1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከህዝብ እይታ መጥፋት፤የኢትዮጵያ የሱዳን የድንበር ውዝግብ

ዓርብ፣ ጥር 21 2013

የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለሳምንታት ከህዝብ እይታ ጠፉ ተብሎ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ስለደኅንነታቸው የተሰራጨው መረጃ ከሰሞኑ አነጋጋሪ ጉዳዮች አንዱ ነበር።ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በድንበር ጉዳይ የምትደራደረው ሱዳን የወረረችውን መሬት ለቃ ስትወጣ ነው ማለቷም እንዲሁ በማኅበራዊ መገናኛዘዴዎች ልዩ ልዩ አስተያየቶች ተንሸራሽረውበታል።

https://p.dw.com/p/3oZ8p
Äthiopien Abiy Ahmed
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማኅበራዊ መገናኛዎች መልዕክቶቻቸውን ከማስተላለፍ ውጭ ለሳምንታት ከህዝብ እይታ ከጠፉ በኋላ ፣ዐቢይ አንድም ታመዋል አለያም አደጋ ተጥሎባቸዋል የሚሉ የተለያዩ መረጃዎችን የፖለቲካ አራማጆች ወይም አክቲቪስቶች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲቀባበሉ ሰንብተዋል።የማኅበራዊ መገናኛዎች ተጠቃሚዎችም በነዚህ መረጃዎች ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል። ከአስተያየቶቹ አብዛኛዎቹ ጽንፍ የያዙና ዘለፋዎች የሚያመዝኑባቸው በመሆናቸው ጥቂቱን  መርጠናል።
ማሬ ቦጋለ በፌስቡክ « ሠው ነውና፡እረፍት፡ላይ ነው እንዳንላቸው እረፍት አልባ መሪ ነው፡፡ ስራ ላይ ነው፡፡ ተቸገረ እኮ የሆነ ቦታ፡ለሥራ ጉብኝ ት ከሔደ ፎቶ ሊነሳ ትሉታላችሁ ዝም ብሎ ስራውን ከሠራ ደሞ ሞቶ ነው ወይ ታሞ ነው ፍልስፍና ይወራበታል።ውይ የቻለው ጉድ፤ ብለዋል።
ስናፍቅሽ ከበደ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ደግሞ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጠ/ሚ አብይ አደጋ ደርሶባቸው ቢሆን በተለያዩ ክልላት በመሄድ የስገነቧቸውን ት/ቤት ባላስመረቁ ነበር ይላል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የብልጽግና ፓርቲ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን የወጡትን መረጃዎች ሃሰት በማለት በማኅበራዊ መገናኛ ገጾቻቸው  አስተባብለዋል።የጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕመድ ቢሮ  በፌስቡክ  ገጹ ባወጣው አጭር መግለጫ "የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ደህንነት አስመልክቶ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ የሀሰት እንደ ሆነ ሁሉም ሰው እንዲገነዘብ ለማሳሰብ እንወዳለን" ብሏል
ብልጽግና ፓርቲም  የዶክተር ዐቢይ አህመድን "ጤንነትና ደህንነት አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ የተናፈሰው ወሬ ፍጹም መሰረተ ቢስና ሆን ተብሎ ህብረተሰቡን ለማደናገር" የተሰራጨ የሐሰት መረጃ ነው ብሏል።የሃሰት ወሬዎችን የሚያሰራጩትንም መንግሥት በጥብቅ ተከታትሎ ተጠያቂ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለበትም አስታውቋል
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትም እነዚህ ያልተረጋገጡ የተባሉ መረጃዎች በማኅበራዊ መገናኛዎች ከተሰራጩ በኋላ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን የሚያሰራጩ ላላቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ህብረተሰቡን ለማደናገር የሚሞክሩ ያላቸው የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች ከሕገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መሥሪያ ቤቱ አሳስቧል።ከዚህ በኋላ የሀሰት መረጃዎችንና አሉባልታዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች በማሰራጨት የሀገርን ብሄራዊ ጥቅምና ህልውና ለመጉዳት እንዲሁም የህዝብን ሰላምና ደህንነት ስጋት ላይ ለመጣል የሚንቀሳቀሱ ያላቸው አካላት ላይ ማስረጃዎችን በማጠናቀር በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግም አስታውቋል።
ብሩክ አበበ በዚህ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መግለጫ ላይ «ከዚህ በኋላ» መባሉን ተቃውመዋል።  
«ከዚህ በኋላ የሚሉት  አይገባኝም።ተቋሙ ተቋም ሆኖ በሕግ ስራ ከጀመረበት ቀን ጀምሮ ማንንም ተጠያቂ የማድረግ ሙሉ ሥልጣን አለው ፤ሰው እየተመረጠ ነው ከዚህ በኋላ የሚባለው ነገም የነሱ ሰው ሲሆን ከዚህ በኋላ ነው?በማለት ቅሬታቸውን በፌስቡክ ገልጸዋል።
ዮናስ ይትባረክ ደግሞ «የሚገርመው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስሙ ጠፋ ብለው መመሪያ ያወጣሉ።ህዝቦችስ ስማቸው ሲጠፋ ማነው ተጠያቂው ሲሉ ይጠይቃሉ።
«እውነት ነው ትክክለኛ ያልሆነ የሀሰት መረጃ ሀገርን ሊጎዳ ይችላል» በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት ምስክር ለማ ድንቁ ነገር ግን በማለት ይቀጥላሉ «ነገር ግን ወደ ህዝብ በመቅረብ ለህዝብ እውነታውን በማስረዳት ታማኝነትን በመገንባት የሀሰት መረጃዎችን ማምከን ያለበት መንግሥት ነው።እኛ ሀገር ከመንግሥት ይልቅ እንደየብሄራችን ውክልና አክቲቪስት የሚታመንበት ብዙ አጋጣሚ አለ።  ምክንያቱ ህዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት መሸርሸር ነው።በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል። 
ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሁኔታ ከታማኝ ምንጮች መረጃ አግኝተናል ብለው በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን ከጻፉት መካከል አክቲቪስት ስዩም ተሾመ በፌስቡክ ገጹ እንዲህ ሲል ይቅርታ ጠይቋል። 
«ስለ ጠ/ሚ አብይ አህመድ የተባለ ነገር በሙሉ ውሸትና የተሳሳተ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም ዓይነት የአካል ጉዳት ሆነ የጤና እክል አልገጠመውም። በመደበኛ ስራ ላይ ያለና እዚሁ አዲስ አበባ ቤተመንግሥት ውስጥ መኖሩን እኔ በራሴ አረጋግጬያለሁ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመንግስት ሃላፊ በስልክ  "በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ምንም አይነት የአካል ሆነ የጤና መታወክ ችግር አልተከሰተም" ብለውኛል። በመሆኑም ተሳስቼ ስላሳሳትኳችሁ፣ ለመጥፎ ስሜት እና ስጋት ለዳረኳችሁ ተከታዮቼ በሙሉ ከልብ የመነጨ ይቅርታ ለመጠየቅ እወዳለሁ» ብሏል ስዩም 
ከህዝብ እይታ ለሳምንታት ጠፍተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ትናንት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘውን የሰው ሰራሽ አካል እና የአካል ድጋፍ ማደራጃ ድርጅትን ተዘዋውረው ሲገበኙ ታይተዋል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በምትወዛገብበት ድንበር ጉዳይ ላይ የምትደራደረው፣የሱዳን ጦር ኃይል ድንበር አልፎ የወረረውን መሬት ሲለቅ ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዚህ ሳምንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ኢትዮጵያ አሁንም ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ናት። ሆኖም ለመደራደር እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠችው፣ ሱዳን ወደ ቀድሞው ይዞታዋ እንድትመለስ ነው።በዚህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ላይ ጥያቄዎችን ጨምሮ በማኅበራዊ መገኛ ዘዴዎች  ልዩ ልዩ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል። 
ኤልያስ ሀበሻ በፌስቡክ «ከሱዳን ጋር ጦርነት ላለማድረግ የሚደረገውን ጥረት አደንቃለው ምክንያቱም ጦርነቱ ቢጀመር የኢትዮጵያ እና የሱዳን ብቻ አይሆንም ብዙ ሀገሮች መሳተፋቸው አይቀርም ግን ከሁሉም ሀገራዊ የውስጥ ችግራችንን ከፈታን ማንም ቢመጣ አያቅተንም» ሲሉ ፍሬው ጥላሁን መግለጫው ትክክለኛ ነው ሱዳን፣ መንግሥት ትኩረቱን ወደ ሌላ ባደረገበት ጊዜ ክህደት በመፈጸም የኢትዮጵያን መሬት ሉዓላዊነታችንን ደፍራለች ወደ ነበረችበት ሳትመለስ ድርድር የለም።»በማለት መግለጫውን ደግፈዋል። 
የኢጂ ጥቁር ሰው አስተያየት ደግሞ ከዚህ ይለያል «የልምምጥ ፖለቲካችሁ ለወያኔና ለሸኔ ጉልበት ሰጥቶ እንዳፈረጠማቸውና ሀገሪቷንም ለምን ዓይነት ችግር እንደዳረጋት ግልጽ ሆኖ ሳለ አሁንም ወሰን ጥሶ የገባን ባዕድ መለማመጥ ላይ ናችሁ።ጠላትን በስሙ መጥራት ያስፈልጋል።ወራሪ መባል አለበት።የኢትዮጵያ ህዝብም እንዴት መቅጣት እንዳለበት ያውቃል።ሲሉ የተለሳለሰ የመሰላቸውን የኢትዮጵያ አቋም ነቅፈዋል። 
ሰሎሞን አዲሴ ደግሞ ጥያቄ ነው ያስቀደሙት?ድንበሩን በሰላም አለቅም ካለችስ? በኃይል እናስለቅቃለን እንበል………! በኃይል በመስዋዕትነት ከለቀቀች በኋላስ ተደራደሩ ብንባል ወይም እሷ እንደራደር ካለች ልንደራደር ነው? ባድመ ላይ የሆነው አይሁን………!ባድመን ልቀቂና እንደራደር አልን እቢኝ አለች……!! በኃይል አስለቅቀን ለመደራደር ቁጭ አልን ከድርድር በኋላ ባድመን ሰጠን!!! ይሄ ነው የሆነው።በማለት አስተያየታቸው አጠቃለዋል 

Tigray-Konflikt | Äthiopien PK Regierungssprecher Dina Mufti
ምስል Solomon Muchie/DW
Symbolbild Apps Facebook und Google Anwendungen
ምስል picture-alliance/dpa/S. Stache

ሳሙኤል  ሳሙኤል በሚል የፌስቡክ ስም ጥያቄ ቀርቧል፤ አዎ ጦርነት መልካም አይደለም ግን እነሱ ከፈለጉስ? የሚል ፤የኛስሰው  በፌስቡክ በተባለ አድራሻም «እስካለቀቁ ድረስ አንደራደርም? የጊዜ ገደብ አለው ወይስ እንደያዙት ይኑሩ ነው? በማለት ጠይቋል።
ጌታ አደም በበኩላቸው ችግሩን ያለጦርነት መፍታት ለሁለቱም ሃገራት ትልቅ ጥቅም አለው።ኢትዮጵያና ሱዳን አዳጊ ሃገራት ስለሆኑ ችግራቸውን በድርድር ከመፍታት ውጭ  ሌላ አማራጭ የላቸውም።ከጦርነት ይልቅ መሠረተ ልማት ነው የሚያስፈልገን።ግብብጽ ናት ሱዳንን የምትገፋፋው።ብለዋል።
ኂሩት መለሰ 

አዜብ ታደሰ