1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 24 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 24 2013

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ ማንቸስተር ሲቲ ላይ ለመቅረብ እና ከሊቨርፑል በነጥብ ለመራቅ የነበረውን ዕድል አምክኗል። በጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ፉክክር ባየር ሙይንሽን በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው። የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ውድድር ሳምንት ይጀምራል።

https://p.dw.com/p/3ogjj
Britain Soccer Premier League Fußball Crystal Palace vs Leicester City
ምስል Marc Atkins/AP/picture alliance

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ ማንቸስተር ሲቲ ላይ ለመቅረብ እና ከሊቨርፑል በነጥብ ለመራቅ የነበረውን ዕድል አምክኗል። ሊቨርፑል ትናንት ወሳኝ የሆነውን ድሉን አስመዝግቦ ዳግም ወደ ፉክክሩ ተመልሷል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ በ3 ነጥብ ልዩነት እየመራ ነው። በጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ፉክክር ባየር ሙይንሽን በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው። ከሦስተኛ እስከ ሰባተኛ ደረጃ ያሉት ቡድኖች እጅግ በተቀራረበ የነጥብ ልዩነት አንገት ለአንገት ተያይዘዋል። በበርካቶች ዘንድ ሲጠበቅ የነበረው የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ውድድር ሳምንት ይጀምራል። ከወዲሁ የማሟሟቂያ ውድሮች መከናወን ጀምረዋል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ ደረጃውን በ44 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ቅዳሜ ዕለት የምድቡ መጨረሻ ላይ የሚገኘው ሼፊልድ ዩናይትድን በጠበበ ሁኔታም ቢሆን 1 ለ0 ማሸነፉ በጅቶታል። በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛነት የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ3 ነጥብ ይበልጠዋል። ማንቸስተር ሲቲ ረቡዕ ዕለት በሚያደርገው ተስተካካይ ጨዋታ በርንሌይን ካሸነፈ ለዋንጫ ግስጋሴው ልዩነት አስፍቶ ይቀጥላል ማለት ነው። ከተሸነፈ ግን ማንቸስተር ዩናይትድ እና በ40 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚከተለው ሊቨርፑል ያሰጉታል። ስለዚህ ለማንቸስተር ሲቲ ቀጣዩ ተስተካካይ ግጥምያ እጅግ ወሳኝ ነው።

 በፕሬሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ መሪው ማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾች
በፕሬሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ መሪው ማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾችምስል Clive Brunskill/PA Images/imago images

ማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት ከአርሰናል ጋር ባደረገው ግጥሚያ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። በዚህም መሰረት ከሊቨርፑል ጋር የነጥብ ልዩነቱ በአንድ ብቻ ተወሰኗል። ሊቨርፑል በአንጻሩ ትናንት ዌስትሀም ዩናይትድን 3 ለ1 በሆነ አስተማማኝ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሦስተኛናነት ማሻሻል ችሏል። ዌስትሀም ዩናይትድ 35 ነጥብ ይዞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገናል። ላይስተር ሲቲ በአራት ነጥብ በልጦት የአራተኛ ደረጃን ተቆናጧል። አርሰናል በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በተጋራው ነጥቡ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 31 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። ቶትንሀም ሆትስፐር 33 ነጥብ ይዞ ደረጃው 6ኛ ነው። የወራጅ ቀጣናው ጠርዝ 17ኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ብራይተን ትናንት የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ዘንድሮ በፕሬሚየር ሊጉ በነጥብ ዝቅተኛ የሆኑ ቡድኖች ለዋናዎቹ ቡድኖች መከራ ሲሆኑ ተስተውለዋል። በርንሌይን ትናንት 2 ለ0 ማሸነፍ የቻለው ቸልሲ እንደቶትንሃም እና ኤቨርተን 33 ነጥብ ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቶትንሃም በግብ ክፍያ በልጦት 6ኛ ደረጃን ይዟል። በደረጃ ሰንጠረዡ ፉልሃም፣ ዌስብሮሚች እና ሼፊልድ ዩናይትድ ከ18ኛ እስከ 20ኛ ተደርድረዋል። ነጥባቸውም 14፣ 12 እና 8 ብቻ ነው።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ዘንድሮም ባየር ሙይንሽን በመሪነት እየገሰገሰ ነው። 45 ነጥብ ይዞ በደረጃው ቀዳሚ ሆኗል። ላይፕሲሽ በ38 ነጥብ ይከተላል። ቮልስፍሱርግ 35 ነጥብ ይዞ ደረጃው ሦስተኛ ነው። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ33 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ባየር ሌቨርኩሰን፣ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በግብ ክፍያ ልዩነት ከአምስተኛ እስከ 7ኛ ደረጃ ተደርድረዋል።  

ትናንት በኮሎኝ የ3 ለ1 ሽንፈት የገጠመው አርሜኒያ ቢሌፌልድ በወራጅ ቃጣናው ግርጌ 16ኛ ላይ ይገኛል። ከስሩ ማይንትስ እና ሻልከ 10 እና 8 ነጥብ ይዘው 17ኛ እና 18ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ትናንት በተደረገ ሌላ የቡንደስሊጋ ግጥሚያ ቮልፍስቡርግ ፍራይቡርግን 3 ለ0 ድል አድርጓል።  ቅዳሜ ዕለት ስድስት ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ብሬመን እና ሻልከ፤ እንዲሁም ዑኒዬን ቤርሊን ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አንድ እኩል ተለያይተዋል። ባየር ሙይንሽን እንደለመደው በሰፋ የግብ ልዩነት ሆፈንሃይምን 4 ለ1 አንኮታኩቷል። ቦሩስያ ዶርትሙንድም አውግስቡርግን በሰፋ ልዩነት 3 ለ1 አሸንፏል። ላይፕትሲሽ በጠበበ የግብ ልዩነት ባየር ሌቨርኩሰንን 1 ለ0 አሸንፏል።

የኮሎኝ አጥቂ ኤማኑዌል ዴኒስ ከአርሜኒያ ቢሌፌልድ ጋር በነበራቸው ግጥሚያ
የኮሎኝ አጥቂ ኤማኑዌል ዴኒስ ከአርሜኒያ ቢሌፌልድ ጋር በነበራቸው ግጥሚያምስል Steffie Wunderl/BEAUTIFUL SPORTS/imago images

ሔርታ ቤርሊን በፍራንክፉርት 3 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። ምናልባትም የመውረድ ዕጣ ሊገጥመው ይችላል። ለዚህም ይመስላል ቡድኑን ከመውረድ እንዲታደገው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዝነኛ ተጨዋች ሳሚ ከዲራን ከጁቬንቱስ ለማስመጣት ጫፍ ደርሷል። 

የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፉክክር

በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ለሦስት ሣምንታት የተሸጋሸገው የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ የፊታችን ሰኞ ይጀምራል። ከወዲሁ የዓለማችን ታላላቅ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኞች ለዋናው ውድድር የሚያደርሳቸውን ቅድመ-ዝግጅት እና ውድድሮች በማከናወን ላይ ናቸው። ተወዳዳሪዎች ለዋናው የአውስትራሊያ የሜዳ ፍጻሜ ውድድር ዕድል እንዲያገኙ በዚህ ሳምንት ውስጥ ስድስት ውድድሮችን ያከናውናሉ ተብሎ ተጠብቋል።

አውስትራሊያ ሜልቦርን ውስጥ ዛሬ በተከናወኑ ውድድሮች የዓለም የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜን ለ23 ጊዜያት ያሸነፈችው አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ ዳግም ብቃቷን ዐሳይታለች። የ39 ዓመቷ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሩስያዊቷ ተፎካካሪ ዳሪያ ጋቭሪሎቫን በ16 ዙር ውድድር 6 ለ1 እና 6 ለ4 ማሸነፍ ችላለች። ሴሬና ዊሊያምስን ከባለፈው የፈረንሳይ የፍጻሜ ውድድር እንድትወጣ ያደረጋት የቊርጭምጭሚት ኅመሟ በሚገባ የተሻላት ይመስላል። በኮሮና ምክንያት ከልጇ ጋር ሆቴል ውስጥ ራሳቸውን ነጥለው ከቆዩ በኋላ ያገኘችው ድል ምናልባትም በአውስትራሊያ የፍጻሜ ውድድር በሚቀጥለው ሳምንት ብርቱ ተፎካካሪ እንደምትሆን አመላካች ነው።

ሰርቢያዊው የዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች እና ባለድል ኖቫክ ጄኮቪች በኮሮና ለብቻው ራሱን ለይቶ
ሰርቢያዊው የዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች እና ባለድል ኖቫክ ጄኮቪች በኮሮና ለብቻው ራሱን ለይቶ ምስል Morgan Sette/AAP Image via AP/picture alliance

እንደ አውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ አዘጋጆች ከሆነ በርካታ ተጨዋቾች እና የቡድን አባላት በኮሮና ምክንያት ራሳቸውን እንዲነጥሉ ተደርገው ቆይተዋል። ከሁለት ሳምንት ግድም በፊት ወደ ሜልቦርን በበረረ የቻርተር አውሮፕላን ውስጥ ኮሮና በመገኘቱም ነበር ውሳኔው የተላለፈው። 72 ፕሮፌሽናል የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች እና የቡድን አማካሪዎች ለ14 ቀናት ከሆቴላቸው መውጣት ሳይፈቀድላቸው ቆይተዋል። ከነዚህ የዓለማችን ድንቅ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች መካከል የዛሬ አምስት ዓመት በሜልቦርን የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ ዋንጫ ያነሳችው ጀርመናዊቷ አንጄሊኩዌ ክሬበርም ትገኝበታለች። ሌሎቹ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች ለልምምድ ብቻ በቀን ቢያንስ ለአምስት ሰአት ሆቴላቸውን መልቀቅ ሲፈቀድላቸው ቆይቷል።  

ሰርቢያዊው የዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች እና ባለድል ኖቫክ ጄኮቪች በዘንድሮ የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ውድድር በበርካቶች ዘንድ ከሚጠበቊ ተፎካካሪዎች መካከል አንዱ ነው።  ኖቫክ ቀደም ሲል የኮሮና ደንብ ላላ እንዲል ባቀረበው ሐሳብ ብርቱ ነቀፌታ ገጥሞታል። እናም ኖቫክ ረዘም ባለው የማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ባሰፈረው ማብራሪያ ሌሎች እንደሚሉት ስግብግብ እና ራስ ወዳድነት አለመሆኑን ገልጧል። ይልቊንስ ከአውስትራሊያ ውድድር ኃላፊ ክሬግ ቲሌይ ጋር ባደረገው የኢሜል መልእክት ልውውጥ ቀደም ሲል ሁሉን ነገር ጠርቅሞ ይዘጋ ስለነበረው የኮሮና ደንብ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮችን ማውሳቱን ጠቊሞ ነበር።  

አጫጭር የስፖርት ዜናዎች

በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አስተናጋጅነት የዛሬ ወር የተጀመረው የከፍተኛ ሊግ የ2013 ዓም የምድብ «ሀ» የመጀመሪያ ዙር ውድድር በባቱ ከተማ በመካኼድ ላይ ነው። በሼር ኢትዮጵያ ስታዲየም በ9 ቡድኖች መካከል በሚካኼደው ውድድር ገላን ከተማ 1ኛ እንዲሁም ደሴ ከተማ እና መከላከያ እግር ኳስ ቡድኖች 2ኛ እና 3ኛ መውጣታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረ ገጹ ዘግቧል። ቀጣይ ውድድሮችን ዛሬ እና ነገ የሚቀጥሉ መሆኑም ተዘግቧል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰባት ሰዎች የኮሮና ተሐዋሲ እንደተገኘባቸው ተገለጠ። በፕሬሚየር ሊግ 2,957 እግር ኳስ ተጨዋቾች እና የቡድን አባላት ላይ በተደረገው የኮሮና መለያ ምርመራ ነው ውጤቱ የታወቀው። ብሪታንያ ሦስተኛ ዙር የኮሮና ወረርሺኝ ስላጠቃት የእንቅስቃሴ ገደብ አውጃለች። በሀገሪቱ በተሐዋሲው የተነሳ የሟቾች ቊጥር ከ106,000 መብለጡም ተዘግቧል። ከምዕራቡ ዓለም ሃገራት ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮና ክትባት በመጀመር ቀዳሚ የኾነችው ብሪታንያ እስካሁን ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ መክተቧም ተገልጧል። በፕሬሚየ ርሊጉ የኮሮና ጥብቅ ደንብ ተግባራዊ ከሆነ ቆይቷል። በኮሮና የተነሳም የዛሬ ዐሥራ አምስት ቀን አስቶን ቪላ ከኤቨርተን ጋር ሊያደርጉት የነበረው ግጥሚያ ለሌላ ጊዜ መዛወሩ ይታወሳል።

ግብጽ ውስጥ በተከናወነው 27ኛው የዓለም የወንዶች የእጅ ኳስ ፉክክር ስዊድንን ያሸነፈው የዴንማርክ ቡድን
ግብጽ ውስጥ በተከናወነው 27ኛው የዓለም የወንዶች የእጅ ኳስ ፉክክር ስዊድንን ያሸነፈው የዴንማርክ ቡድንምስል Petr David Josek/AP Photo/picture alliance

የሻልከው የ20 ዓመቱ ወጣት ተጨዋች ኦዛን ካባክ ወደ ሊቨርፑል ሊያቀና እንደሚችል እየተነገረ ነው። በእሱ ምትክ የ28 ዓመቱ ሽኮርዳን ሙስጣፊ  ከአርሰናል ይመጣል ተብሏል። ሊቨርፑል ቫን ጃይክ ለረዥም ጊዜ በጉዳት ከተገለለ ወዲህ የመሀል ተከላካይ ሲፈልግ ነበር። ምናልባትም ኦዛን ካባክ ይህን የሊቨርፑል ክፍተት ይደፍንለት ይሆናል። የዛሬ ሁለት ዓመት ኦዛን ካባክ ከሽቱትጋርት ወደ ሻልከ የተዛወረው በ15 ሚሊዮን ዩሮ ነበር።

ግብጽ ውስጥ በተከናወነው 27ኛው የዓለም የወንዶች የእጅ ኳስ ፉክክር ዴንማርክ ስዊድንን አሸንፋ ለሁለተኛ ጊዜ በተከታታይ ዋንጫ መውሰድ ችላለች። ዴንማርክ ስዊድንን በፍጻሜው ያሸነፈችው 26 ለ24 በሆነ ጠባብ የነጥብ ልዩነት ነው። የስፔን ቡድን የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልሟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ