1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥምቀት በዓል አከባበር በተለያዩ ከተሞች

ዓርብ፣ ጥር 11 2010

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበረዉ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ዛሬም በተለያዩ ከተሞች ደምቆ መከበሩን በስፍራዉ የተገኙ የበዓሉ ተካፋዮች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ከአዲስ አበባ፤ ጎንደር እና ባህር ዳር የበዓሉ ታዳሚዎች በያሉበት ክብረ በዓሉ የደመቀ እንደሆነ ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/2rATp
Äthiopien Epiphany fest
ምስል DW/Z. Haile

በዓሉ በደማቅ ሁኔታ መከበሩን ታዳሚዎቹ ይናገራሉ፤

በዓሉ እንደወትሮው ሁሉ ከትናንት ጥር 10 ቀን ማለትም ከከተራ በዓል ጀምሮ ታቦታት ከየ አድባራቱ ወጥተው በየተዘጋጀላቸዉ ማደሪያ በማረፍ በሕዝበ ክርስቲያኑ፤ በካህናት ማኅሌት እንዲሁም ወረብ ታጅበው ስብሃተ እግዚአብሔር ሲደርስ መዋሉንም ያነጋገርናቸው ምዕመናን ያስረዳሉ። አዲስ አበባ ላይ ታቦታትን ከጃንሜዳ አጅበው ሲመለሱ መንገድ እንደሆኑ ካገኘናቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች አንዳንዶቹ ለበዓል የወጣው ሕዝብ ካለፈው ዓመት ቀንሶ ማየታቸውን ይናገራሉ። ለሌሎቹ ደግሞ ከወትሮው ለየት ብሎ በዓሉ የደመቀ ነበር።

በበዓሉ ላይ ካነጋገርናቸዉ መካከል በጠቅላይ ቤተክህነት የልማት እና ተራድኦ ኮሚሽን መምሪያ፤መምህር አስቻለዉ ካሴ ፤ የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ከወትሮው ለየት ባለ የመገናኛ ብዙሃንን ሽፋን ማግኘቱን ገልጸው፤ የወጣቱ ተሳትፎ ለየት ማለቱን ዘርዝረዋል።

Äthiopien Epiphany fest
ምስል DW/H. Yared

በአዲስ አበባዉ ጥምቀተ ባህር የተገኘው ሕዝብ ቁጥር የቀነሰው ምናልባት ወደጎንደር ለበዓሉ ብዙ ሰው ተጎዞ ይሆናል የሚለውን የበዓሉን ታዳሚዎች ግምት በመያዝ ወደ ጎንደር ደወልን። ታቦት አጅቦ ሲመለስ ያገኘነው የከተማዋ ነዋሪ የሆነዉ ወጣት ዳዊት፤ ከአምናዉ የበለጠ ሕዝብ ለበዓሉ ጎንደር ከተማ መገኘቱን አመክቷል። በዓሉ ባህር ከተማም ደምቆ መከበሩን ከስፍራዉ ያነጋገርነዉ ዲያቆን ሙሉቀን ብርሃኑ በአጭሩ ገልጾልናል። የበዓሉ ተሳታፊዎች የጥምቀትን በዓል በማዕዳሰስ ቅርስነት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ስለሚደረገዉ ጥረትም የሚሰማቸዉን አካፍለዉናል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ