1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው ጥሪ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 21 2014

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በድል ለማጠናቀቅ መቃረባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ። ከጦር ግንባሩ ሆነው በተንቀሳቃሽ ምስል መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደራዊ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው የተባለውን የሰሜን ወሎ ዞን ተራራማው ስፍራ ጋሸናን በአጠረ ጊዜ እንደሚቆጣጠሩትም ዐስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/43fN7
Äthiopien I Konfliktregion Tigray
ምስል Ethiopian News Agency/AP/picture alliance

ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ መቃረባቸውን ዐስታውቀዋል

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በድል ለማጠናቀቅ መቃረባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ። ከጦር ግንባሩ ሆነው በተንቀሳቃሽ ምስል መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደራዊ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው የተባለውን የሰሜን ወሎ ዞን ተራራማው ስፍራ ጋሸናን በአጠረ ጊዜ እንደሚቆጣጠሩትም ዐስታውቀዋል። በመሆኑም ጠላት ያሉት የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታጣቂዎች መሣሪያ ፈተው እጅ እንዲሰጡ አስጠንቅቀዋልም። በተመሳሳይ የሕወሓት  ጦር የተቆጣጠራቸው የአማራ ክልል አከባቢዎች በመከበቡ ነዋሪዎች ታጣቂዎችን ይዘው ለፀጥታ አካላት እንዲያስረክቡ አሊያም ርምጃ ወስደውበት እንዲታጠቁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ትዕዛዝ አስተላልፏል። 

የመንግስት ኃላፊነታቸውን ለምክትላቸው አስረክበው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘውን ጦርነት በግምባር መምራት ከጀመሩ ዛሬ አንደኛ ሳምንታቸውን የደፈኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወታደራዊ ኃይላቸው ለድል መቃረቡን ነው ዛሬ ከጦር ግንባሩ ባስተላለፉት መልእክት ዐስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መልእክታቸው ጠላት ያሉት የሕወሓት ሰራዊት ያለ እቅድ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ዘልቆ መግባቱን ተችተው፤ በርካታ ሰብዓዊ ጥሰቶችን በመፈጸምም ከሰውታል።

የጦር ሰራዊታቸው ለድል ለማድረግ መቃረቡን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለተቀናቃኛቸው የእጅ ስጡ ማስጠንቀቂያንም አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰርትሩ በዚሁ መልእክታቸው በርካታ ያሉት የትግራይ ወጣቶች በጦርነቱ ሕይወቱን እንዳጣም አመልክተዋል። መንግስታቸው ወደ ጦርነቱ የገባ ተገዶ መሆኑንም ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመንግስታቸው ቀዳሚ ዓላማ ሰላምን መሻትና ልማትን ማስቀጠል መሆኑንም በዚሁ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና በሰሜን ወሎ አካባቢዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች ብሎ ዛሬ ባስተላለፈው ተመሳሳይ መልእክት፤ ጠላት ያለው የሕወሓት ታጣቂዎች መሸነፋቸውን ገልጾ፤ ወይ ይማረካል፤ ወይ ርምጃ ይወሰድበታል ሲል የማስጠንቀቂያውን መልእክት አሰራጭቷል።

ዕዙ ለታጣቂዎቹ ባስተላለፈው መልእክት መሣሪያን በማውረድ ለመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እጅ እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡ ይህን ለሚያደርጉ ሕዝቡ እንክብካቤ እንዲያደርግ እና ለጸጥታ አካላቱ እንዲሰጥ ብሏል ዕዙ፡፡ ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ለሚደርሰው ጉዳት መንግስት ኃላፊነቱን እንደማይወስድ ነው ዕዙ ለታጣቂዎች ያስተላለፈው ማስጠንቀቂያ መልእክት ያሳየው። 
በአከባቢዎቹ የሚገኙ ነዋሪዎች መኪናዎቹ እንዳያልፉ መንገዱን በሙሉ በድንጋይና በግንድ እንዲዘጉ የጦር መሳሪያዎችንም እንዲማርኩ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዙ በዛሬው መግለጫው አውስቷል።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ