሰዎችን ማየት እጅግ ይቀፋል» ብለዋል። ምንም ማድረግ ባይችሉም አምላካቸውን ግን ተማጽነዋል፦ «አላህ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን» ሲሉ።

የብርጋዴር ጄኔራሉ መታፈን እና መታሰር

በኢትዮጵያ በተለይም በዋና ከተማዪቱ አዲስ አበባ በብዛት ደግሞ አማራ ክልል ውስጥ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑ እየተነገረ ነው። የገቡበት ሳይታወቅ ለቀናት የሚሰወሩ ታዋቂ ሰዎች እና ተቺዎች ቁጥር እየተበራከተ መሆኑ ያሳስበናል የሚሉ ድምፆች ተበራክተዋል። በዚሁ ሳምንት ከቤታቸው እንደወጡ ታፍነው ደብዛቸው ለቀናት ሳይታወቅ በመቆየታቸው ከእየ አቅጣጫው የቁጣ ድምፆች እንዲስተጋቡ ያደረገው የብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ እስር ይጠቀሳል።

Äthiopien Addis Abeba |  Tefera Mamo
ምስል Solomon Muchie/DW

የአማራ ክልል የልዩ ኃይል የቀድሞው ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ ደብዛቸው ከጠፋ ከሁለት ቀናት በኋላ አማራ ክልል፤ ባህር ዳር ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንደሚገኙ መልእክት እንደደረሳቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ መነን ኃይሌ ሐሙስ እለት ለዶቼቬለ አረጋግጠዋል።

«ጦርነቱ ሲጀመር ድረስልን ብለው ይለቁታል» ሲሉ የተሳለቁት አቤ ማኛ በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ አችር አስተያየት ነው። «ፈጣሪ ካተ ጋር ይሁን» ይህ ደግሞ አብርሃም ጌትነት በፌስቡክ ገጻቸው ያኖሩት ምኞት ነው።  ሙሉጌታ ዘውዱ በበኩላቸው፦ «እውነትን ፊት ለፊት እሚናገር ጀግናን በማሰር በማሳደድ አገር እንደ አገር አይቀጥልም» ይሉና ጽሑፋቸውን ይቀጥላሉ። ስድቡን ቆርጠነዋል። «ሰከን በሉ» ሲሉ ጽሑፋቸውን አሳርገዋል።

የኔነሽ ንጉሤ በፌስቡክ ያሰፈሩት ጥያቄ እንዲህ ይነበባል፦ «ለእውነት መቆም ወይም ደግሞ ሰው ሆኖ መገኘት ምላሹ ግን ይሄ ነው?»  በጥያቄ ይሰናበታሉ። «ፍቅር አያረጅም» የፌስቡክ መጠሪያ ስም ነው። በዚህ መጠሪያ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል።  «አይገርምም ከሠው የሚደበቅ የለም»። ይህ መልእክት የተጻፈው የጄኔራሉ መሰወርን ባለቤታቸው ለዶይቸ ቬለ ከተናገሩ በኋላ አመሻሹ ላይ ደግሞ ባህርዳር እስር ላይ መገኘታቸውን ካሳወቁ በኋላ ነው።

ዶ/ር ሰናይት የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ስለ እስሩ ዝርዝር ጽሑፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አስፍረዋል። እንዲህ የሚል ይገኝበታል። «የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን የሚያደርገው ከሕወሓት ጋር ሲሸልስ እና ናይሮቢ ውስጥ በጥልቀት ከተደራደረ በኋላ መሆኑ የሚጠበቅ ነው» ሲሉ ግምታቸውን ሰንዝረዋል። አክለውም፦ «በአሁኑ ወቅት በሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍል ዘንድ ተከታታይ እስሮች፣ ጠለፋዎች እና ግድያዎች ወዘተረፈ አሉ» ሲሉ ጽፈዋል። ዶ/ር ሰናይት ስላሉት የሲሸልስ እና የናይሮቢ ድርድር ፌዴራል መንግስትም ሆነ ሕወሓት በቀጥታ ያሉት ነገር ባይኖርም፤ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ረቡዕ እለት ቀጣዩን በጋዜጣዊ መግለጫው ተናግረዋል።

Äthiopien Präsident der Amhara-Region Yilkal Kefale
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

«ብዙ የሚፈለጉ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ሲሆን፤ የእነሱ ጉዳይም እየተጣራ በአብዛኛው በውይይት፤ በንግግር እንዲፈታ እና ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ ጥረት ይደረጋል። ከፍተኛ ወንጀል የሠሩ ደግሞ ተጣርቶ በፍርድ ቤት ቀርቦ ፍርድ በሚሰጣቸው መሰረት የሚፈጸም ይሆናል። አንዳንድ የማይመለከታቸው ሰዎች ተይዘው ከሆነ በእየ ደረጃው ያለው መርማሪ አካል በአግባቡ እና በፍጥነት አጣርቶ፤ ፈጣን ርምጃ በመውሰድ እንዲለቃቸው፤ የተያዙት ሰዎችም በአግባቡ እና በስርዓት ተይዘው ተገቢው መብታቸው እንዲከበር ይደረጋል።» ሐቢባ ያሲን የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚም በእንግሊዝኛ የጄኔራሉ መታሰር ሊያስከትል ይችላል ያሉትን መዘዝ ጠቅሰው ጽፈዋል። «ሁሉም አማራ የእኔ ነው ያሉት የመጀመሪያ ሰው ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ናቸው። ይህን ሰው መንካት ዋጋ እንደሚያስከፍል ማሳየት ያስፈልገናል። ጄኔራሉ ቀይ መስመራችን መሆናቸውን ለመንግሥት ማሳየት ከተሳነን፤ ተተኪዎቻችን በሕዝባቸው ዘንድ ብዙም የማይታመኑ ያደርጋል» ብለዋል። ደሴ ምስጋናው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ፍቱ» ሲሉ መልእክታቸውን በአጭሩ አስፍረዋል።

የአይንትራኅት ፍራንክፉርት የአውሮጳ ሊግ የዋንጫ ድል

የጀርመኑ አይንትራህት ፍራንክፉርት እግር ኳስ ቡድን ከ42 ዓመታት ቆይታ በኋላ የአውሮጳ ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። ፍራንክፉርት ረቡዕ ዕለት ማታ ከስኮትላንዱ ግላስኮው ሬንጀርስ ቡድን ጋር ስፔን ሴቪያ ከተማ ውስጥ ያደረገው የዋንጫ ግጥሚያ በመደበኛ ሰአቱም ሆነ በተራዘመው የጨዋታ ጊዜ እንድ እኩል ነበር የተጠናቀቀው።

Europa League Finale | Eintracht Frankfurt - Glasgow Rangers
ምስል HMB-Media/IMAGO

በመለያ ምቱ ግን ሬንጀርስ አንድ ስተው፤ አይንትራኅት ፍራንክፉርቶች ሁሉንም አግብተው 5 ለ4 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። ውጤቱ መላ ጀርመንን እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአይንትራኅት ፍራንክፉርት ደጋፊዎችን አስቦርቋል። የአይንትራኅት ፍራንክፉርት ቡድን ይፋዊ የትዊተር ገጹ ስያሜን፦ «የአውሮጳ ሊግ የ2022 ሻምፒዮን» በሚል ቀይሯል። ቡድኑ እዛው ትዊተር ላይ፦ «ድንገት ካልሰማችሁ፤ በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመን በሻምፒዮንስ ሊግ ውስጥ እንጫወታለን» ሲልም ጽፏል።

አይንትራኅት ፍራንክፉት የአውሮጳ ሊግ የዘንድሮ የዋንጫ ባለድል በመሆኑ ከግማሽ ምእተ ዓመት ርቆ ቢቆይም ዳግም በሻምፒዮንስ ሊግ በቀጥታ ተሳታፊ መሆን ይችላል። «42 ዓመታት የአውሮጳ ሊግ ዋንጫ ጥበቃ አክትሟል» ኤጅስፕረስ ስፖርት በትዊተር ገጹ ያሰፈረው ነው።

Europa League Finale | Eintracht Frankfurt - Glasgow Rangers | Verletzung Sebastian Rode
ምስል Pierre-Philippe Marcou/AFP/Getty Images

በረቡዕ ጨዋታ ግንባሩ ላይ በታኬታ ተረግጦ የተተረተረው ሰባስቲያን ሩደ የተሰፋ ግንባሩን ወደፊት አድርጎ የሐኪም ቤት አልጋ ላይ ተኝቶ የሚታይበትን ፎቶውን ሐሙስ ዕለት ትዊተር ላይ አስፍሯል። የአይንትራኅት ፍራንክፉርት አማካዩ ሰባስቲያን ሩደ በጀርመንኛ ያሰፈረው ጽሑፉ፦ «ዋናው ጉዳይ ያ ነገር መጥቷል» ሲል ይነበባል። ዋንጫውን ማለቱ ነው። «ሌላው ነገር በአጠቃላይ የራሱ ጉዳይ!»  ይሄ ደግሞ በጉዳት የተሰፋ ግንባሩን ለማጣቀስ ነው። ለዘመናት ሲጠበቅ ለቆየ በስንት ትግል ለተገኘ ዋንጫ የተከፈለ መስዋዕነት። መስዋዕትነቱ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን ከ66 ዓመት በኋላ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ መልሶታል። «ዋናው ጉዳይ ያ ነገር መጥቷል፤ ሌላው ነገር በአጠቃላይ የራሱ ጉዳይ!»  ለዛሬ በዚሁ አበቃን!

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ