1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠ/ሚው የምክር ቤት ገለጻና የሕዝብ አስተያየት

ሐሙስ፣ ሰኔ 30 2014

ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ሰኔ 30 2014 ዓ. ም በምክር ቤት ቀርበው ከ 18 የምክር ቤቱ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ምላሽ እንዲሰጡባቸው ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል። በተለይ ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ የተደጋገመውን በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመ ግድያ አስመልክተው በተነሱት ጥያቄዎች መንግሥት እንዲህ ያለውን ጥቃት ማስቆም ለምን ተሳነው? የሚለው ይጎላል።

https://p.dw.com/p/4DpAl
Äthiopien, Addis Abeba | Äthiopisches Parlament
ምስል Solomon Muchie/DW

የጠ/ሚው የምክር ቤት ገለጻ

325 የምክር ቤቱ አባላት በተገኙበት 16ኛው መደበኛ ጉባኤ ላይ ከተነሰት ጥያቄዎች መካከል የአገሪቱ ሰላምና ፀጥታን የተመለከቱት ሰፋ ያለውን ጊዜ የወሰዱ ናቸው። ምክር ቤቱ በአሸባሪነት የፈረጀው ኦነግ ሸኔ በተደጋጋሚ የሚፈጽማቸው የሽብር ጥቃቶች መሠረታዊ መነሻቸው ምንድን ነው? መንግሥት ይህን ዘር ተኮር ጥቃት ማስቆም ያልቻለውስ ለምንድነው? ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን ለየት ያለ ስልት መከተል ያስፈልጋል? የሽብር ቡድኑ እስከመቼ ድረስ የአገሪቱ ሥጋት ሆኖ ይቀጥላይ? የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል። ለዚህም መንግሥት መከላከል፣ መከታተል፣ መጠበቅ እና መዘጋጀት በተባሉ ጉዳዮች ላይ ዘለቄታ ያለው መፍትሔ ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
በወለጋ ማንነታቸው ተለይቶ ለተጨፈጨፉ አማራዎች ማዘናቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዜጎችን ለመታደግ የፀጥታ አካላት ጭምር በየዕለቱ እየሞቱ መሆኑን፣ ድርጊቱም ሽብር እንደሆነና ያም የኢትዮጵያ ችግር ብቻ አለመሆኑን ለማስረዳት ጥረዋል። የመንግሥት መዋቅር በጥቃቶች ውስጥ አለበት ለሚለው ሲመልሱም መንግሥታቸው አሸባሪን ለማጥፋት የሚሰራ እንጂ አሸባሪ አለመሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በሌሎች የውጭ ኃይሎች በመረጃ ፣ በተልእኮ ፣ በዲፕሎማሲ እና በሳይበር የተደገፈ ግራጫ ያሉት ጦርነት ተከፍቶባታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን በዚህ ሂደት ኢትዮጵያን ማፍረስ እንዳልቻሉ እና ቀጣዩ ሂደታቸው በቀጥታ ኃይል አስገብተው የመውጋት ልምድ ያላቸው መሆኑን ለምክር ቤቱ አባላት ጠቅሰዋል። ጅምላ ጭፍጨፋዎች የሚፈፀሙባቸው አካባቢዎችን የሚመሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ እርምጃ ለምን አይወሰድም ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ እርምጃ በፕሮፖጋንዳ አንወስድም ብለዋል። ግድያን ለማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጡ ሰዎች በግፍ ስለመገደላቸውም ተጠይቀው ነበር ። በዚህም በተለይ በሰሜን ሸዋ 12 ሰዎች ለተቃውሞ ወጥተው መገደላቸው ተጠቅሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰልፈኞች መከልከል ዙሪያ ተጨማሪ ጥፋትን ለመከላከል በማሰብ ለዜጎች ደህንነት ሲባል የሚወሰድ እርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል። ከሕወሓት ጋር የሚደረግ ድርድርን በተመለከት መንግሥት ብቻውን ወሳኝ የመሆኑ ተገቢነት ላይም ጥያቄ ቀርቦ ነበር። እሳቸው የሰላም መንገድን ማየቱ እድል ሊሰጠው ይገባል የሚል ምላሽ ሰጥተውበታል።
የሽግግር ማንግሥት ጥያቄ የሚያቀርቡ ወገኖች መኖራቸው ተጠቅሶ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥያቄው በንጉሡም ፣ በደርግም ፣ በኢሕአዳግም አሁንም የሚጠየቅ መሆኑን፣ ነገር ግን ብዙም ጆሮ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ አድርገው መልሰዋል። ሕገ መንግሥት ሕግን ተከትሎ እንደሚሻሻልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ከነገ ጀምሮ እረፍት የሚወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ 2015 ዓ. ም በመንግሥት የቀረበውን 786.61 ቢሊዮን ብር በጀት በአራት ድምፅ ታቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል።
ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ወቅታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህም በኢትዮጵያ እየደረሰ ላለው የጅምላ ጭፍጨፋዎች «ከውጪ ኃይላት ፍሪፋሪ የሚለቃቅሙ ያሏቸውን» ተጠያቂ በማድረግ ኅብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በዚሁ ላይ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ሥዩም ጌቱ ከነዋሪዎች አስተያየት አሰባስቧል። አስተያየታቸውን ያጋሩት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነቱ የሆነውን የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ሚናውን ከምንም በላይ ቅድሚያ እንዲሰጥ ነው የጠየቁት።

Äthiopien, Addis Abeba | Äthiopisches Parlament
ምስል Solomon Muchie/DW

ሰሎሞን ሙጩ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍት ስለሺ