1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 16 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 16 2013

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ሳዲዮ ማኔ ሊቨርፑልን ከጭንቀት ታድጎ ለሻምፒዮንስ ሊግ አብቅቷል። በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ የጌርድ ሙይለርን የግብ ብዛት ክብረወሰን ሰብሮ 42 ግቦችን አስቆጥሯል። ከወራጅ ቀጠናው የወጣው ኮሎኝ በቡንደስሊጋው ለመቆየት የደርሶ መልስ ግጥሚያ ይጠብቀዋል።

https://p.dw.com/p/3tszW
Fußball Bundesliga | FC Bayern München vs. FC Augsburg | Robert Lewandowksi
ምስል Christof Stache/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ሳዲዮ ማኔ ሊቨርፑልን ከጭንቀት ታድጎ ለሻምፒዮንስ ሊግ አብቅቷል። በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ የጌርድ ሙይለርን የግብ ብዛት ክብረወሰን ሰብሮ 42 ግቦችን አስቆጥሯል። ከወራጅ ቀጠናው የወጣው ኮሎኝ በቡንደስሊጋው ለመቆየት የደርሶ መልስ ግጥሚያ ይጠብቀዋል።  በስፔን ላሊጋ የዋንጫ ባለድሉ አትሌቲኮ ማድሪድ ፌሽታ ታዳጊ ወጣት ደጋፊ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጧል። በፈረንሳይ ሊግ ፓሪ ሳን ጃርሞን በአንድ ነጥብ የበለጠው ሊል ለመጀመሪያ ጊዜ የፈረንሳይ ሊግ ኧ ዋንጫን አንስቷል። በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ የዘንድሮ ግጥሚያ ፋሲል ከነማ ዋንጫውን ተረክቧል። ፈረንሳይ ሞናኮ ውስጥ በተከናወነው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ማክስ ፈርሽታፐን ለመጀመሪያ ጊዜ በነጥብ መምራት ችሏል። የሰባት ጊዜያት አሸናፊ ብሪታኒያዊው ሌዊስ ሐሚልተን በአራት ነጥብ ይበለጣል። አብራችሁን ቆዩ!

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የላይስተር ሲቲ እና የቸልሲ ያልተጠበቀ ሽንፈት ለሊቨርፑል ሲሳይ ኾኗል። ብዙዎች ዘንድሮ በአምስተኛ ደረጃ በማጠናቀቅ ለሚቀጥለው የሻምፒዮንስ ሊግ ሊሳተፍ አይችልም ያሉት ሊቨርፑል በሦስተኛ ደረጃ አጠናቋል።  ትናንት ሊቨርፑል በሳዲዮ ማኔ ሁለት ግቦች ክሪስታል ፓላስን 2 ለ0 ድል በማድረግ ነጥቡን 69 አድርሶ ደረጃውን ወደ ሦስተኛ ከፍ በማድረግ ታላቅ እመርታ አስመዝግቧል።

Premier League Flagge
ምስል Richard Heathcote/empics/picture alliance

ሦስተኛ ደረጃ ላይ የነበረው ቸልሲ በአስቶን ቪላ በደረሰበት የ2 ለ1 ሽንፈት ወደ አራተኛ ደረጃ ተንሸራትቶ ቦታውን ለሊቨርፑል አስረክቧል። ከዚህ ቀደምምም አስቶን ቪላ ቸልሲን 1 ለ0 ማሸነፉ አይዘነጋም። 67 ነጥብ ይዞ በአራተኛ ደረጃ በማጠናቀቁ ግን ለቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ማለፉን አረጋግጧል።  በቶትንሀም 4 ለ2 የተሸነፈው ላይስተር ሲቲ 66 ነጥብ ይዞ አምስተኛ ኾኗል። በአንድ ነጥብ ዝቅ ካለው ዌስት ሀም ጋር የአውሮጳ ሊግ ቦታን ይዟል። እስከ 36ኛው ዙር ድረስ የሦስተኛ ደረጃ የሻምፒዮንስ ሊግ ሥፍራውን አስጠብቆ የቆየው ላይስተር ሲቲ በስተመጨረሻ ወደ አውሮጳ ሊግ መንሸራረተቱ ለደጋፊዎቹ እጅግ የሚያስቆጭ ነው። በመጨረሻዎቹ ሁለት ዙር ግጥሚያዎች ከአምስተኛ ደረጃ ወደ ሦስተኛ ከፍ ብለው የሻምፒዮንስ ሊግ ሥፍራን ለነጠቁት ሊቨርፑል ደጋፊዎች ግን ፌሽታ። ቶትንሀም ሆትስፐር ለአውሮጳ ኮንፈረንስ ሊግ ሲያልፍ፤ ፉልሃም፣ ዌስት ብሮሚች እና ሼፊልድ ዩናይትድ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ተሰናብተዋል።

ኖርዊች ሲቲ እና ዋትፎርድ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ፕሬሚየር ሊጉን ተቀላቅለዋል። ሦስተኛ ኾኖ የጨረሰው ብሬንትፎርድ ከስዋንሲቲ የፊታችን ቅዳሜ ዌምብሌይ ስታዲየም ውስጥ ወደ ፕሬሚየ ርሊጉ ለማለፍ ወሳኝ ግጥሚያ ይጠብቃቸዋል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቅዳሜ ዕለት ሲጠናቀቅ የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አንጋፋ ተጨዋች ሉቃስ ፒስቼክ ከቡድኑ ተሰናብቶ ጫማውን ሰቅሏል። ጄሮም ቦኣቴንግ፣ ዳቪድ አላባ እና ጃቪ ማርቲኔዝም ከጨዋታው በፊት እና በኋላ በሐዘን እና በእንባ ተውጠው ተጨዋቾች እና ደጋፊዎችን ተሰናብተዋል። ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ጄሮም ቦአቴንግ የቡድኑ አባላትን ተራ በተራ ተሰናበተ። ወደ አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ሲያቀና ግን ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት አንብቷል። አሰልጣኙ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ጄሮም ቦኣቴንግ ሊመለስ እንደሚችል ተስፋ ማድረጋቸውን ኋላ ላይ ተናግረዋል።

በመሰናበቻ ግጥሚያቸውም ባየርን ሙይንሽን አውግስቡርግን 5 ለ2 ድል አድርጓል። ነጥቡንም 78 አድርሶ በአንደኛነት ዋንጫውን ተረክቧል። ላይፕትሲሽ 65 ነጥብ ይዞ የዘንድሮ ቡንደስሊጋ የመጨረሻ እና 34ኛ ግጥሚያ አጠናቋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ64 ነጥብ፣ ቮልፍስቡርግ 61 ነጥብ ሰብስቦ በቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነታቸውን አረጋግጠዋል። ከቮልፍስቡርግ በአንድ ነጥብ ብቻ ተብልጦ ያጠናቀቀው አይንትራኅት ፍራንክፉርት እና 52 ነጥብ የሰበሰበው ባየርን ሌቨርኩሰን ለአውሮጳ ሊግ የምድብ ውድድር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

Fussball Bundesliga l 33. Spieltag l Hertha BSC vs 1. FC Köln
ምስል Soeren Stache/dpa/picture alliance

ቅዳሜ ዕለት ሻልከን 1 ለ0 ያሸነፈው ኮሎኝ ከወራጅ ቀጣናው ወጥቶ በ16ኛነት አጠናቋል። በቀጣይ የውድድር ዘመን በቡንደስሊጋው ለመቀጠል ግን በኹለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ኾኖ ከጨረሰው ሆልሽታይን ኪይል ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ይጠብቀዋል። ብሬመን እና ሻልከ ከቡንደስሊጋው ተሰናብተው ወደ ሁለተኛ ደረጃ አሽቆልቁለዋል። በሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚገኙት ቦኹም እና ግሮኅቴር ፍዩርት ወደ ቡንደስሊጋው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

ዴቪድ አላባ ወደ ሪያል ማድሪድ ለማቅናት መወሰኑ አደጋ ቢኖረውም ትክክለኛ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል። በሪያል ማድሪድ የ35 ዓመቱ ወሳኙ ተከላካይ ሠርጂዮ ራሞስ ይጠብቀዋል። ራሞስ በሪያል ማድሪድ ተጨማሪ ዓመት ከቆየ ዴቪድ አላባ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጦ ተቀያሪ መኾኑ የማይቀር ነው።

የስፔን ብሔራዊ ቡድን ለአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ሠርጂዮ ራሞስን አሰናብቶ በምትኩ የማንቸቸስተር ሲቲው አይመሪክ ላፖርቴን ጠርቷል። ለስፔን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለ180 ጊዜያት የተሰለፈው ሠርጂዮ ራሞስ በብሔራዊ ቡድኑ ሳይካተት የቀረው ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ሠርጂዮ ራሞስ ከስፔን ቡድን ጋር የዓለም ዋንጫን ማንሳት ችሏል። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቡድኑ ለድል ሲበቃም አብሮ በፌሽታ ጮቤ ረግጧል። ዘንድሮ ሉዊ ኤንሪኬ ሠርጂዮ ራሞስን በቡድኑ ያላካተቱት በደረሰበት ጉዳት ለማገገም ትግል ላይ በመኾኑ ነው። ሠርጂዮ ራሞስ ለብሔራዊ ቡድኑ ለመድረስ በእየቀኑ በአካልም በመንፈስም ጥረት ቢያደርግም እንዳሰበው እንዳልሆነለት የትዊተር ይፋዊ መገናኛ አውታሩ ላይ ጽፏል። ዘንድሮ በስፔን ብሔራዊ ቡድን አንድም የሪያል ማድሪድ ተጨዋች የለም።

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ 38ኛ እና የመጨረሻ ዙር ግጥሚያ ቫላዶሊድን ቅዳሜ ዕለት 2 ለ1 የረታው አትሌቲኮ ማድሪድ ዋንጫውን አንስቷል። ሪያል ማድሪድ ቪላሪያልን በተመሳሳይ 2 ለ1 ማሸነፍ ቢችልም በ2 ነጥብ ተበልጦ በሁለተኛነት ለማጠናቀቅ ተገዷል። በ84 ነጥብ ነው ያጠናቀቀው። ቅዳሜ ዕለት ያለ ሊዮኔል ሜሲ የተሰለፈው ባርሴሎና በበኩሉ በአንቷን ግሪንዝማን ብቸኛ ግብ ወራጅ የኾነው አይበርን 1 ለ0 በማሸነፍ 79 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። የቡድኑ አምበል እና ኮከብ ተጨዋች ሊዮኔል ሜሲ ቀደም ብሎ የዓመት ረፍቱን እንዲወስድ አሰልጣኝ ሮናልድ ኮይማን በመወሰናቸው ሳይሰለፍ ቀርቷል።  አራተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ሴቪያን ጨምሮ አራት ቡድኖች ለሻምፒዮንስ ሊግ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ሳን ሰባስቲያን እና ቤቲስ ለአውሮጳ ሊግ አልፈዋል። በ7ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ቪላሪያል ለአውሮጳ ኮንፈረንስ ሊግ ማለፉን አረጋግጧል። ሆዌይስካ፣ ቫላዶሊድ እና በ20ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው አይባር ከላሊጋው ተሰናብተዋል።

Lionel Messi
ምስል Imago Images/ZUMA Wire/E. Alonso

በስፔን ላሊጋ የዘንድሮ ዋንጫን ማንሳት የቻለው አትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊዎች በፌሽታ በተዋጡበት ወቅት አሳዛኝ ነገርም ተከስቷል። የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት የአትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊ ጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት አደጋ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጧል። ታዳጊው ወጣት ከኔፕቱንብሩነን ብዙም ባልራቀ አንድ ጋራጅ ውስጥ ጭንቅላቱን በመኪና መስኮት ብቅ አድርጎ በደረሰበት አደጋ ከአንድ ሰአት በኋላ ሕይወቱ አልፋለች።

ሊግ ኧ

በፈረንሳይ ሊግ ኧ ሊል ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ችሏል። የዘንድሮ 38ኛ ዙር የሊጉ ግጥሚያ ሲጠናቀቅ ሊል ከፓሪ ሳን ጃርሞ የበለጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። ሊል ትናንት አንጌርን 2 ለ1 አሸንፎ ነጥቡን 83 በማድረሱም ነው ለዋንጫ ድል የበቃው። ከሌን ጋር ያለ ግብ የተለያየው እና በሊጉ ሦስተኛ ኾኖ የጨረሰው ሞናኮ የሻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ ቦታውን ወስዷል። በሜዳው ተጫውቶ በኒስ የ3 ለ2 ሽንፈት የገጠመው ሊዮ እንዲሁም በሜትዝ 1 ለ0 የተረታው ማርሴ አራተኛ እና አምስተኛ በመሆን ለአውሮጳ ሊግ አልፈዋል። ኒም እና ጂዮን ከሊጉ ለመውረድ ተገደዋል።

ፎርሙላ አንድ

Formel 1 Monaco Grand Prix | Max Verstappen
ምስል Eric Gaillard/REUTERS

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ማክስ ፈርሽታፐን ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንሳይ ሞናኮ ግራንድ ፕሪ ፉክክር አሸናፊ ኾኗል። ማክስ ውድድሩን ሲጀምር በፎርሙላ አንድ የሰባት ጊዜያት ባለድል የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን በ14 ነጥብ ተበልጦ ነበር። በውድድሩ ያገኘው ድል ከሐሚልተን በአራት ነጥብ ለመብለጥ አስችሎታል። በዚህም የ23 ዓመቱ ሆላንዳዊ የሬድ ቡል አሽከርካሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም መሪ መኾን ችሏል።  ሰባስቲያን ፌትል በአምስተኛ ደረጃ አጠናቋል። የፌራሪው አሽከርካሪ ካርሎ ሳይንዝ 2ኛ፣ ሌላኛው የማክላረን አሽከርካሪ ላንዶ ኖሪስ 3ኛ ኾኖ አጠናቋል። ላንዶ ለጥቂት ነው የሁለተኛ ደረጃውን የተነጠቀው። የአራተኛ ደረጃውን ያገኘው ሌላኛው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ሠርጂዮ ፔሬዝ ነው። ሌዊስ ሐሚልተን የሆንዳው አሽከርካሪ ፒዬር ጋስሌይን ተከትሎ በ7ኛ ደረጃ አጠናቋል።

እስካሁን በተደረጉ አጠቃላይ ውድድሮችም ብሪታኒያዊው ሌዊስ ሐሚልተን የመሪነቱን ስፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ አስረክቧል። 105 ነጥቦችን በሰበሰበው ማክስ ፈርሽታፐን በአራት ነጥብ ይበለጣል።  የማክላረኑ ኖሪስ በ56 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ