1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 22 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ማክሰኞ፣ ጥር 23 2015

ከጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ወዲህ ባየርን ሙይንሽን በቡንደስሊጋ ማሸነፍ አልቻለም። በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ አርሰናል እና ሊቨርፑል ጓዛቸውን ጠቅልለው ተሰናብተዋል። ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ አሁንም አለን ብለዋል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጀርመን የካርልስሩኸ የዓለም የቤት ውስጥ የሩጫ ፉክክር ድል ቀንቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/4Mt31
Fußball Bundesliga | Bayer Leverkusen - Borussia Dortmund | Karim Adeyemi
ምስል Dennis Ewert/RHR-FOTO/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ከጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ወዲህ ባየርን ሙይንሽን በጀርመን ቡንደስሊጋ አንዱንም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። ከፊቱ የጀርመን ዋንጫ እና የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ይጠብቁታል። በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ አርሰናል እና ሊቨርፑል ጓዛቸውን ጠቅልለው ተሰናብተዋል። ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ አሁንም አለን ብለዋል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጀርመን የካርልስሩኸ የዓለም የቤት ውስጥ የሩጫ ፉክክር ድል ቀንቷቸዋል። በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ዳግም ድል ተቀዳጅቷል። የዓለማችን ምርጡ የቴኒስ ተጨዋች መሆኑንም አስመስክሯል። 

አትሌቲክስ

Symbolbild Leichtathletik Laufen
የሯጮች እግሮች በመሮጫ ሜዳው ላይ ይታያሉምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

በጀርመን የካርልስሩኸ የቤት ውስጥ የዓለም የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተከታትለው በመግባት ደማቅ ድል አስመዝግበዋል። ባለፈው ዐርብ ምሽት ጀርመርን ካርልስሩኸ ከተማ ውስጥ በተከናወነው በዚህ ውድድር ለምለም ኃይሉ 8 ደቂቃ ከ37,55 ሰከንድ በመሮጥ የአንደኛ ደረጃን ስታገኝ፤ የሀገሯ ልጅ ወርቅዋ ጌታቸው በ43 ማይክሮ ሰከንድ ተበልጣ ሁለተኛ ወጥታለች። ዳዊት ሥዩም በ8 ደቂቃ ከ39,20 ሰከንድ የሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች። ሚዛን ዓለም እና ዘርፌ ወርዶፋ 4ኛ እና 5ኛ ወጥተዋል።

በወንዶች ተመሳሳይ የቅዳሜ ዕለቱ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አዳጊ አትሌት አብዲሳ ፈይሳ በ3 ሺህ ሜትር ርቀት 7 ደቂቃ ከ40 ነጥብ 35 ሰከንድ በመሮጥ ታሪክ አስመዝግቧል። አትሌት አብዲሳ በ17 ዓመቱ የመጀመሪያው በሆነው የቤት ውስጥ የሩጫ ፉክክር በዚህ ዕድሜ የተገኘ ፈጣኑ ሰአት ተብሎ እንደተመዘገበለት የዓለም አትሌቲክስ ዘግቧል። ብርቱ ፉክክር በታየበት በዚሁ ውድድር ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ግርማ አዲሱ የጀርመኑ ሯጭ ሔንድሪክ ሮቢንን በአንድ ሰከንድ ልዩነት ተከትሎ የሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል። የገባበት ሰአትም 7 ደቂቃ ከ41.53 ሰከንድ ተመዝግቧል።

የዛሬ ዓመት በ5 ኪሎ ሜትር የወንዶች የሩጫ ፉክክር የዓለም ክብረ ወሰን የሰበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት ብርሃኑ አረጋዊ በካርልስሩኸው ፉክክር በ3000 ሜትር ፈጣን የተባለውን ሰአት 7:26.20 በመሮጥ ማስመዝገቡ ይታወሳል። በያኔው ውድድር አትሌት ብርሃኑ ክብረወሰን ሳይሰብር የቀረው እጅግ ለጥቂት ነበር።  በወቅቱ ግን በ3000 ሜትር የሩጫ ውድድር ታሪክ አምስተኛው ፈጣን ሰአት ተብሎ ተመዝግቦለታል።

World Athletics Championships I Bronze für deutsche Sprintstaffel
ፎቶ ከማኅደር፦ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን በዩጂን ኦሬገን፤ ዩናይትድ ስቴትስምስል Patrick Smith/AFP

በዐርብ ምሽቱ የካርልስሩኸ የ800 ሜትር የሴቶች የሩጫ ፉክክርም ፍሬወይኒ ኃይሉ በስሎቫኪያዋ አኒታ ሖርቫት ለጥቂት በ4 ማይክሮ ሰከንዶች ተበልጣ ሁለተኛ ወጥታለች። አንደኛ ደረጃ ያገኘችው አኒታ ሖርቫት የገባችበት ሰአት 2 ደቂቃ ከ44 ማይክሮ ሰከንድ ነው።  የስዊትዘርላንዷ ሯጭ ሎሬ ሖፍማን የሦስተኛውን ደረጃ አግኝታለች።

እግር ኳስ

በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ኢትዮጵያዊው አንጋፋ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ በቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል። ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በስፖርት ጋዜጠኝነት ከ25 ዓመታት በላይ አገልግሏል።  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፦ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ጋዜጣዎች እና መፅሄቶች እንዲሁም የሬድዮ ዝግጅቶች ላይ በመሥራት እንደሚታወቅ በመግለጥ የሀገራችን ስፖርት የሚድያ ትኩረት እንዲኖረው ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ ምስጉን ጋዜጠኞች ግንባር ቀደሙ ነበር ብሏል።

ቡንደስሊጋ፦

በጀርመን ቡንደስሊጋ ለዐሥር ጊዜያት ዋንጫ በማንሳት ማንም የማይስተካከለው ባየርን ሙይንሽን ዘንድሮ ሦስቱንም ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ተስኖታል። ከገና ረፍት በኋላ ዳግም በጀመረው ቡንደስሊጋ ከላይፕትሲሽ ጋር አንድ እኩል በመለያየት የጀመረው ባየርን ሙይንሽን፤ ከኮሎኝም ሆነ ቅዳሜ ዕለት ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር በተመሳሳይ አንድ እኩል ተለያይቷል። ሁኔታው አሰልጣኝ ጁሊያን ናግገልስማን ላይ ብርቱ ጫና አሳድሯል። አሰልጣኙ ከኮሎኝ ጋር ከነበራቸው ጨዋታ በኋላ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ቀጣዩን ብለዋል።

Fußball Bundesliga | Bayer Leverkusen - Borussia Dortmund
በጀርመን ቡንደስሊጋ የቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ባየርን ሌቨርኩሰን ተጨዋቾችምስል Lars Baron/Getty Images

«15 ደቂቃዎች በጣም ጥሩ ነበርን። ኳስ ከተነጠቅን በኋላ እንኳን ፈጣን ነበርን። በጣም ጉጉት እና ስሜት ነበረን። ግን ያን ፈጣን እንቅስቃሴ ድንገት ተነጠቅን። በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ወደ በኋላ እንደውም ትንሽ ጥንቃቄ ያበዛን ይመስለኛል። በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኘናቸውን ሁለት ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ወይንም መሆን የሚገባቸው እድሎች አልተጠቀምንባቸውም።»

ባየርን ሙይንሽን ከሁለት ሳምንት በኋላ በሻምፒዮንስ ሊግ ከፓሪ ሳን ጃርሞ ጋር ከመጋጠሙ አስቀድሞ ረቡዕ በጀርመን ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ከማይንትስ ጋር ይጋጠማል። በቡንደስሊጋው ማይንትስ 35 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባየርን ሙይንሽን 37 ነጥብ ይዞ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ቢቆይም ዑኒዮን ቤርሊን በአንድ ነጥብ ልዩነት ከስሩ ይገኛል። ዑኒዮን ቤርሊን ቅዳሜ ዕለት ከከተማው ቡድን ሔርታ ቤርሊን ጋር ባደረገው ግጥሚያ 2 ለ0 አሸንፏል። ማይንትስ ትናንት ቦሁምን 5 ለ2 ሲያሸንፍ፤ ቬርደር ብሬመን ቮልፍስቡርግን 2 ለ1 ድል አድርጓል። በደረጃ ሰንጠረዡ 34 ነጥብ ይዞ 4ኛ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት ባዬር ሌቨርኩሰንን 2 ለ0 አሸንፏል። ኮሎኝ ወደ ሻልከ አቅንቶ ያለምንም ግብ ተለያይቷል።

ኤፍ ኤ ካፕ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎች ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ ድል ሲቀናቸው፤ አርሰናል እና ሊቨርፑል በሽንፈት ተሰናብተዋል። በትናንቱ ግጥሚያ ብራይተን ሊቨርፑልን 2 ለ1 በማሸነፍ አሰናብቶታል። ከትናንት በስትያ በነበሩ የኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታዎች ማንቸስተር ዩናይትድ ሬዲንግን 3 ለ1 አሸንፏል። ከፕሬሚየር ሊግ የዘንድሮ ተጋጣሚዎች መካከል፦ ማንቸስተር ሲቲ የዘንድሮ ዋነኛ ተቀናቃኙ አርሰናልን እንዲሁም ላይስተር ሲቲ ዋልሳላን 1 ለ0 ድል አድርገዋል። ሊድስ ዩናይትድ አክሪንግተንን 3 ለ1 ሲያሸንፍ ፉልሀም ከሰንደርላንድ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ሳውዝሐምፕተን ብላክፑልን 2 ለ1 አሸንፏል። ዛሬ ማታ ዌስትሀም ዩናይትድ ወደ ዴርቢ ኮንቲን በማቅናት በ4ኛው ዙር የኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታ ይጋጠማል።

የሜዳ ቴኒስ፦

Tennis | Australian Open Finale | Gewinner Novak Djokovic
በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ያሸነፈውን ዋንጫ ከፍ አድርጎምስል Paul Crock/AFP

በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ትናንት ሜልቦርን ከተማ ውስጥ ድል በመቀዳጀት አሁንም የዓለማችን ምርጡ የቴኒስ ተጨዋች መሆኑን አስመሰከረ። ኖቫክ ጄኮቪች ተጋጣሚው እስጢፋኖስ ጺጺጳስን 6 ለ3፤ እንዲሁም ሁለት ጊዜ 7 ለ6 በማሸነፍ ነው 10ኛድሉን ሜልቦርን ላይ ያጣጣመው።

በዚህ ውጤቱም ኖቫክ ጄኮቪች በዓለም የሜዳ ቴኒስ አጠቃላይ ብቃት መለኪያ 7070 ነጥብ በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የስፔኑ ካርሎስ አልካራዝ 6730 ነጥብ በመሰብሰብ የሁለተኛ ደረጃ ይዟል። የግሪኩ ጺጺፓስ በ6195 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃ አግኝቷቷል። ስ«ፔናዊው የዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተፎካካሪ ራፋኤል ናዳል 6ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። በሴቶች ፉክክር የ24 ዓመቷ ቤላሩሳዊት አርያና ሳባሌንካ የዌምብልደን አሸናፊዋ ኤሌና ሪባኪናን ድል አድርጋለች። በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ አርያና ኤሌናን ቅዳሜ ዕለት ያሸነፈችው 6-4 እና 6-3 ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ