1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግሉ ወረት እና አፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 24 2011

የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በአፍሪቃ ወረታቸውን ለሚያሰሩ የጀርመን ኩባንያዎች ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ሜርክል ይህን ያሉት በበርሊን 11 አፍሪቃ ሀገራት መሪዎች፣ ዓ/አቀፍ ድርጅቶችና የተቋማት ኃላፊዎች በተሳተፉበት የአፍሪቃን ልማት ለማሳደግ በተካሄደው የቡድን 20 የጀርመን ንግድና ከአፍሪቃ ጋር አጋርነት ጉባዔ ላይ ነበር።

https://p.dw.com/p/37aa6
Afrika-Verein der deutschen Wirtschaft
ምስል picture-alliance/dpa/L. Schulze

የግሉ ወረት እና አፍሪቃ

የጀርመን አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማህበር ያዘጋጀው ጉባዔ ጀርመን የቡድን 20 ፕሬዚደንት በነበረችበት ባለፈው ዓመት በተነቃቃው ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ በተሰኘው መርሀግብር አማካኝነት በአፍሪቃ የግል ወረት ስምሪትን የማበረታታት  ዓላማ የያዘ ነው። 
ለወትሮው የጀርመን የአፍሪቃ ፖሊሲን አጥብቀው የሚነቅፉት የጀርመን የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ማህበር፣ ዶይች አፍሪቃ ፈርአይን ሊቀ መንበር ሽቴፋን ሊቢንግ  በጉባዔው የሰሙትን የመራሒተ መንግሥቷን ቃል አሞግሰዋል፣  የሀገራቸው መንግሥት ለኩባንያዎቹ  ንዑሱን ድጋፍ  ነው ያደረገው በሚል ሲወቅሱ የነበሩት ከ500 የሚበልጡ በአፍሪቃ የሚንቀሳቀሱ የጀርመን ኩባንያዎች የተጠቃለሉበት የዚሁ ማህበር ሊቀ መንበር ይህ ከብዙ ጊዜ ወዲህ ከመንግሥታቸው ሲጠብቁት የነበረው ርምጃ አሁን እውን ከጀርመን የወረቱን ፍሰት ሊያበረታታ እንደሚችል ገልጸዋል።ማህበሩ ካዘጋጀው ስልታዊ ጽሁፍ የተወሰደ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
« መካከለኛ ኩባንያዎችን  ለመደገፍ የሚያስችል፣ ታሪካዊ የሚባል አዲስ የድጎማ መርሀግብር ይፋ ማድረግ የሚያስችለንን ሁኔታ እንደፈጠርን አምናለሁ። ይህን እውን ለማድረግ የሚያስፈልገውን መሰረት ጥለናል።»
ሜርክል በበርሊኑ ጉባዔ የገቡት ቃል ስለአህጉሩ ልማት እና እድገት ወደፊት ከአፍሪቃውያን ጋር መነጋገሩ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
«  ከአፍሪቃ ጋር ጥሩ እና ትርፋማ ጉርብትና መፍጠር ለኛ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ዛሬ ግልጽ ምልክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን። ጎረቤቶች ነን፣ አጋሮች ነን፣ እና እኛ አውሮጳውያን የአፍሪቃ ሀገራት ጥሩ ኤኮኖሚያዊ እድል እንዲኖራቸው ትልቅ ፍላጎት አለን።  ይህ የመንግሥታት ወረትን፣ ከሁሉም በላይ ግን የግሉ ወረት አስፈላጊ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ለኛ ስለ አፍሪቃ  መናገሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከአፍሪቃውያኑ ጋር በቀጥታ መነጋገሩ ወሳኝ የሆነው። ይህ ነው ያን ያህል ውጤት ካላስገኘው የልማት ርዳታ አቅርቦት የወሰድነው ትምህርት። ለዚህም ነው አሁን በቀጥታ የምናነጋግራችሁ። » 
በዚሁ የሜርክል ቃል መሰረት የጀርመን መንግሥት አነስተኛ እና መካከለኛ ኩባንያዎች በአፍሪቃ ወረታቸውን የሚያሰሩበትን ሁኔታ ለማቃለል የሚረዳ አንድ ቢልዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ ወስኗል። 
« ከዚህ በተጨማሪ ለኩባንያዎቹ የተሻለ ዋስትና ለማረጋገጥ እና ለወጣት አፍሪቃውያንም ስልጠና  ለመስጠት ታስቧል። ከዚህ በተረፈ መሰረት ኩባንያዎች ሁለት ጊዜ ቀረጥ እንዳይከፍሉ በጀርመን እና በኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ መርሀ ግብር በተጠቃለሉ አፍሪቃውያት ሀገራት፣ ማለትም፣ ቤኒን፣ ኮት ዲቯር፣ ግብፅ፣  ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ርዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ፣ ቶጎ፣ ቡርኪና ፋሶ መካከል የቀረጥ አከፋፈል ስምምነት ተደርሷል። 
በጉባዔው የተሳተፉት አፍሪቃውያን መሪዎች ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃካ መር,ግብርን ያሞገሱ ሲሆን፣ የርዋንዳ ፕሬዚደንት እና የወቅቱ የአፍሪቃ ህብረት ፖል ካጋሜ  መራሒተ መንግሥት  ውጤት እንዲያስገኝ የጀመሩትን ጥረት አድንቀዋል። በኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ የተከተቱት 11 አፍሪቃውያት ሀገራት ኤኮኖሚ ተሀድሶ ለማነቃቃት ግዴታ መግባታቸውን እና በዚሁ መሰረት ለውጤት መብቃታቸውን ካጋሜ አክለው ገልጸዋል።
« በፊናንሱ እና ተቋማዊ ተሀድሶ የተነሳ የአፍሪቃ ህብረት ለቀጣዩ በጀቱ 12 ከመቶ ቁጠባ አድርጓል፣ በዚህ ላይ አባል ሀገራት ያበረከቱት  አስተዋፅዖ ትልቅ ነው። ሰዎች በነፃ መዘዋወር የሚችሉበትን፣ እንዲሁም፣ አፍሪቃን አንድ የንግድ አካል የሚያደርግ ፣ በምህጻሩ ሲ ኤፍ ቲ ኤ የተባለውን አህጉር አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጠና እውን ማድረግ የሚያስችሉ ስምምነቶችን ተፈራርመናል። »
ምዕራባውያን አጋሮችም ባለተቋማት አፍሪቃ ውስጥ እንዲወርቱ ቴክኒካዊ ተሞክሮ ልውውጥ እና ርዳታ በመስጠት የሚያደርጉት ትብብር ለአህጉሩ ተጠቃሚ እንደሚሆንም የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ ተናግረዋል።
« በአፍሪቃ እና በቡድን 20 መካከል ስለተፈጠረው አጋርነት ጥቂት ለማለት አጋጣሚውን በማግኘቴ አመሰግናለሁ። ይህ አጋርነት ዛሬ እዚህ በተገኙ መሪዎች የተወከሉትን ዜጎች ህይወት እና የተቋማትን ንግድ ለመለወጥ ትልቅ አጋጣሚ የያዘ ነው። »
በጉባዔው የተሳተፉት ጀርመናውያን የተቋማት ኃላፊዎችም  አፍሪቃ እንደ ገበያ የያዘችውን ትርጓሜ  በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ አስታውቀው፣ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ወረት ለማፍሰስ ስምምነት ተፈራርመዋል።  ባጠቃላይ ጉባዔው ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ውጤታማ መሆኑን ግልጽ መልዕክት ለማስ,ተላለፍ የታሰበ ነበር። ገሀዱ ግን ይህን መልዕክት የሚያንጸባርቅ ሆኖ አልተገኘም። እርግጥ፣ በኮምፓክት የተጠቃለሉት ሀገራት ተሀድሶ ቢያነቃቁም፣ በአገሮቻቸው የፈሰሰው የውጭ ወረት ይህ ነው የሚባል እድገት አላስገነም። በአፍሪቃ ገንዘባቸውን የሚያሰሩት የጀርመን ኩባንያዎችም ቁጥር ያን ያህል ጭማሪ እንዳላሳየ እና መርሀግብሩ ውጤታማ መሆን አለመሆኑ ወደፊት እንደሚለይ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ይስማማሉ። 
የጀርመን መንግሥት አሁን የወሰደው አዲሱ ርምጃ በርግጥ ድህነትን ከአፍሪቃ ማጥፋት መቻሉን ጠበብቱ ጥርጣሬ አላቸው፣ ርምጃው ከውረታ ጋር አብረው ሊያያዙ የሚገባቸውን የመብት፣ አስተዳደር እና አካባቢ ጥበቃን ያላገናዘበ ነው ሲሉ ዋን የተባለው የልማት ድርጅት ሊቀ መንበር ሽቴፋን ኤክሶ ክሪኸር ቅሬታቸውን ገልጸዋል። 
« « የግሉ ወረት፣ የውጭው ብቻ ሳይሆን  የሀገር ውስጥም፣  በጣም አስፈላጊ እና ትክክለኛ ነው።  ይህ ወረት በአህጉሩ ዘላቂ እድገት እና ለህዝቦቹም ጥቅም የሚያስገኝ መሆን እንዳለበት ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። የወረትን ፍሰት ለማሳደግም አመቺውን  ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር፣  የአካባቢ ጥበቃን፣ የሰብዓዊ መብትን እና መልካም አስተዳደርን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አሰራር ያስፈልጋል። በኔ አስተያየት ግን ይህ ሁሉ ተጓድሎ ነው የሚገኘው። »
የልማት ድርጅቶች በኮምፓክት ውስጥ 11 አፍሪቃውያት ሀገራት ብቻ መጠቃለላቸውን በማመልከት ፣ ድሆች ሀገራት ወረት ሊያሰሩ ለሚችሉ ባለተቋማት ያን ያህል የማያጓጉ በመሆናቸው ከመርሀ ሀግብሩ መገለላቸውን ነቅፈዋል። 
የአፍሪቃ ጀርመን የኤኮኖሚ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ክርስቶፍ ካንንጊሰር ፣ ጉባዔው ለአፍሪቃ ጀርመን የኤኮኖሚ ማህበር የተዋጣ ነበር ቢሉም፣ ጅምሩ መልካም ቢሆንም መርሀግብሩ ፈጣን ስኬት ያስገኛል ተብሎ እንደማይጠበቅ አመልክተዋል።
«አህጉሩ የያዘው እድል ላይ ማትኮር ይገባናል። የሚታዩት ችግሮች፣ በተለይ የጀርመን መንግሥት ጠንካራ ድጋፍ ሲያደርግ እና  ሊፈጠር የሚችልን ክስረትንም በከፊል ለመቀበል ዝግጁ ሲሆን፣ ሊቀረፉ የሚችሉ ናቸው።  ይህ ስኬታማ ለሆኑት እና ከብዙ ዓመታት ወዲህ አዳዲስ ገበያ በመፈለግ ላይ ላሉት ለጀርመናውያኑ መካከለኛ ኩባንያዎች ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል ብየ አምናለሁ። ስለዚህ ወረት ለማፍሰስ የሚያስችል ማሻሻያ ከማድረግ ባለፈ ፣ ስለጥቅሙ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ማስታወቂያ ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል።»  

Deutschland Afrika-Gipfel bei Bundeskanzlerin Angela Merkel
ምስል Reuters/A. Schmidt
"Compact with Africa"-Konferenz in Berlin
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka
Ruanda VW eröffnet Werk
ምስል Getty Images/AFP/C. Ndegeya

አርያም ተክሌ/ዳንየል ፔልስ

ተስፋለም ወልደየስ