1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 10 ቀን 2014 ዓም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሰኔ 10 2014

üሰላም በአንድ ወገን ስለተፈለገም አይመጣም፤ድርድር "የሚባለውቋንቋ ሰው ከመገበሩ በፊት ቢሆን ያስማማን ነበር፤ አሁን ግን ከቁጥር በላይ የሚሆን ጀግና ሰውተናል።እነዚህን ጀግኖች እንደ ንግድ ኪሳራ አናስባቸውም፤ ለደማቸው ተጠያቂ የሆነ አካል መገኘት አለበት።»

https://p.dw.com/p/4CpQu
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed im Parlament
ምስል Solomon Muche/DW

የዐርብ ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡት መልስ ፣ባገባደድነው ሳምንት በጋምቤላ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት፣ እንዲሁም የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ለዶቼቬለ የሰጡት ቃለ ምልልልስ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተጻፉ አስተያየቶችን ከሞላ ጎደል እንቃኛለን።  
ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓም በተካሄደው የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።  በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣በኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ፣በተለያዩ የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ፣ በተፈናቃዮች ፣ በሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ጋዜጠኞችና ማኅበራዊ አንቂዎችን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ከመካከላቸው በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ህወሓት ጋር ድርድር ጀምሯል ስለመባሉ የሰጡት መልስ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ትኩረት ከሳቡት ውስጥ አንዱ ነው። ዐቢይ  ከህወሓት ጋር የሚካሄደውን ጦርነት መንግሥታቸው በድርድር ለማብቃት እንደሚፈልግ ለምክርቤቱ አስረድተዋል።የተለያዩ ቦታዎችና አገራት እየተጠቀሱ በመንግሥትና በህወሓት መካከል ድርድር እየተደረገ ነው ተብለው የሚወጡ ዘገባዎችን ያስተባበሉት ዐቢይ ከህዝብ የተደበቀ ድርድር አናደርግም ብለዋል። ድርድሩን የሚያስተባብር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙንም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥታቸው ከህወሓት ጋር ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው ባሳወቁበት በዚህ ሳምንት ህወሓትም «ታማኝ፣ያልወገነና በመርሕ ላይ በተመረሰተ የሰላም ሒደት» ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ይፋ አድርጓል።በዚህ ጉዳይ ላይ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች የተለያዩ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል። 
 ገዛኽኝ መገርሳ በፌስቡክ «ከዚ በላይ መሸወድ የለብንም ለሁሉም ለአገሬ እዝብ የሚበጀው ይሄ ነው። ኪሳራውንንማ በሚገባ አየነው እኮ ለሁላችንም የሚበጀን ሰላም ሰላም ሰላም ብቻ ነው ወገኖቼ።»ብለዋል። የሞተው ወንድምሽ ነው። የገደለው አባትሽ ነው። ለሠላማችን ስንል ድርድር ግድ ይላል።» የሚለው ደግሞ የጥላሁን ጳውሎስ አስተያየት ነው ። ኤስ ቢ ስማርት በሚል የፌስቡክ ስም እንዲሁ «ዕርቅ፡ጥሩ፡ነዉ፡ለሰላም፡ለጤና፡ለፍቅር፡መታረቅ፡ያስፈልጋል»ይላል። 
«በተደጋጋሚ ስንማጸንና ስንሰደብበት የከረመው ሰላምና ድርድር ይደረግ የሚለው ጥያቄአችን እጅግ ዘግይቶም ቢሆን በቅርቡ ሊፈጸም መሆኑን ስንሰማ ደስ ብሎናል»የሚለው ደግሞ «ልይ ልዩ አዳዲስ ሀሳቦች» በሚል ስም ከትዊተር የተገኘ አስተያየት ነው። ቀጣዩ የከበደ መንጂ አስተያየት ደግሞ ከቀደሙት ይለያል። 
« ሰላም በአንድ ወገን ስለተፈለገም አይመጣም፤ንግድ ጀምረህ ብትከስር ድካምህንና ገንዘብህን ነው የከሰርከው ሰርተህ ልታገኘው ትችላለህ። "ድርድር "የሚባለውቋንቋ ሰው ከመገበሩ በፊት ቢሆን ያስማማን ነበር፤ አሁን ግን ከቁጥር በላይ የሚሆን ጀግና ሰውተናል።እነዚህን ጀግኖች እንደ ንግድ ኪሳራ አናስባቸውም፤ስለሆነም ለደማቸው ተጠያቂ የሆነ አካል መገኘት አለበት። ይላል።
በትዊተር «ድርድር ለሁሉም ወገን መልካም ነው። ሁሉም ምክክር ለህዝብ ይገለጽ አይባልም።ግን ድርድር መደረጉንና ከድርድር በኋላ ችግር ሊመጣ ስለሚችል ህዝቡ እንዲዘጋ ጅማድረግ ነው። ሲሉ በትዊተር ምክራቸው ያስተላለፉት ደግሞ ያረጋል ተስፋዮ ናቸው።በዚሁ በትዊተር አብራር ሱሌይማን መንግሥት ሁሉን ሚስጥር ይንገረን የምል አይደለሁም። ጦርነቱ በሰላም ማለቁን፣የኢትዮጵያ ህዝብ ይፈልጋል ድርድር መደረግ ካለበት ግን ህወሓት ትጥቅ መፍታት አለበት የአማራ አፋርና የኤርትራን ህዝብ ማካተት አለበት ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለዋል። 
ሀገር ወዳዱ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ደግሞ ስጋት አካቷል።«ትግራይ እና አብይ ሰላም ፈጥረዋል ማለት ይችላል ያለቀ ጉዳይ ነው አሁን ችግሩ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሌላ ጦርነት እዳይፈጥሩ ነው መፍራት የሚል። «ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ግን ድርድሩ ለአንዳቸው ድል ለአንዳች ሽንፈት ነው ያም ሆኖ ከተሳካ ህዋሓት እያለና በአንድ ሀገር ሁለት መከላከያ እያለ ለዛውም ድጋሚ ለጦርነት እየተዘጋጁ ብቻ አላህ ሰላሞን ያምጣልን ድጋሚ ጦርነት አንፈልግም» ያሉት ደግሞ ኡም ፈራሀን ናቸው በፌስቡክ።ዮናስ በርሀ ጦርነት አስፈላጊ አልነበረም ግን በመሃል የሞቱት ወጣቶች ተጎዱ ይላል።

በዚህ ሳምንት ታጣቂዎችና የጋምቤላ ነጻነት ግምባር ጋነግ ጋምቤላ ከተማ ውስጥ የፈጸሙት ጥቃት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትኩረት ከሳቡት ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር። በዚሁ ማክሰኞ በተፈጸመው ጥቃት ከመንግሥትም ከታጣቂዎችም በአጠቃላይ የ37 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የክልሉ መንግስት አስታውቋል። በእለቱ ጥቃት አድራሾቹ የከተማይቱን የተወሰነ ክፍል ቶቆጣጥረው እንደነበረ ትናንት ተናግሯል። 
ስለ ጋምቤላው ጥቃት በማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። አብዛኛዎቹ ግን ስሜታዊነትና ጥላቻ የሚያመዝንባቸው በመሆናቸው ልናቀርባቸው አልቻልንም። ጥቂት የተሻሉ የሚባሉትን መርጠናል። 
ሳንጆ ካሳ በፌስቡክ «ለመሆኑ የሐገራችን ሕዝብ ሁሉም አበደ ማለት ነው?ሲሉ ጠይቀው« ገዳይስ ሟችስ ማነው ካልን ሁለቱም ወንድማማቾች ናቸው»
በማለት ትዝብታቸውን አስፍረዋል። «ያሳዝናል መሀል ከተማ አስኪገቡ ድረስ የፀጥታ መዋቅሩ እንቅልፍ ላይ ነበር ማለት ነው ? የሚል ጥያቄ የቀረበው ደግሞ «ባህርዳር ነው ቤቴ» በሚል የፌስቡክ አድራሻ ነው።ወርቅነህ ጌትየ ከቡልጋሪያ ማዞሪያ 
ደግሞ መንግስት ባለበት ሀገር የሀገሬ ገበሬ አርሶ ባበላን ምን በወጣው ባበዱ ቡድኖች ይሙት ይላል። ዳንኤል ማሞ  ኢትዮጵያ 
ማንም ዋና ከተማ ድረስ እየገባ የሚፈነጭባት ሀገር ሆነች?ሲሉ አማረዋል።
የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እንዳለው በማክሰኞው ጥቃት ከመንግሥት በኩል  በኩል 11 የፀጥታ አባላት ህይወታቸው አልፏል፣ 42 ደግሞ ቆስላዋል፣ ከቆሰሉት መካከል 3ቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ናቸው፡፡የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ የታጣቂው 26 አባላት ተገድለዋል ብለዋል።
የጋምቤላ መንግሥት ፣ በጥቃቱ ምክንያት በከተማይቱ ስራ ያቋረጡ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ቀስ በቀስ ስራ እየጀመሩ መሆናቸውን ትናንት ተናግሯል።

ከተቋቋመ ሦስት ወር ስለሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ክንውኖች እንዲሁም ለወቅታዊው የሀገሪቱ ችግሮች ስላለው ፋይዳ  ዶቼቬለ በዚህ ሳምንት ከኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዶ ነበር። የኮሚሽኑ ትልቁ ግብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደረስ ማስቻል መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን በቃለ ምልልሱ ተናግረዋል።በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ በፌስቡክ አስተያየት ከሰጡት አንዱ ወንድሙ ታረቀኝ ኮሚሽነሩን አመስግነዋል።«ክቡር ፕሮፈሰር መስፍን አርአያ ለዶቸቬለዋ ለሰጡት ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን ሲሉ። አቶ ገሞራ ደግሞ በሀገራችን ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ ፕሮፌሰሩን በእንግድነት መጋበዛችሁ ለሀገራችንም ለታዳሚዎቻችሁም የምትሰጡት ቅድሚያ እንደሆነ ማረጋገጫ ነዉ እናመሠግናለን !! ብለውናል እኛም እናመሰግናለን። ዜና ደስታ ደግሞ አጭር ሃሳብ ሰጥተዋል። «በምክክሩ ሁሉንም ማሳተፍ ማካተት ያስፈልጋል» ሲሉ። 
«ሠላም በሀገራችን የሚሰፍነው ሁሉም ነፍጡን ዘቅዝቆ በሠላም  የመደራደር መንገድ ሲሄድ ብቻ ነው አለበለዚያ ሀገራችን ግልፅ አደጋ ዉስጥ ገብታለች፤የሚለው ማሳሰቢያ  «የሐርላዎች ልጅ ነኝ»በሚል የፌስቡክ ስም የተጻፈ ሃሳብ ነው።  «የያሬድ ማኅበረሰብ ድምጽ» በፌስቡክ  «ሰላም በሌለበት ስለ ብሄራዊ እርቅ ማሰብ በጣም ከባድ ነው፤ካሉ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአይዶሎጂ ልዩነት አይደለም ። ኢትዮጵያ እንድትፈርስ በሚፈልጉ ኃይሎች እና ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል በሚፈልጉ ወገኖች መሀከል ያለ ልዩነት ነው። ይህንን እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው? ሲሉ ጠይቀዋል።

Äthiopien Parlament Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW
Äthiopien | Chef von Gambella Omod Ojulu
ምስል Gambella Communication
Äthiopien Konflikt in Tigray | Debretsion Gebremichael
ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ