1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅ ዉሎ

ሐሙስ፣ የካቲት 3 2003

የካይሮዉ ተሕሪር ወይም የነፃነት-አደባባይ ዛሬም እንደ መሰንበቻዉ መብት ነፃነቱን በሚጠይቀዉ የግብፅ ሕዝብ እንደተጨናነቀ ነዉ።የአሌክሳንዴሪያ፥ የስዌዝና የሌሎችም ትላልቅ ከተሞች አዉራ ጎዳኖች የሙባረክ ተቃዋሚች ይርመሰመሱባቸዋል

https://p.dw.com/p/QzkW
አሌክሳንደሪያምስል AP

የፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባራክ አገዛዝ፥ ሙስና፥ ሥራ አጥነት፥የኑሮ ዉድነት ያስመረረዉ የግብፅ ሕዝብ የአደባባይ ሠልፍ እና አመፅ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።ከተለመደዉ የአደባባይ ሠልፍ በተጨማሪ የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤት ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መትተዋል።ግብፃዊ የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አምር ሙሳ የግብፁ ሕዝባዊ አመፅ የአረቡን አለም እየቀየረዉ ነዉ ሲሉ ዩናይትድ ስቴትስ በፋንታዋ በፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክ ላይ የምታደርገዉን ግፊት አጠናክራለች።የሙባረክ ባለሥልጣናት ግን የዉጪዉንም ሆነ የሕዝቡን ግፊት እስካሁን አልተቀበሉትም።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።

የካይሮዉ ተሕሪር ወይም የነፃነት-አደባባይ ዛሬም እንደ መሰንበቻዉ መብት ነፃነቱን በሚጠይቀዉ የግብፅ ሕዝብ እንደተጨናነቀ ነዉ።የአሌክሳንዴሪያ፥ የስዌዝና የሌሎችም ትላልቅ ከተሞች አዉራ ጎዳኖች የሙባረክ ተቃዋሚች ይርመሰመሱባቸዋል።ከወንዶቹ ይልቅ የሴቶቹ ጥንካሬ ፅናት አረብን-አጃኢብ ዓለምን ጉድ እያሰኘ ነዉ።«እሱ (ሙባረክ) መሔድ አለበት» ይላሉ እነሱ «እኛ አንሔድም።»

የአደባባዩ አመፅ-ሠልፍ አስራ-ሰባተኛ ቀኑን ሲደፍን ዛሬ የካይሮዉ ትልቅ የሕክምና ማዕከል የቃስር አል-አይኒ ሐኪሞችና ሠራተኞች ሥራቸዉን አቋርጠዉ ከሠልፈኛዉ ባሕር ተቀይጠዋል። ሰወስት ሺሕ ናቸዉ።

የአዉቶቡስ፥ የታክሲ እና የሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ሾፌሮች ሥራ በማቆማቸዉ የግል አዉቶሞቢል ለሌለዉ መላወሻዉ-እግር፥ ግመል፥ጋሪ-ፈረስ ሆኗል።በርግጥም የአረብ-አፍሪቃዊቱ ሐገር ሕዝብ አመፅ፥ ሠልፍ፥ አድማ አረብን አጃኢብ እያሰኘ ነዉ።የቀድሞዉ የግብፅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እና ያሁኑ የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አምር ሙሳም መሰከሩ።

«የአረቡ አለም በለዉጥ ሒደት፥ በለዉጥ ስሜት ነዉ።የለዉጡ ሒደት-ስሜት በርግጥ የተለያየ ደረጃ ያለዉ፥ ትርጓሜዉም የተለያየ ነዉ።ግን ባጠቀላይ እና የመጨረሻ መጨረሻ የዚሕን ሠልፍ ዉጤት ሁሉም የሚጋራ፥ የሚሰማዉ ለዉጥ ነዉ።እነደነገርኩሕ ለግብፅ ታላቅ ታሪካዊ ለዉጥ ነዉ።ለግብፅ ብቻ በሐገራት ታሪክ ታላቅ እዉነታ ነዉ።የሕዝብና በሕዝብ የተደረገ አመፅ ነዉ።በዚሕ የዓለም ክፍል አዲስ ነዉ።ከዚሕ በፊት በተወሰኑ ሐገራት ተደርጎ ይሆናል ግን በዚሕ መጠን አልነበረም»

NO FLASH Revolution in Ägypten
ምስል picture alliance/dpa

የአረቡን አለም የሚንጠዉ የሙባረክን ጠንካራ-ሥልጣን የሚገዘግዘዉ ሕዝባዊ አመፅ-አድማ ባሕር ዉቅያኖስ ተሻግሮ የዋሽንግተን መሪዎችንም አቋም እያስለወጠ ነዉ።ድፍን ሠላሳ አመት ለሙባረክ ሥርዓት ፅናት ዙሪያ መለስ ድጋፍ ስትሰጥ የቆየችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ሙባረክ ሥልጣን እንዲለቁ እስካሁን በግልፅ መናገሩን አልፈቀደችም።

የዋይት ሐዉሱ ቃል አቀባይ ሮበርት ጊቢስ ትናንት እንዳሉት ግን ዩናይትድ ስቴትስ ዘላቂ ጥቅሟ ከሚያጣጥረዉ የሙባረክ ሥርዓት ጋር ወደ መቀባር እንዲወርድ አለመፈለጓን በግልፅ ጠቋሚ ነዉ።

ይሕ ሙባረክና ተከታዮቻቸዉን ከሁለት ያጣ አይነት ነዉ-ያደረገዉ።የተቀጣጠለዉን ሕዝባዊ አመፅ እንዲያለዝቡ ሙባረክ ከሁለት ሳምንት በፊት የምክትል ፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን የሾሟቸዉ የቀድሞ የጦር ጄኔራል፥ የረጅም ጊዜዉ የስለላ ድርጅት ሐላፊ ዑመር ሱሌይማን በአሜሪካኖች አስተያየት ክፉኛ ተበሳጭተዋል።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ከሳቸዉም ብሰዋል።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አሕመድ አቡ ጋይት አሜሪካኖችን «የራሳቸዉን ፊላጎት በሌላዉ ላይ መጫን አይገባም አሉ።»

ጋይት የሕዝቡና የዉጪዉ ግፊት በዚሑ ከቀጠለ ጦር ሐይሉ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ እንደሚገደድም አስጠንቅቀዋል።

Ägypten Vizepräsident Omar Suleiman
ም/ዑመር ሱሌይማንምስል picture-alliance/dpa

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ