1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የጋዛ መዘዝ፣ የመን ሶስተኛ ግንባር መሆንዋ ይሆን?

ሰኞ፣ ጥር 6 2016

የዋሆች ይጠይቃሉ፤ የአሜሪካና የብሪታንያ ጦር መካከለኛዉ ምሥራቅ ምን ያደርጋል? እያሉ።ሌሎች ደግሞ የዚሕ ሁሉ ምስቅልቅል ምክንያት ኢራን ከሆነች ቴሕራንን በቀጥታ ከመግጠም ይልቅ ሊባኖስ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ጋዛ፣ ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ሕዝብ የሚያልቅ፣ የሚሸበር፣የሚሰደድበት ተጠየቃዊ ምክንያት ማግኘት ግራ ይሆንባቸዋል።

https://p.dw.com/p/4bHNY
ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ጥቃት ከመከላከል አልፈዉ የመንን ደብድበዋል
የየመን ሁቲዎችን ጥቃት ለመከላከል ተብሎ ቀይ ባሕር ላይ የሰፈረዉ የአሜሪካ ባሕር-ኃይልምስል U.S. Navy/abaca/picture alliance

የጋዛ መዘዝ፣ የመን የሶስተኛ ግንባር ኢላማ መሆኗ ይሆን?

ደቡባዊ እስራኤል ለሰዓታት ከተጠቃኝ፣ጋዛ መንደድ ከጀመረች አንድ-መቶ ቀን አለፈ።የጋዛ ዉድመት፣ የፍልስጤም ሕዝብ እልቂትና ስቃይ መዘዝ ሌላ ግጭትና ጦርነት እንዳያስከተል ብዙዎች ደጋግመዉ ጠይቀዉ ነበር።ምክር ማስጠንቀቂያዉ ሰሚ አጥቶ ሒዝቦላሕን ከሊባኖስ፣ሁቲዎችን ከየመን፣ ሌሎች አማፂያንን ከኢራቅ ጎትቶ ከግጭቱ ዶሏል።

ለእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ሙሉ ድጋፍ የሚሰጡት ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ለእልቂት ፍጅቱ እልባት ከመስጠት ይልቅ ባለፈዉ ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ የመንን መደብደብ ጀምረዋል።ድብደባዉ፣ የአፀፋ ዛቻ፣ ዉግዘትና ቅሬታዉ የተፈራዉ ለመድረሱ ማረጋገጪያ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የኢራን ጠላትነት፣ የቬትናም አብነት

ዩናይትድ ስቴትስ ከ1950ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ እስከ 1975 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የተማገደችበት የቬትናም ጦርነት እንዲቆም የሚጠይቁ፣ አንዳዴም አሜሪካን የሚያወግዙ ወገኖች የምዕራብ አዉሮጳና የራስዋን የዩናይትድ ስቴትስን ትላልቅ ከተሞች በሰልፍ በሚያጥለቀለቁበት በዚያ ዘመን የዋይት ሐዉስ ባለስልጣናትና ደጋፊዎቸዉ «የምንዋጋዉ ኮሚንስቶችን ለማዳከም ነዉ»ይሉ ነበር-አሉ የፃፉ።

ለአሜሪካ መሪዎችና ለደጋፊዎቻቸዉ መልስ ተጠየቃዊ ምክንያት ያጡለት ተንታኞች «ዉጊያዉ ኮሚንስቶችን ለማጥፋት ከሆነ ዋናዋ ኮሚንስት ሶቭየት ሕብረት አዉሮጳ አናት ላይ ተቀምጣ እስያ ድረስ ምን አዘመተን እያሉ ይሳለቁ ገቡ።

ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራና የምታስተባብራቸዉ መንግስታትና ደጋፊዎቻቸዉ እንደሚሉት የሶሪያ መንግስትን፣ የፍልስጤሙን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስን፣ ደቡባዊ ሊባኖስ ዉስጥ የሸመቀዉን ሒዝቦላሕን፣ አብዛኛ የመንን የሚቆጣጠረዉን አንሳር አላሕን (ሁቲን)ና ኢራቅ ዉስጥ የሸመቁ አማፂያንን የምታስታጥቅና የምትረዳዉ ኢራን ናት።

ታጋቾቹን ለማስለቀቅና ሐማስን ለማጥፋት የእስራኤል ጦር ጋዛ ላይ የከፈተዉ ዘመቻ 100 ቀን አለፈዉ
ሐማስ ያገታቸዉን ሰዎች ዘመድ ወዳጆች ታጋቶቹ እንዲለቀቁ ባደባባይ ሰልፍ ሲጠይቁምስል Gonzalo Feuntes/REUTERS

የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩበት ዘመን ሊቢያን በግንባር ቀደምትነት ከወረሩት አንዱ የነበሩት ዴቪድ ካሜሩን አሁን እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የምስቅልቅሉ ሁሉ ምንጭ ኢራን ናት በማለት ብዙ ጊዜ የተባለዉን በቀደም ደገሙት።

«ደሕና፣ የአካባቢዉ የጥፋት ተዋኝ፣ ከነዚሕ ተላላኪ ቡድናት ጀርባ ያለችዉ ኢራን መሆንዋ ምንም አያጠራጥርም።ኢራን ሐማስን ትደግፋለች፣ሒዝቦላሕን፣ ሑቲዎችን ይደግፋሉ።ጦር መሳሪያ ያስታጥቋቸዋል።ኢራቅ ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ፣ የብሪታንያና የአሜሪካ የጦር ሠፈሮችንና ወታደሮችን የሚያጠቁ ታጣቂ ቡድናትንንም ይደግፋሉ።ሥለዚሕ እነሱ (ኢራኖች) ይሕን እንደሚያደርጉ እናዉቃለን።» 

የዋሆች ይጠይቃሉ፤ የአሜሪካና የብሪታንያ ጦር ኢራቅ፣ ቀይ ባሕር ወይም መካከለኛዉ ምሥራቅ ምን ያደርጋል? እያሉ።ሌሎች ደግሞ የዚሕ ሁሉ ምስቅልቅል ምክንያት ኢራን ከሆነች ቴሕራንን በቀጥታ ከመግጠም ይልቅ ሊባኖስ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ጋዛ፣ ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በየዘመኑ ሕዝብ የሚያልቅ፣ የሚሸበር፣የሚሰደድበት ተጠየቃዊ ምክንያት ማግኘት እንደ ቬትናሙ ዘመን ሁሉ በርግጥ ግራ ይሆንባቸዋል።

የ3 ወር ከሁለት ሳምንቱ ድብደባና ዉጤቱ

እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተከታዮቻቸዉ ባሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ ባለፈዉ መስከረም 26 ደቡባዊ እስራኤልን አጥቅቶ 1140 የእስራኤልና የሌሎች ሐገራት ዜጎችን መግደሉን የእስራኤል ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።

የዩናትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባደን ቴል አቪቭን በጎበኙበት ወቅት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ጋር
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንና የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁምስል Avi Ohayon/Israel GpoI/Zuma/MAGO

ሐማስ ካገታቸዉ ሰዎች  130 ያክሉ እስካሁን አልተለቀቁም።የፍልስጤሙ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ጋዛን የከበበዉን የእስራኤልን የግንብ አጥር፣እንቅስቃሴ ጠቋሚ መሳሪያና ጦር ኃይል ጥሶ ደቡባዊ እስራኤልን መዉረር የቻለበት ምክንያት ለአብዛኛዉ ሰዉ እስካሁን ሚስጥር ነዉ።
የእስራኤል መሪዎችም «ሐማስን ማጥፋት» ባሉት የብቀላ ዘመቻ የጋዛን ሕዝብ በእሕል ዉኃ-መድሐኒት እቀባ ከማሰቃየት፣ በቦምብ-ሚሳዬል ከመፍጀት ሌላ ሐማስ ግዛታቸዉን ደፍሮ ያደረሰዉን ጥፋት እስኪያደርስ ስለወሰዱት ርምጃ በዝርዝርና በግልፅ ያስረዱት ነገር የለም።

የፍልስጤም ባለስልጣናት እንዳስታወቁት የእስራኤል ጦር ጋዛን መደብደብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞች፣ጋዜጠኞች፣ ሐኪሞች፣የአምቡላስ ሰራተኞች፣ ሕፃናት፣ሴቶች፣አዛዉንቶች አልቀዋል።ከ24 ሺሕ በላይ።ወደ ስልሳ ሺሕ ቆስሏል።ከሞት፟ የተረፈዉ ከ2.2 ሚሊዮን የሚበልጥ ፍልስጤማዊ ቢያንስ አንድ ጊዜ ተፈናቅሏል።

ሶስት ወር ከሁለት ሳምንቱ።ታጋቾቹ አልተፈቱም።ሐማስም አልጠፋም።የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ግን እሁንም ይፎክራሉ።እልቂት ፍጅቱ ሌላ ብልሐት እንዲፈለግለት የሚጠይቁ ወገኖችን ደግሞ ኔታንያሁ የቴሌቪዝን አስተያየት ሰጪዎች በማለት ተሳለቁባቸዉ።

«ድል እስከምናደርግ ድረስ እንቀጥላለን።ምክንያቱም ሌላ ምርጫ የለንም አስተያየት ሰጪዎች በቴሌቪዥን አይቻልም፤ አስፈላጊ አይደለም ሲሉ እሰማለሁ።እናንተ እንደምትሉት ሁሉ-እኔ የምለዉ ይቻላል፣ እናደርገዋለን ነዉ።»

የእስራኤል ጦር ሐማስን ማዉደም ከጀመረ 100 ቀናት አለፈዉ።ታጋቾች አልተለቀቁም፤ ሐማስ አልጠፋም ሕዝብ ግን አልቋል
ጋዛ ወድማለች።ሕዝቧ እያለቀ፣ እየተራበ እየተሰደደም ነዉ 100 ቀናት ምስል Fatima Shbair/AP Photo/picture alliance

የሁቲዎች ጥቃትና የየመን አበሳ

እስራኤል በጋዛ ሕዝብ ላይ የምትፈፅመዉን ግፍ ካላቆመች ቀይ ባሕርን አቋርጠዉ ከና ወደ እስራኤል የሚቀዝፉ መርከቦችን እንደሚያጠቁ በተደጋጋሚ ያስጠነቀቁት የየመን ሁቲዎች ካለፈዉ ሕዳር አጋማሽ ጀምሮ በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ መርከቦችን ማጥቃት ጀምረዋል።ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራና የምታስተባብራቸዉ 10 መንግስታት የሁቲዎችን ጥቃት ለመከላከል ዘመቻ-ብልፅግና ያሉትን የጋራ ግንባር መሥርተዋል።

ዋና ማዘዢያዉን ባሕሬን ላደረገዉ ጦር መርከብና ወታደር ካዋጡት ሐገራት አንዳዶቹ ዘመቻዉ ጥቃትን ከመከላከል እንዳያላፍ ሲያስጠነቅቁ ነበር።የኢጣሊያዉ መከላከያ ሚንስትር ጉይዶ ክሮሴቶ ባለፈዉ ሳምንት አጋማሽ ላይ የሁቲዎች ጥቃት «ሶስተኛ ግንባር» ያሉትን ጦርነት ሳይጭር መቆም አለበት ብለዉ ነበር። 

የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ መሪዎች ግን የሩቁን ታዛቢ ማስጠንቀቂያ አይደለም የቅርብ ወዳጆቻቸዉን ምክርም አልሰሙም።አንግሎ-አሜሪካኖች ያዘመቱት ጦር ባለፈዉ ሐሙስ-ለአርብ አጥቢያ የየመንን ሉዓሉዊ ግዛት ጥሰዉ ሰነዓን፣ታኢዝን፣ ሁዴይዳሕና ሌሎች የየመን ትላልቅ ከተሞችና ወደቦችን ደበደቡ።ምን አደርግናቸዉ ይላል-የዋሁ ዳቦ ጋጋሪ የመናዊ።

«ይሕ ዓለም አቀፍ ወንጀል ነዉ።ጥቃቱ፣ ከበባዉ፣ በየመን ላይ የተከፈተዉ ጦርነት።ለምንድነዉ ይህን የሚያደርጉት።»

ባለፈዉ ሐሙስ-ለአርብ አጥቢያ የመንን የወረረዉ የአንጎሎ-አሜሪካን ጦር ኃይል ካደረሰዉ ጥፋት አንዱ-ሁዴይዳሕ
የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ጦር ኃይላት ከደበደቡት አካባቢ አንዱ-ሁዴይዳሕ በከፊልምስል /Maxar Technologies/AP/dpa/picture alliance

በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ መርከቦችን ደሕንነት ያስጠብቃል ለተባለዉ ዘመቻ መርከብና የባሕር ጦር ካዋጡት ሐገራት የፈረንሳይ፣ የኢጣሊያና የስጳኝ ጦር ኃይላት በጥቃቱ አልተካፈሉም።ሮይተርስ ዜና አገልግሎች እንደዘገበዉ ሶስቱ መንግስታት ስለአርቡ ጥቃት የተረቀቀዉን የጋራ መግለጫም አልፈረሙም።የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መስተዳድርና የምዕራብ አዉሮጳ ተባባሪዎቹ ዘለዉ የተመሰጉበት የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ዩክሬንን እንዳጠፋ፣ ሕዝቧን እንዳሰደደ-ቀሪዉን እንዳሸማቀቀ ሁለተኛ ዓመቱን ሊደፍን  ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል።

ምዕራባዉያን መንግስታት በጋዛዉ እልቂት ከዲፕሎማሲዉ ዘመቻ- ጦር መሳሪያ እስከማቀበል፣ ከፍርድ ቤቱ ሙግት እስከ ፖለቲካዊ መድረክ ለእስራኤል ሁለንተናዊ ድጋፍ እየሰጡ ነዉ።አሁን ደግሞ የዋሽግተን-ለንደን ተሻራኪዎች የመንን መደብደባቸዉ የኢጣሊያዉ መከላከያ ሚንስትር እንዳሉት ሌላ ሶስተኛ የጦርነት ግንባር መክፈት እንዳይሆን ብዙዎችን አስግቷል።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ግን ጦራቸዉ የመንን መደብደቡ ይቀጥላል ባይ ናቸዉ። «ሁቲዎች ይሕን መጥፎ ባሕሪያቸዉን ካላቆሙ፣ ከተባባሪዎቻችን ጋር አፀፋ መስጠታችንን እንደምንቀጥል እናረጋግጣለን።»

አብዱል መሊክ አል-ሁቲ የሚመሩት የሁቲ ቡድን አብዛኛዉን የመንን ይቆጣጠራል።ቡድኑ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ከተራ ክላሺንኮቭ ታጣቂነት ወደ ሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) ባለቤትነት፣ ተዋጊዎቹ ከሰነደል ጫማ አጥላቂነት ወደ ሔሊኮብተር አብራሪነት ተቀይረዋል።በዩናይትድ ስቴትስና በብሪታንያ የሚረዱትን የሳዑዲ አረቢያ፣የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣የግብፅ፣ የዮርዳኖስ፣ የሞሮኮ፣ የሱዳንና የሌሎች መንግስታትና ቡድናትን ጦር ጥቃት ለስምት ዓመት መክቶ መልሷል።

የየመን ሁቲዎች የአንግሎ አሜሪካኖችን ጥቃት ይበቀላሉ-ጄኔራል ያሕያ ሳሬኢ
የየመን ሁቲዎች ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ብርጌድየር ጄኔራል ያሕዛ ሳሬኢምስል DW

የሁቲ የጦር ኃይል ቃል አቀባይ ጄኔራል ያሕያ ሳራኢ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት ቡድናቸዉ የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ጦር ኃይላት በየመን ላይ ያደረሱትን ጥቃት ይበቀላል።
የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ጦር ኃይላት የመንን መደብደባቸዉን የሁለቱ ሐገራት የቅርብ ታማኞች የሚባሉት ሳዑዲ አረቢያና ግብፅ አሳሳቢ ሲሉት፣ ኦማን አዉግዛዋለች።ኢራንም አጥብቃ አዉግዛዋለች።የኢራን ወዳጅ የምዕራባዉያን ጠላት የምትባለዉ ሩሲያ ደግሞ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንዲነጋገር ጠይቃለች።ቻይና ሁሉም ወገኖች ጠቡን ከማባባስ እንዲታቀቡ መክራለች።

ይሁንና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ባለፈዉ ቅዳሜም የመንን መደብደቡ ተዘግቧል።የሁቲ ታጣቂዎች ባለፈዉ ዕሁድ በዩናይትድ ስቴትስ የጦር መርከቦች ላይ የተኮሱትን ሚሳዬል የአሜሪካ ጦር ማክሸፉን አስታዉቋልም።

የአዉሮጶች ዝግጅት

የአዉሮጳ ሕብረት በበኩሉ በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ መርከቦችን ደህንነት የሚጠብቅ  ጦር ኃይል ለማዝመት መምከር ጀምሯል።የሕብረቱ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች በሚቀጥለዉ ሳምንት በጉዳዩ ላይ ለመወሰን ቀጠሮ አላቸዉ።ጀርመን ጦር የማዝመቱን ሐሳብ እንደምትደግፈዉ የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታዉቋል።

ስጳኝ ሀሳቡን ባትቃወምም ጦር እንዳማታዘምት መከላከያ ሚንስትሯ አስታወቀዋል።ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ኢጣሊያ፣ ፈረንሳይና አየርላንድን የመሳሰሉ የሕብረቱ አባል ሐገራትም ሐሳቡን ለመደገፍና ለመቃወም እያቅማሙ ነዉ። ጥያቄዉ፣ የጋዛዉ ጦርነት መዘዝ ተስፋፋ ወይስ ባለበት ቆመ?

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ