1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 29 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 29 2015

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውድድር ዘርፍ የዕድሜ ማጭበርበር አፋጣኝ መፍትኄ የሚያሻው ጉዳይ ሆኗል። ባለፈው እሁድ አሰላ ከተማ ውስጥ በተጠናቀቀው ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ፉክክር በመጀመሪያ ማጣሪያ ብቻ 250 አትሌቶች የዕድሜ ማጭበርበር መፈጸማቸው ተገልጧል። የሀገር ውስጥና የውጭ የእግር ኳስ መረጃዎችንም አካተናል።

https://p.dw.com/p/4N9e3
FIFA Club World Cup | Seattle Sounders vs Al Ahly
ምስል Susana Vera/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውድድር ዘርፍ በዕድሜ ማጭበርበር አፋጣኝ መፍትኄ የሚያሻው ጉዳይ ሆኗል። ባለፈው እሁድ አሰላ ከተማ ውስጥ በተጠናቀቀው ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ፉክክር በመጀመሪያ ማጣሪያ ብቻ 250 አትሌቶች የዕድሜ ማጭበርበር መፈጸማቸው ተገልጧል። ሁኔታው ያሳሰባቸው በርካታ የስፖርቱ አፍቃሪዎች ሕግ እና ሥርዓት ይከበር ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። 

አትሌቲክስ

በአሰላ አረንጓዴው ስታድየም ለ11ኛ ጊዜ በተከናወነውና እድሜያቸው «ከ20 ዓመት በታች» አትሌቶች በተሳተፉበት ውድድር ብርቱ የዕድሜ ማጭበርበር መፈጸሙ ተዘግቧል። ከማክሰኞ ጥር 23 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ተካሂዶ እሁድ ዕለት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአጠቃላይ ውጤት አሸናፊ ሆኖ ውድድሩ ተጠናቋል። በውድድሩ ከተሳተፉ ከአንድ ሺህ በላይ አትሌቶች መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች ላይ የዕድሜ መጭበርበር መፈጸሙን የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ ምሥግናው ታደሰ አሳሳቢ ብሎታል።

እግር ኳስ

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ከአዳማ/ናዝሬት ከተማ ወደ ሌላ ቦታ መዛወሩ ተገልጧል። የ12ኛ እና የ11ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎችን ጨምሮ ከ14ኛ ሳምንት በኋላ የሚኖሩ ጨዋታዎች የሚከናወኑበት ከተማ እና ስታዲየሞች ገና አልተመረን ለመምረጥ ውሳኔ ይጠበቃል። ውድድሮቹን በድሬዳዋ አለያም በባሕር ዳር ከተማ ለማከናወን መታሰቡ ለዚያም ሜዳዎቹን የሚገመግም ኮሚቴ መዋቀሩ ተዘግቧል። የእግር ኳስ ውድድሮቹ ቀድሞ በታቀደላቸው ከተማ እና ስታዲየም ለምን እንደማይካሄዱ የተነገረ ነገር የለም። ውድድሮቹ የሚካሄዱባቸው ቦታዎች መረጣን በተመለከተ ግን ነገ ውሳኔ እንደሚሰጥ የፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማኅበር ሥራ አመራር ቦርድ ይፋ አድርጓል። ከተራዘሙ ጨዋታዎች መካከል በዝዙዎች ዘንድ ይጠበቅ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ይገኙበታል።

እግር ኳስ ዘረኝነት

Fußball Brasilien vs. Ghana Freundschaftsspiel
ብራዚሊያዊው አጥቂ ቪንሺየስ ጁኒየር ስፔን ውስጥ በተደጋጋሚ ለዘረንነት ስድብ ተዳጓልምስል Zumapress/picture alliance

ብራዚሊያዊው አጥቂ ቪንሺየስ ጁኒየር ስፔን ውስጥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የቆዳ ቀለም ያሰከራቸው ዘረኞች ዘረኛ ቃላትን እየተጠቀሙ ሲሰድቡት እንደነበር ተዘገበ።   የስፔን ሊግ ጉዳዩን በቀላሉ እንደማያየው እና ምርመራ እንደሚያደርግ ገልጧል። የቆዳ ቀለሙ ጥቁር የሆነው ብራዚሊያዊ አጥቂን «ጦጣ» ብሎ የሚሳደብ ሰው ያለበት ምስል በቴሌቪዥን መተላለፉን የስፔን ሊግ እንደሚመረምር ዐስታውቋል። ቪንሺየስ የዘረኝነት ጥቃት የደረሰበት ቡድኑ ሪያል ማድሪድ በማዮካ 1 ለ0 በተሸነፈበት ወቅት ነው። ጨዋታው ተጠናቆ ለአድናቂዎቹ ፎቶግራፍ ለመነሳት እና ለመፈረም በተዘጋጀበት ወቅትም የዘረኝነት ስድብ ተሰንዝሮበታል። ቪንሺየስ ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ስፔን ላሊጋ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ከዘረኞች ተደጋጋሚ ጥቃት ማምለጥ አልቻለም። የዘረኝነት ጥቃቱ መረን ለቅቆም ባለፈው ወር ከከተማው ተመሳሳይ ቡድን አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር በነበራቸው የ«ኮፓ ዴል ሬይ» ግጥሚያ ወቅት የቪንሺየስ አምሳለ ሰብ ድልድይ ላይ ተሰቅሎ ታይቶ ነበር። በባርሴሎና ካምፕ ኑ ስታዲየም ጨምሮ በተለያዩ ስታዲየሞች ተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃት ደርሶበታል።  የስፔን ሊግ የዘረንነት ስድቦቹን ለስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ማመልከቱንም ይፋ አድርጓል። «አንዳችም ትእግስት የሚያስፈልጋቸው የዘረኝነት ስድቦች ቪንሺየስ ላይ እየታየ» ነውም ብሏል። የስፔን ሊግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ዘረኞቹን ሕግ ፊት ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልጧል። ለዘረኝነት አንዳችም ቦታ እንደሌለው የገለጠው የእግር ኳስ ጉዳዮች የበላይ ተቋም ጥፋተኞች የእጃቸውን ማግኘታቸው አይቀርም ሲልም ተደምጧል።

Madrid vs Barcelona
ፎቶ ከማኅደር፦ ባርሴሎና ከሪያል ማድሪድ ጋር ሲጫወት። ግብ ጠባቂው ኳስ ለማጨናገፍ ሲጥርምስል Manu Fernandez/AP/picture alliance

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ከረዥም ጊዜ በኋላ ሽንፈት ሲገጥመው ሊቨርፑል የቁልቁለት ሩጫውን ተያይዞታል። አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ወራጅ ቀጣና ውስጥ በሚገኘው ኤቨርተን የገጠመው የ1 ለ0 ሽንፈት ትናንት ማንቸስተር ሲቲንም ደርሶታል። ማንቸስተር ሲቲ በተመሳሳይ የግብ ልዩነት በቶትንሀም 1 ለ0 ተሸንፏል። ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት በዎልቨርሀምፕተን የ3 ለ0 ከባድ ሽንፈት አስተናግዶ በ29 ነጥቡ ወደ 10ኛ ደረጃ ተንሸራቷል። አርሰናል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ50 ነጥብ ፕሬሚየር ሊጉን ይመራል። ማንቸስተር ሲቲ በ45 ይከተላል። ክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይድ እና ከዌስትሀም ጋር አንድ እኩል የተለያየው ኒውካስትል 4ኛ እና 5ኛ ደረጃን ይዘዋል። ነጥባቸውም 42 እና 40 ነው። ቶትንሀም በ39 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኤቨርተን፤ ቦርመስ እና ሳውዝሀምፕተን ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ።

ቡንደስሊጋ

Fussball Bundesliga VfL Wolfsburg und FC Bayern München
በጀርመን ቡንደስሊጋ የባየርን ሙይንሽን አጥቂ ጃማላ ሙሳይላምስል Michael Sohn/AP Photo/picture alliance

በጀርመን ቡንደስሊጋ ግን ከመሪው ባየርን ሙይንሽን ጀምሮ ስድስተኛ ደረጃ እስከሚገኘው ፍራይቡርግ የነጥብ ልዩነቱ ስድስት ብቻ ነው።  ባየርን ሙይንሽን ትናንት ቮልፍስቡርግን 4 ለ2 አሸንፎም ከዑኒዮን ቤርሊን የሚበልጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። 39 ነጥብ ያለው ዑኒዮን ቤርሊን ቅዳሜ ዕለት ማይንትስን 2 ለ1 ድል አድርጓል። ከትናንት በስትያ ፍራይቡርግን 5 ለ1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት የረታው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ37 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ላይፕትሲሽ ከኮሎኝ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል፤ በ36 ነጥብ ደረጃው 4ና ነው። አይንትራኅት ፍራንክፊርት እና ፍራይቡርግ 35 እና 34 ነጥብ ይዘው 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። አይንትራኅት ፍራንክፊርት ቅዳሜ ዕለት ሔርታ ቤርሊንን 3 ለ0 አሸንፏል። ሽቱትጋርት፤ ሔርታ ቤርሊን እና ሻልከ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

እሸቴ በቀለ