1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 30 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 30 2013

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከኒጀር አቻው ጋር ለአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያ ወደ ኒያሚ ዛሬ ጠዋት ማቅናቱ ተዘግቧል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ትናንት ሊቨርፑልን በደረጃ ሰንጠረዡ ቀዳሚ ከመኾን አግቶታል።

https://p.dw.com/p/3l4ZO
Bundesliga I Borussia Dortmund v Bayern München
ምስል Leon Kuegeler/Pool/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከኒጀር አቻው ጋር ለአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያ ወደ ኒያሚ ዛሬ ጠዋት ማቅናቱ ተዘግቧል። ከ5:00 ሰዓት በረራ በኋላም በኒጀር ኒያሚ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም መድረሱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረ ገጹ ማምሻውን ዐሳውቋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ትናንት ሊቨርፑልን በደረጃ ሰንጠረዡ ቀዳሚ ከመኾን አግቶታል። አርሰናል በአስቶን ቪላ የ3 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ቸልሲ በግብ ሲንበሸበሽ፤ ላይስተር ሲቲ ለመሪነት ያበቃችውን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ዋነኛ ተቀናቃኙ ቦሩስያ ዶርትሙንድን ድል ያደረገው ባየር ሙይንሽን በደረጃ ሰንጠረዡ የመሪነቱን ስፍራ አስጠብቋል። በዚሁ ወሳኝ ጨዋታ ጉዳት የደረሰበት ዮሱዋ ኪሚሽ ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት አይሰለፍም። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከነገ በስተያ የወዳጅነት ከዚያም የኔሽን ሊግ ግጥሚያዎችን በተከታታይ ያከናውናል።

ዐርብ ማታ ከሱዳን አቻው ጋር አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ በተካሄደው ጨዋታ 2 ለ 2 የተለያየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የፊታችን ዐርብ ከኒጀር ጋር ይጋጠማል። ቀደም ሲል ብሔራዊ ቡድኑ ሀገር ውስጥ ባደረጋቸው ተከታታይት የወዳጅነት ግጥሚያ በዛምቢያ 3 ለ2 እና 3 ለ1 ተሸንፎ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከኒጀር ቡድን ጋር ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያውን ዐርብ ዕለት በኒያሚ ከተማ ጄኔራል ሴይኒ ኩንትቼ ስታዲየም ያከናውናል። የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ግጥሚያ ማክሰኞ ዕለት በባህር ዳር ስታዲየም ተብሏል።   

Äthiopien Nationalteam EFF Freundschaftsspiel
ምስል Omna Tadele/ DW

ብሔራዊ ቡድኑ ከኒጀር አቻው ጋር ለሚኖረው የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ በዛሬው እለት ጥቅምት 30 ቀን፤ 2013 ዓ.ም ጠዋት ወደ ኒጀር አቅንቷል።   የኒጀር ቡድን አሰልጣኝ ዦን ሚሼል ካቫሊ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለሚኖረው ግጥሚያ በደንብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። የኒጀር ሁለት ተጨዋቾች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ለማወቅ ተችሏል። አሰልጣኙ ቡድናቸው «የመፎካከር አቅም» እንዳለው ጠቊመዋል። ኒጀር በምድቡ በማዳጋስካር እና አይቮሪ ኮስት በመሸነፏ በዜሮ ነጥብ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የማለፍ ዕድሏን ከፍ ለማድረግ በኒያሚውም ኾነ በባህርዳሩ ግጥሚያ ማሸነፍ ይጠበቅባታል። በአንፃሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 3 ነጥብ ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ምድቡን ማዳጋስካር በ6 ነጥብ ትመራለች። በምድቡ ከኢትዮጵያ እና ከኒጀር በተጨማሪ ማዳጋስካር እና አይቮሪ ኮስት ቡድኖችም ይገኙበታል።

ከአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያ ወደ አውሮጳ እግር ኳስ ስንመለስ ደግሞ፦ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ግጥሚያውን ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር ከነገ በስትያ ያከናውናል። የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ኃላፊ የቀድሞው የብሔራዊ ቡድኑ ግብ አዳኝ ዖሊቨር ቢርሆፍ፦ ዛሬ ከላይፕሲሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ብሔራዊ ቡድኑ የቀድሞው ገናናነቱ ባለመመለሱ በእጅ አዙር ቅሬታውን ገልጧል። «ደጋፊዎቻችንን በዓለም ዋንጫ መመለስ አለብን» ያለው ዖሊቨር ቢርሆፍ ያን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ፦ «በመፈክር ሳይኾን» በትጋት መኾኑን አክሏል።  ብሔራዊ ቡድኑ ለአውሮጳ ሊግ አምስተኛ እና ስድስተኛ ዙር ውድድር ደግሞ ቅዳሜ ዕለት ከዩክሬን ጋር እንዲሁም የነገ ሳምንት ከስፔን ጋር ይጫወታል። 

ቡንደስሊጋ

ባየር ሙይንሽን ቦሩስያ ዶርትሙንድን 3 ለ2 ባሻነፉበት ወሳኝ ግጥሚያ ጉልበቱ ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰበት አማካዩ ዮሱዋ ኪሚሽ ከጉዳቱ ለማገገም እስከ ጥር አጋማሽ ድረስ ጊዜ እንደሚወስድበት ተገለጠ። የባየር ሙይንሽኑ አማካይ ጉልበቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት በቦሩስያ ዶርትሙንዱ አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ ነው። ዮሱዋ ኪሚሽ በጉዳት የተጎዳ የቀኝ ጉልበቱን ቀዶ ጥገና ተደርጓል።  እስካሁን ከተከናወኑ 34 ግጥሚያዎች 33ቱን በድል ላጠናቀቀው የአሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ቡድን ባየር ሙይንሽን የዮሱዋ መጎዳት ደስታውን ሙሉ ለሙሉ እንዳያጣጥም አድርጎታል። ባየር ሙይንሽን የደረጃ ሰንጠረዡን በ18 ነጥብ ይመራል። ቅዳሜ ዕለት በነበረው ሌላኛው ግጥሚያ ፍራይቡርግን 3 ለ0 ድል ያደረገው ላይፕሲሽ 16 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ15 ነጥብ ሦስተኛ ነው። ተመሳሳይ ነጥብ ያለው ባየር ሌቨርኩሰን በግብ ክፍያ ተበልጦ አራተኛ ደረጃን ይዟል። ትናንት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 4 ለ3 ያሸነፈው ባየር ሌቨርኩሰን አሰልጣኝ ፔተር ቦሽ ቡድናቸው ማሸነፉ ተገቢ መኾኑን ተናግረዋል።

Bundesliga - Bayer Leverkusen v Borussia Moenchengladbach
ምስል Martin Meissner/REUTERS

«እንደሚመስለኝ ከመጀመሪያው አንስቶ ወደፊት ገፋ አድርገን በመከላከል ነው የተጫወትነው። በዚያም ጫና ማሳደር ችለናል። ከምንም በላይ ግን ኳስን በቁጥጥር ስር በማዋል ጥሩ ተጫውተናል።»

በትናንቱ ሌላኛው ግጥሚያ የሆፈንሃይሙ አዲሱ አሰልጣኝ ሰባስቲያን ሆይኔትስ አልቀናቸውም።  ቡድናቸው በቮልፍስቡርግ 2 ለ 1 ተሸንፏል። ሆፈንሃይም 7 ነጥብ ይዞ ደረጃው 13ኛ ነው። ቮልፍስቡርግ በ11 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቀዳሚዋን ግብ ጨዋታው በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው የቮልፍስቡርጉ አማካይ ሬናቶ ሽቴፋን ደስታውን እንዲህ ነበር የገለጠው፦

«ልዩ ስሜት ነበር ለእኔ። በዚያ ላይ ጨዋታውን የተቆጣጠርነው ይመስለኛል። በእርግጥ በኹለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው አልነበርንም። ሰዎቹ የተሻለ እንዲጫወቱ ለቀቅ አድርገናቸዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ፈዘዝ ያልን ይመስለኛል። ስለዚህ ለእኔ ከጨዋታው በኋላ ልዩ ስሜት ነው የተሰማኝ።  እንደው ሰአቱ እንደምንም ባለቀ እያልኩ ስመኝም ነበር።»

ከታችኛው ዲቪዚዮን ዘንድሮ ያደገው አርሜኒያ ቢሌፌልድን 5 ለ0 ያንኮታኮተው ዑኒዮን ቤርሊን በ12 ነጥብ ወደ አምስተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። ባለፈው ሳምንት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ነበር። አርሜኒያ ቢሌፌልድ ወራጅ ቃጣና ግርጌው 15ኛ ላይ ነው የሚገኘው። 3 ነጥብ ብቻ ያለው ኮሎኝ 16ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ሻልከ በተመሳሳይ 3 ነጥብ 17ኛ፤ እንዲሁም ማይንትስ በ1 ነጥብ ብቻ የመጨረሻ 18 ደረጃ ላይ ተደርድረዋል።  

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ላይስተር ሲቲ ትናንት ዎልቨርሀምፕተንን 1 ለ0 አሸንፎ የመሪነቱን ስፍራ በ18 ነጥብ አስጠብቋል። ዌስትብሮሚችን 1 ለ0 ያሸነፈው ቶትንሃም በበኩሉ 17 ነጥብ ይዞ ኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተመሳሳይ 17 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ የሚበለጠው ሊቨርፑል ትናንት ባደረገው ግጥሚያ በደረጃው የመሪነት ስፍራውን የመረከብ ዕድል አምልጦታል። ማንቸስተር ሲቲ 12 ነጥብ አለው፤ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

UK Timo Werner Jubel | Chelsea gegen Souththampton
ምስል Matthew Childs/AFP/Getty Images

በማንቸስተር ሲቲ ኤቲሃድ ስታዲየም የተጋጠመው ሊቨርፑል በተጋጣሚው የተበለጠ ቢሆንም አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል። የተከላካይ ስህተት ጋብሪዬል ጄሱስ 31ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ ጎል እንዲያስቆጥር አስችሎታል። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በተለይ እስከ 20ና ደቂቃ ድረስ በብርቱ ሲያጠቃ የነበረው ሊቨርፑል በ13ኛው ደቂቃ ላይ ነበር በሞሀመድ ሳላህ ግብ ማስቆጠር የቻለው። በዕለቱ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ሴኔጋላዊው አጥቂ ሣዲዮ ማኔ ላይ ካይ ዎከር ባደረሰው ጥፋት ነበር ፍጹም ቅጣት ምቱ የተሰጠው።

39ኛው ደቂቃ ላይ ደብረወይና ወደግብ የላካትን ኳስ ተከላካዩ ጎሜዝ በእጁ በመንካቱ ለማንቸስተር ሲቲ ፍጹም ቅጣት ምት ተሰጥቶ ነበር። በቪዲዮ ርዳታ ታግዘው የመሀል ዳኛው ፍጹም ቅጣት ምት ቢሰጡም፤ ደብረወይና ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከርን በሌላ አቅጣጫ እንዲወረወር ቢያደርገውም ኳሷን ግን ወደ ውጭ ልኳታል። በእርግጥ የፍጹም ቅጣት ምቱ ተገቢነት አጠያያቂ ነበር፤ ምክንያቱም ጎሜዝ ኳሷን ላለመንካት እጁን ለማራቅ ሲጣጣር ታይቷልና።

ትናንት በአስቶን ቪላ 3 ለ 0 የተሸነፈው አርሰናል 12 ነጥብ ይዞ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቅዳሜ ዕለት ኤቨርተንንን 3 ለ 1 ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ በ10 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቸልሲ ሼፊልድ ዩናይትድን 4 ለ1 ድል አድርጎ ነጥቡን 15 በማድረስ 5ኛ ላይ ይገኛል። ዌስት ብሮሚች፣ በርንሌይ እና ሼፊልድ ዩናይትድ በወራጅ ቃጣናው ከ18ኛ እስከ 20 ደረጃ ላይ ተደርድረዋል።

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ ሌዮኔል ሜሲ የአፍና የአፍንጫ መከለያ ጭምብል እንዲሁም ወፍራም ጃኬት ለብሶ ከአንድ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀያሪ ወንበር ላይ ለመቀመጥ በተገደደበት ጨዋታ ባርሴሎና ሪያል ቤቲስን 5 ለ 2 ድል አድርጓል። ባርሴሎና በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ሲያጠቃ ነበር። አንቱዋን ግሪስማን ሁለት ጊዜ ግብ ሊኾኑ የሚችሉ ኳሶች ለጥቂት ከግቡ ማእዘን አቅጣጫ ወደ ውጪ ወጥተውበታል። 22ኛው ደቂቃ ላይ ግን ባርሴሎና በዑስማን ዴምቤሌ የመጀመሪያዋን ግብ በድንቅ ኹኔታ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። የግብ ክልሉ ላይ አራት ተከላካዮች ቢኖሩም በበቂ ኹኔታ አለመከላከላቸው እና የዑስማን ዴምቤሌ ድንገተኛ ምት ግቧ እንድትቆጠር አስችሏል። በቅዳሜው ግጥሚያ የመጀመሪያ አጋማሽ ዕድል የራቀችው አንቱዋን ግሪስማን 26ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ሊኾን የሚችል ኳስ አምክኗል። 32ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምትም አንቱዋን ግሪስማን ለግብ ጠባቂው ነበር ያሳቀፈው። ምሽቱ ለአንቱዋን ግሪዝማን አልነበረም ማለት ይቻላል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው ሰአት ሳናብሪያ ሪያል ቤቲስን አቻ የምታደርገውን ግብ አስቆጥሯል።

UEFA Champions League | SSC Neapel - FC Barcelona | 1. TOR Barcelona, Antoine Griezmann
ምስል Reuters/C. de Luca

በሁለተኛው አጋማሽ አምበሉ ሊዮኔል ሜሲ ተቀይሮ ወደሜዳ ገብቷል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ሜሲ የተላከለትን ኳስ ሳይነካ ለአንቱዋን ግሪስማን አሳልፎ ግብ እንድትሆን አስችሏል። በእለቱ ግብ ለራቀው አንቱዋን የሊዮኔል ሜሲ መግባት የግብ አይነጥላውን ገፎለታል። ሊዮኔል ሜሲ ኳሱዋን የሚመታ መስሎ ሳይነካት በተከላካዮች እና በግብ ጠባቂው መሀል አልፋ ወደ አንቱዋን ግሪዝማን እንድታልፍ ማድረጉ ድንቅ ነበር። 60ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። 60ኛው ደቂቃ ላይ ሌዮኔል ሜሲ በፍጹም ቅጣት ምት ሦስተናዋን ግብ አስቆጥሯል። 72ኛው ደቂቃ ላይ በተከላካዮች ስህተት የሪያል ቤቲሱ ሎሬን ሞሮን ኹለተኛ ግቡን ማስቆጠር ችሏል። 81ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ሜሲ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል። 89ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ፔድሪ አምስተኛ እና የመጨረሻውን ግብ ከመረብ አሳርፏል።  

ሪያል ሶሴዳድ ላሊጋውን በ20 ነጥብ ሲመራው፤ ባርሴሎና 11 ነጥብ ይዞ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ግራናዳን 2 ለ0 ድል አድርጓል።  ቪላሪያል በ18 ነጥብ ኹለተኛ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ 17 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ትናንት ቫሌንሺያን 4 ለ1 ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ 16 ነጥብ ይዞ ደረጃው አራተኛ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ