1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 17 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ማክሰኞ፣ ጥር 18 2013

ፍራንክ ላምፓርድ ከቸልሲ አሰልጣኝነት መሰናበቱ ዛሬ ተዘግቧል። በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ያልተጠበቊ ውጤቶች ተከስተዋል። ማንቸስተር ሲቲ ዝቅተኛ ዲቪዚዮን በሚገኝ ቡድን ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ ለድል በቅቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዡን የነጠቀው ዋነኛ ተቀናቃኙ ሊቨርፑልን ከኤፍ ኤ ካፕም አሰናብቶታል።

https://p.dw.com/p/3oOTY
Deutschland Bundesliga Borussia Mönchengladbach vs Borussia Dortmund | Tor 4:2
ምስል Lars Baron/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ፍራንክ ላምፓርድ ከቸልሲ አሰልጣኝነት መሰናበቱ ዛሬ ተዘግቧል። በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ያልተጠበቊ ውጤቶች ተከስተዋል። ማንቸስተር ሲቲ ዝቅተኛ ዲቪዚዮን በሚገኝ ቡድን ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ ለድል በቅቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዡን የነጠቀው ዋነኛ ተቀናቃኙ ሊቨርፑልን ከኤፍ ኤ ካፕም አሰናብቶታል። ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በጣሊያን ቡድን ላይ ክስ ሊመሰርት ይችል ይሆናል። ክሱ ከተጀመረ የጣሊያን ቡድንም እንደ ሩስያ ቡድን በኦሎምክ ጨዋታዎች እንደ ሀገር መሳተፍ አይችልም። በቡንደስሊጋው ባየር ሙይንሽን በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው። ትናንት መከረኛው ሻልከ ላይ በግብ ተንበሽብሿል።

በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ዘጠነኛ ዙር የእግር ኳስ ግጥሚያ ፋሲል ከነማ በ22 ነጥብ እየመራ ይገኛል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ16 ነጥብ ይከተላል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩትሀዲያ ሆሳዕና ዛሬ ከሰአት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። በዚህም መሰረት በደረጃ ሰንጠረዡ 16 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና 16 ነጥብ ያለው ኢትዮጵያ ቡና  አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ቀደም ሲል ጣሬ በነበረው ሌላ ግጥሚያ ድሬዳዋ ከተማ አዳማ ከተማን 3 ለ0 አሸንፏል። ድሬዳዋ ከተማ በ10 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም አዳማ ከተማ በ4 ነጥብ 12 ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ሁለቱም አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀራቸዋል።

ኤፍ ኤ ካፕ

በፕሬሚየር ሊጉ ዝቅተኛ አቅም ባለው በርንሌይ ባለፈው ሳምንት 1 ለ0 የተሸነፈው ሊቨርፑል በኤፍ ኤካፑ ደግሞ በማንቸስተር ዩናይትድ 3 ለ2 ተሸንፏል። ሊቨርፑልን ጉድ ያደረገው በርንሌይ ትናንት በኤፍ ኤ ካፑ ፉልሃምን 3 ለ0 ኩም አድርጓል። ማንቸስተር ዩናይትድ ዋነኛ ተቀናቃኙ ሊቨርፑልን ድል ባደረገበት የትናንቱ የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ቀዳሚዋን ግብ በ18ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሞሀመድ ሳላህ ነበር። በ26ኛው ደቂቃ ላይ ግን ማሶን ግሪንውድ ማንቸስተር ዩናይትድን አቻ የምታደርገውን ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ማርኩስ ራሽፎርድ በ48ኛው ደቂቃ አግብቶ ማንቸስተር ዩናይትድ ቢመራም፤ በ58ኛው ደቂቃ ላይ ሞሀመድ ሳላህ 2ኛ ግቡን በማስቆጠሩ ሁለት እኩል አቻ ሆነው ቆይተዋል። በ78ኛዋ ደቂቃ ላይ ግን ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ ብሩኖ ፌርናንዴዝ በማስቆጠሩ ማንቸስተር ዩናይትድ ለድል በቅቷል። ሊቨርፑልም በአራተኛው ዙር ከኤፍ ኤ ካፑ ተሰናብቷል።

Fußball Europa League FC Valencia - FC Arsenal
ምስል picture-alliance/empics/N. Potts

ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ በድል ከፍ ከፍ ሲል ሊቨርፑል አሽቆልቊሏል። ፕሬሚየር ሊጉን ከ19 ጨዋታዎች በኋላ ማንቸስተር ዩናይድ በ40 ነጥብ ይመራል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ በ38 ነጥብ ይከተላል። በተስተካካይ ጨዋታው ነገ ዌስትብሮሚችን ካሸነፈ ማንቸስተር ሲቲ በተራው የመሪነቱን ሥፍራ ከማንቸስተር ዩናይትድ ይረከባል ማለት ነው።

ላይስተር ሲቲ በ38 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ቀደም ሲል በፕሬሚየር ሊጉ መሪነት የዘለቀው ሊቨርፑል በ34 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ምናልባትም አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም ለተስተካካይ ጨዋታው የፊታችን ሐሙስ ሊቨርፑልን ሲገጥም ካሸነፈው ሊቨርፑል ወደ አምስተኛ ደረጃም ሊያሽቆለቊል ይችላል።

ሊቨርፑልን ባሸነፉበት የኤፍ ኤ ካፕ ውድድር ጉልበቱ ላይ ጥሩ ስሜት ያልተሰማው የማንቸስተር ዩናይትዱ ማርኩስ ራሽፎርድ የጉልበት ምርመራ እንደሚደረግለት አሰልጣኝ ኦሌ ጉናር ሶልስካዬር ዐሳውቀዋል። ማርኩስ ራሽፎርድ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ለራሱ 15ኛ ግቡን ከመረብ ከማሳረፉ አስቀድሞ በ26ኛው ደቂቃ ላይ ለማሶን ግሪንውድ ግብ ኳሷን አመቻችቷል።  ከረፍት መልስም የመጨረሻው ፊሽካ ከመነፋቱ በፊት በአንቶኒ ማርሺያል ተተክቷል።

ባለፈው የኤፍ ኤ ካፕ ፍጻሜ አርሰናል ቸልሲን ድል ሲያደርግ ማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠረው ፒየር ኤመሪክ ኦውባማያንግ ለረዥም ጊዜ አለመሰለፍ ቡድኑን ሊጎዳው እንሚችል ተነገረ። የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ግን ከ19 ዓመቱ ብራዚሊያዊ አጥቂ ጋብሪዬል ማርቲኔሊ ብዙ እንደሚጠብቊ ተናግረዋል። አርሰናል በኤፍ ኤ ካፕ ውድድር በሳውዝሀምፕተን 1 ለ0 ሲሸነፍ አውባሜያንግ አልተሰለፈም። ጋቦናዊው አጥቂ በውድድሩ ወቅት ከተቀመጠበት የቅያሪ ወንበር ተነስቶ በግል ጉዳይ ከቡድኑ ተለይቶ መኼዱም ተዘግቧል። ሚኬል አርቴታ ፒዬር ኤመሪክ ኦውባማያንግን ለምን ያህል ጊዜ ሳይሰለፍ እንደሚቀጥል ከመግለጥ ተቆጥቧል።

የ31 ዓመቱ ጋቦናዊ አጥቂ ፒየር ኤመሪክ ኦውባማያንግ
የ31 ዓመቱ ጋቦናዊ አጥቂ ፒየር ኤመሪክ ኦውባማያንግምስል Reuters/K. Pfaffenbach

የ31 ዓመቱ ጋቦናዊ አጥቂ ግን በዚህ የጨዋታ ዘመን ወደ ቀድሞ ብቃቱ ለመመለስ በትግል ላይ ይገኛል።  በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን ስምንት ግቦችን ብቻ ከመረብ በማሳረፍ፣ ለግብ የሚሆን ኳስ ያመቻቸው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።   ባለፈው የኤፍ ኤካፕ የፍጻሜ ግጥሚያ ቸልሲን 2 ለ1 ሲረቱ ሁለቱንም ግቦች ያስቆጠረው ፒዬር ኤመሪክ ኦውባማያን ነበር። ለዚያውም ፑሊሲች ጨዋታው በተጀመረ አምስተኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ ሲመሩ ቆይተው ነበር ይኸው ጋቦናዊ አጥቂ ከጉድ አውጥቶ ለድል ያበቃቸው የነበረው። ያኔ በ28ኛው ደቂቃ እና በ67ኛው ደቂቃ ላይ በተገኘው ፍጹም ቅጣት ምት ግቦች አርሰናልን ለ14ኛ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ባለድል አድርጎ ቢያስፈነድቅም ዘንድሮ ግን ይኸው ጋቦናዊ አጥቂ በአርሰናል የቅያሪ ወንበር ላይ ተከፍቶ ለመቀመጥ ተገዷል።  በዘንድሮው የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ያለፈው ዓመት ባለድል አርሰናል በቅዳሜ ዕለቱ የሳውዝሀምፕተን የ1 ለ0 ሽንፈት ከውድድሩ ተሰናብቷል።

በኤፍ ኤ ካፕ ሌላ ግጥሚያ፦ ማንቸስተር ሲቲ አራተኛ ዲቪዚዮን በሚገኘው ቼልቴንሐም ቡድን ጨዋታው በተጀመረ አንድ ሰአት ላይ በተቆጠረ ግብ በአስደንጋጭ ኹኔታ 1 ለ0 ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ ለድል በቅቷል። ለቼልቴንሐም በ59 ደቂቃ ላይ ግብ ያስቆጠረው አልፊዬ ማይ ነው። በዚሁ በአራተኛ ዙር የኤፍ ኤ ካፕ ውድድር መደበኛ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 9 ደቂቃ እስኪቀረው ድረስ ማንቸስተር ሲቲ እየተመራ ነበር። በ81ኛው፣ 84ኛው እና በ94ኛው ደቂቃዎች በፊል ፎደን፣ ጋብሪዬል ጄሱስ እና ፌራን ቶሬዝ ግቦች 3 ግቦችን በተከታታይ በማስቆጠር ደጋፊዎቹን እፎይ አስብሏል።

ቡንደስሊጋ

በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 4 ለ2 የተሸነፉት የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋቾች በከፊል
በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 4 ለ2 የተሸነፉት የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋቾች በከፊል ምስል Martin Meissner/AP Photo/picture alliance

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን በ42 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ላይፕሲሽ በ35 ነጥብ ይከተላል። ባየር ሌቨርኩሰን 32 ነጥብ ይዞ፤ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተመሳሳይ 32 ነጥብ ያለው ቮልፍስቡርግ 4ኛ ደረጃን ይዟል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በ31 ነጥብ፣ አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ30፤ እንዲሁም ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ29 ነጥብ ከ5ኛ እስከ 7ኛ ደረጃ ተደርድረዋል።  ኮሎኝ በ15 ነጥቡ የወራጅ ቀጣና አፋፍ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማይንትስ እና ሻልከ በ10 እና 7 ነጥብ የመጨረሻ የወራጅ ቀጣናው ግርጌ 17ኛ እና 18ኛ ላይ ተዘርግተዋል።

ትናንት በነበሩ የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያዎች፦ ኮሎኝ በሆፈንሃይም የተሸነፈው 3 ለ0 ነበር። ሆፈንሃይም እንደ ሽቱትጋርት እና አውግስቡርግ 22 ነጥብ ይዞ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሽቱትጋርት 10ኛ ከታች አውግስቡርግ 12ኛ ደረጃ ላይ ናቸው። መሪው ባየር ሙይንሽን ትናንት በነበረው ግጥሚያ ሻልከን 4 ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎታል። በቅዳሜ ዕለት ግጥሚያዎች ደግሞ፦ ቬርደር ብሬመን ሔርታ ቤርሊንን 4 ለ1 ድል አድርጓል። ቬርደር ብሬመን 21 ነጥብ ይዞ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የትናንት ተጋጣሚው ሔርታ ቤርሊን በ17 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ይዟል። 17 ነጥብ ይዞ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሚኒያ ቢሌፌልድ በአይንትራኅት ፍራንክፉርት የ5 ለ1 ከባድ ሽንፈት ገጥሞታል። ቮልፍስቡርግ ባየርን ሌቨርኩሰንን 1 ለ0 ሲያሸንፍ፤  ሽቱትጋርት በፍራይቡርግ 2 ለ 1 ተረትቷል። ፍራይቡርግ 27 ነጥብ ይዞ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አውግስቡርግ ዑኒዬን ቤርሊንን 2 ለ 1 በረታበት የቅዳሜ ዕለት ግጥሚያ ዶርትሙንድ ለቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ እጅ ሰጥቷል። 4 ለ2ም ተሸንፏል።

አጫጭር ዓለም አቀፍ የስፖርት ዜናዎች

ቸልሲ ለ18 ወራት በአሰልጣኝነት ያገለገለውን ፍራንክ ላምፓርድ ዛሬ አሰናብቷል። አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ በተጨዋችነት ዘመኑ ከቡድኑ ልብ የማይወጣ ውለታ የዋለ ነው። ሆኖም ግን በበጋ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከ200 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ቢያውልም እንደተጨዋችነት ዘመኑ ግን በአሰልጣኝነቱ ከቸልሲ ጋር አልተሳካለትም። የቀድሞው የፓሪ ሳን ጃርሞ ቡድን አሰልጣኝ ጀርመናዊው ቶማስ ቱኁል የላምፓርድን ቦታ ይተካሉ ተብለው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው አሰልጣኞች መካከል ቀዳሚው መሆናቸውም ተዘግቧል። አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ቸልሲን ባለፈው የፕሬሚየር ሊግ የጨዋታ ዘመን በግብ ልዩነት ብቻ በማንቸስተር ዩናይትድ ተበልጦ በአራተኛነት እንዲያጠናቅቅ ያስቻለ እንዲሁም በኤፍ ኤ ካፕ የዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ደርሶ የነበረ አሰልጣኝ ነው። በፍጻሜው ግጥሚያ በአርሰናል 2 ለ1 ነበር የተሸነፈው። በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን ግን ቸልሲ በስምንት የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች በአምስቱ ተሸንፎ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።     

 አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ከቸልሲ ተሰናበተ
አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ከቸልሲ ተሰናበተምስል Phil Noble/dpa/picture alliance

ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴ

የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ (IOC) የረዥም ጊዜ አባል ዲክ ፓውንድ፦ የውድድር ጊዜው የተራዘመው የቶኪዮ ኦሎምፒክ በኮቪድ-19 ምክንያት ያለ ታዳሚ ሊከናወን እንደሚችል በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተናግረዋል። «ጥያቄው የግድ ሊኖር ይገባል ወይንስ ቢኖር ደስ ይላል ነው?» ብለዋል ለ43 ዓመታት ግድም የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ካናዲያዊ።  ታዳሚያን ቢኖሩ ደስ ይላል፤ ግን የግድ ይኑሩ ማለት አይደለም ሲሉም የ78 ዓመቱ የኦሎምፒክ አባል ውድድሩ ያለታዳሚ ሊካኼድ እንደሚችል ጥቊምታ ሰጥተዋል።

የሩስያ ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ኩባንያ (RUSADA) የሩስያ እንደሀገር በኦሎምፒክ እና ሌሎች ዋና ዋና የስፖርት ክንውኖች ላይ የተጣለባት ገደብን አስመልክቶ አቤቱታ እንማያቀርብ ዛሬ ይፋ አድርጓል።   የስፖርት ብይን ሰጪ ፍርድ ቤት (CAS) ሩስያ እንደ ሀገር በታላላቅ የስፖርት ክንውኖች ላይ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት እንዳትሳተፍ መወሰኑ ይታወሳል። ሩስያ የቶኪዮ ኦሎምፒክ እና እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2022 ሊከናወን ቀጠሮ በተያዘለት የቤጂንግ የክረምት ኦሎምፒክ ላይ እንዳትሳተፍ እገዳ ተጥሎባታል።  ሆኖም የሩስያ አትሌቶች በሀገራቸው ባንዲራ ስር ሳይካተቱ በውድድሮቹ መሳተፍ ይችላሉ። 

የሩስያ ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ኩባንያ (RUSADA)
የሩስያ ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ኩባንያ (RUSADA)ምስል picture-alliance/dpa/M. Shipenkov

ከኦሎምፒክ ጋር በተያያዘ ዜና፦ የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የጣሊያን ቡድን በቅሌት የሚያስጠይቅ ምርመራ ሊጀምር እንደሚችል ዐሳውቋል። ምርመራው ከተጀመረና ቡድኑ ጥፋተኛ ከሆነ የጣሊያን ቡድንም በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ላይሳተፍ ይችል ይሆናል። ኮሚቴው፦ የስፖርት ገቢዎችን እንዲቆጣጠር በጣሊያን መንግስት ከ2 ዓመት በፊት የተቋቋመው «ስፖርት ኤ ሳሉቴ» የተሰኘው ተቋም የመንግስት ጣልቃ ገብነት አለው ብሏል። አዲሱ ተቋም የሚጠቀመው ገንዘብም ቀደም ሲል በሀገሪቱ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እጅ የነበረ ነው ሲል ከሷል። ኮሚቴው የጣሊያን ቡድንን ከከሰሰ የሀገሪቱ የኦሎምፒክ ቡድን አባላት በውድድሩ የሚሳተፉት ልክ እንደ ሩስያ አትሌቶች ከሀገራቸው ባንዲራ ውጪ ይሆናል። ያኔም በውድድሮቹ ወቅት የሀገራቸውን ስም ማስጠራት፣ ብሔራዊ መዝሙራቸውን ማስዘመር እና ሠንደቅ ዓላማ ማውለብለብ አይፈቀድላቸውም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ