1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋና # FixTheCountry ዘመቻ 

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 8 2014

በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ጋና ወጣቶች ስለሚያካሂዱት ትልቅ የሃሽታግ FixTheCountry የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ምንነት እና እንዴት ዘመቻው ከኢንተርኔት ዘመቻነት አልፎ ወደ ጎዳና ንቅናቄ እንደተቀየረ እንቃኛለን።

https://p.dw.com/p/44PPD
Ghana | Fixthecountry Proteste in Accra
ምስል Nipah Dennis/AFP/Getty Images

ባለፉት ጊዜያት አንዳንድ በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረጉ እንደ #FridaysForFuture ያሉ ዘመቻዎች ዓለም አቀፍ ትኩረት ሲያገኙ አይተናል። ጤና ይስጥልን የተከበራችሁ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተከታታዮች፤ የዛሬው ዝግጅት ወደ ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ጋና ይወስደናል። በጋና የሚገኙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በመንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር FixTheCountry በሚል ሃሽታግ  የጀመሩት ዘመቻ ከኢንተርኔት ዘመቻነት አልፎ  ወደ ጎዳና ንቅናቄ ተቀይሯል። 
ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የጋና ኢኮኖሚ እያደገ ቢሄድም የስራ እድል ፈጠራ ግን በዚያው መልኩ እንዳላደገ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው እና ብሩኪንግስ ቲንክ ታንክ የተባለው ተቋም ያደረገው ጥናት ያሳያል።  
ጋና ከ 31 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ያላት ሲሆን ከግማሽ በላዩ እድሜው ከ25 ዓመት በታች ነው።አብዛኞቹ ወጣቶች ዩንቨርስቲ የመግባት አቅም እንደሌላቸው እና አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት እንደውም ስራም ሆነ ምንም አይነት ሙያዊ ስልጠና እንደሌላቸው የአለም ባንክ ይጠቁማል። የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለው ችግር ደግሞ ድሮም በወጣቱ ዘንድ ያለውን ብስጭት የባሰ አድርጎታል። ስለሆነም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ #FixThe Country የሚለውን ሃሽታግ ያስቀመጡት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ማሻሻያ የፈለጉ ወጣት ጋናውያን ናቸው።  

በወጣት አፍሪቃውያን ጉዳይ ላይ የሚያተኩረው የዶይቸ ቬለ 77 ከመቶው ዝግጅት የጋና መዲና አክራ ላይ ይህንኑ እንቅስቃሴ የዳሰሰ ውይይት አካሂዶ ነበር። በውይይቱ ላይ የተሳተፈው ሚአዬ ኮፓሬ ይህንን በትዊተር የተጀመረ ዘመቻ እንዴት በርካታ ግለሰቦች እና ተቋማት እንደተቀላቀሉት ያስረዳል። ኮፓሬ የ«ኢኮኖሚክ ፋይተርስ ሊግ» እና  #FixTheCountry ዘመቻ ጥምረት አስተባባሪ ነው።  « የተወሰንን ወጣቶች ተሰብስበን የዕለት ከዕለት ኑሮ እና ተሞክሮዋችን እየተወያየን ነበር። ከዛ ሁላችንም ተመሳሳይ ችግር እየገጠመን እንደሆነ ተረዳን። በተለይ በእኛ ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች። ሌላው ደግሞ ጠቅላላ ጋናውያንን ይመለከታል። ከዛ ምን ቢደረግ ይሻላል ስንል። ይቺህ ሀገር መጠገን አለባት አልን። ከዛ በቃ ሀሽታግ ተጨመረበት።» ሲል ኮፓሬ ዘመቻው እንዴት እንደቀልድ እንደተጀመረ ያስረዳል። ከዛም ያንን ያኑ በርካታ የጋና ወጣቶች ሀሽታጉን ተጠቅመው ሀሳባቸውን ይገልፁ ጀመር።

Ghana | Fixthecountry Proteste in Accra
ምስል Nipah Dennis/AFP/Getty Images

ከፖለቲካ ነፃ ነን የሚሉት እና ከሃሽታጉ በስተጀርባ ያሉት ወጣቶች ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የጎዳና ሰላማዊ ሰልፍ ጠሩ። ሰልፉ ግን በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት እንዳይካሄድ ተከለከለ።  ኮፓሬ በዚህ አይስማማም። እሱ  እንደሚለው የሰልፉ መከልከል ህገመንግሥቱን የሚቃረን እና ኢ ዲሞክራሲያዊ ነው። ይህም ዘመቻው ይበልጥ ከጋና ውጪ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል። « በፖሊስ እና በንቅናቄው መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ሰልፉን ከማካሄድ ቢያስቆመንም ንቅናቄውን ግን አላስቆመውም እንደውም ይህ በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ ድንበር መሻገር ቻለ። በጥቂት የአክራ ጎዳናዎች ላይ ሊካሄድ የነበረው ሰልፍ አለም አቀፋዊ ትኩረት አግኝቶ በ 6 እና 7 የአሜሪካ የአውሮፓ እና ሉሎች ቦታዎች ሰልፍ ሊካሄድ ቻለ። አስገራሚው ነገር ደግሞ ሌሎች ሀገራት ላይ ሰልፍ ያደረጉት ጋናውያን ቢሆኑም መልዕክቱ የሌሎችንም ፍላጎት የሚገልፅ ነበር» 

ኮፓሬ #FixTheCountry ወደ አለም አቀፋዊ ንቅናቄ ተቀይሯል። ለማለት ባይደፍርም የጋና ወጣቶች ፈተና የበርካታ ሀገራት ወጣቶች ፈተና ነው ይላል።  እ.ጎ.አ. ነሀሴ 6 ቀን የመንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው NDC በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ Fix The Country ሃሽታግ ያደረጉ መፈክሮች በአክራ ጎዳና ላይ ታይተዋል። የንቅናቄው አባላት በደቡብ አሻንቲ ክልል በፖሊስ በጥይት የተገደሉ ሁለት ሰዎች ፍትህ እንዲያገኙም ጠይቀዋል። ወጣቶቹ ሰኔ 29 ቀን ወጣት አክቲቪስት ኢብራሂም "ካካ" መሀመድ ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ድብደባ በመቃወም ተቃውሞ አሰምተዋል። ታድያ ጋናን ወጣቶቹ እንደሚሹት የሚጠግነው ማነው? ያለ ፖለቲካዊ ተሳትፎስ እንዴት ነው ፍላጎታቸውን ማሟላት የሚችሉት?  « አሁን በዚህ ወሳኝ የሆነ ንቅናቄ የሚሳተፉ ሰዎችን እያነቃቃን እና እያደራጀን ነው። ይህንን ማድረግ ከቻልን፤  ከዛ ሌሎች አማራጮች ይኖሩናል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን የምንረዳው ነገር ወጣቱ በሀገሪቱ ላይ ስለሚካሄደው ፖለቲካ ያለው ግንዛቤ በቂ እንዳልሆነ ነው።  ስለዚህ የንቅናቄው ዋና ትኩረት የወጣቱን የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ማጠንከር ነው።» ይላል ኮፓሬ።

ሪጃይና አሜጋ ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ እና ጠበቃ ናት። ራሷን ከወጣቶቹ ተርታ ነው የምትመድበው። « ይሁንና የ Fix The Country ንቅናቄ ሁሉንም ሰው ይመለከታል። እኔ ወጣት ስለሆንኩ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ጋናዊ ይመለከታል። ከህፃን እስከ ወጣት ከጎልማሳ እስከ አዛውንት። ምክንያቱም የ Fix The Country ጥሪ ህገ መንግሥቱ እንዲቀየር፣ ወሳን የሆኑ ህጎች እንዲተገበሩ፤ የህብረተሰቡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና እንዲጎለብት የመሳሰሉ ናቸው። ይህ ደግሞ ወጣትም ሆነ አዛውንቱን ሁሉ ይመለከታል» 

Ghana | Fixthecountry Proteste in Accra
ምስል Nipah Dennis/AFP/Getty Images

ወይዘሮ ቲውደር ዊልያም የሲቪክ ማህበረሰብን የሚወክሉ እና በሴቶች ፣ ሰላም እና ደህንነት  ላይ የሚሰሩ ጋናዊት ናቸው። እንደዛቸው ከሆነ የንቅናቄው ወጣቶች እንዲሻሻል የሚጠይቁት ነገር ብዙ ነው። « ይህ ለእኔ መጠነ ሰፊ ጥሪ ነው። ሀገራችን ትጠገን ፤ ህገ መንግሥቱ ወዘተ ። አንድ ወይም ሁለት ነገሮች ላይ ተተኩሮ ቢሰራ ጥሩ ነው ባይ ነኝ። አንድ መንግሥት ብቻ ተጠያቂ የሚሆንበት። ይህ መንግሥት ስልጣን ከመልቀቁ በፊት እነዚህን ነገሮች እንጠግናቸው እንበል። መንግሥት ለስራ ፈጣሪዎች የመደበው ባጀት አለ። ይህንን እንዴት ነው የምንቆጣጠረው የሚለው ላይ ቢተኮር ጥሩ ነው።  » 
እንደ ወይዘሮ ዊልያም እምነት በሚቀጥሉት አመታት ውስጥ ስራ ፈጣሪዎች ለሌሎች ወጣቶች ስራ እየፈጠሩ ችግሩ ይቀረፋል። ወጣቷ ጠበቃ ግን ንቅናቄው የተወሰኑ ነገሮች ላይ ብቻ አተኩሮ ይሰራ በሚለው የወይዘሮ ቲውደር ዊልያምስ ሀሳብ አትስማማም። ለእሷ ሁሉም ነገሮች ተያያዥነት አላቸው። « ለምሳሌ ትምህርት እና የስራ ገበያን እንመልከት። መጨረሻ ላይ የስራ ገበያ የምናገኝበት የሙያ ትምህርት እንፈልጋለን። ለምሳሌ ከ 1 እስከ 4ኛ አመት ዮንቨርስቲ ገብተን የቃል ትምህርት እንወስድ እና በ4ኛው አመት ጥናት አድርገን የመመረቂያ ፁሁፍ እንፅፋለን። ከዛ ግን መደርደሪያ ላይ አስቀምጠን ምንም ማድረግ አንችልም።   
ጋና ውስጥ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወይም ተመራቂዎች 10% ያህሉ ብቻ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ከአንድ አመት በኋላ ሥራ እንደሚያገኙ ጥናቶች ያመላክታሉ። በየዓመቱ ግን ከ270,000 በላይ ምሩቃን ከመንግሥትና ከግል ዩኒቨርሲቲዎች ይመረቃሉ።  ወደፊት ተመርቀው ስራ የሚያስገኛቸው ሙያ ከመማር ባሻገር ንቅናቄውን የሚደግፉት ጋናውያን የሚጠይቁት ፣ ሙስና እንዲቆም፣ ግብር እንዲቀነስ ፣የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል የመሳሰሉት ይገኙበታል።  ይህንን ጥያቄያቸውን ለመንግሥት ለማቅረብ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያ ጥሩ አማራጭ ሆኖ አግኝተውታል። የንቅናቄው ጫና ይሁን አይሁን በይፋ ባይገለፅም የጋና ብሄራዊ ፔትሮሊየም ባለስልጣን የቤንዚን ዋጋ ላይ መጠነኛ ማሻሻያ አርጓል። 
ኮጆ ኦፖንግ ንክሩማህ የጋና የመረጃ ሚኒስትር ናቸው። መንግሥት የ Fix The Country ንቅናቄን እንዴት እንደሚያየው ተጠይቀው ሲመልሱ « የ Fix The Country ንቅናቄ፣ አጀንዳ፤ ወይም ዘመቻ በማህበረሰባችን ላይ ያሉ አንዳንድ ችግሮች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኝ የሚረልግ ጥሪ ነው። በእኔ እምነት ፖለቲከኛ ያልሆኑ እና ተራው ዜጋ ፈጣን ምላሽ የሚሹ ነገሮች አሉ ብለው ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ተቃውሞ ነው።»  
በጋና ያሉ የመንግስት ደጋፊዎች በፊናቸው  'FixYourself' በሚል ሃሽታግ ስር መንግሥታቸውን የሚደግፍ እና ንቅናቄውን የሚቃወም መልዕክቶች ማንሳት ጀምረዋል። ይህ የሆነውም የፓርላማ አባል የሆኑት ፍራንክ አኖህ-ዶምፕሬህ መንግስት ሀገሪቱን እንዲያስተካክል ከመጠየቃችሁ በፊት ራሳችሁን ጠግኑ የሚል መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ነው። የገጠማቸው ተቃውሞ ግን ኃላ ላይ የፓርላማው አባል ይቅርታ እንዲጠይቁ አስገድዷቸዋል።  በትዊተር ባስተላለፉትም መልዕክት « ቀደም ብዬ ለለጠፍኩት መልዕክት ይቅርታ እጠይቃለሁ። የዘመኑን ከባድ ችግር ያልጠቀሰ  እና የወጣቱ ፍላጎት ያልጨበጠ ነበር። »  ብለዋል።  ይህ ይቅርታ ግን ለበርካታ ጋናውያን በቂ አይደለም። ስለሆነም ከንቅናቄው አራማጆች አንዱ የሆነው ኤርኔስቶ ዬቦአህ ተስፋውን የሚጥለው በሀገሪቱ ወጣቶች ላይ ነው። "መሪዎቻችን ይህችን ሀገር ከድህነት አረንቋ ፣ ከገባችበት ድህነት፣ ከበሽታ፣ ከስቃይ እና ከውድቀት ማጥ ውስጥ ለማውጣት አቅም የሌላቸው እንደሆነ ለእኛም ሆነ ለብዙ ወጣቶች ግልጽ ነው። ስለዚህም አመራር ውስጥ የወጣቶች ተሳትፎ ሊጨምር ይገባል ሲል ለዶይቸ ቬለ ገልጿል። 

Ghana | Fixthecountry Proteste in Accra
ምስል Nipah Dennis/AFP/Getty Images

 ክሪስቲና ክሪፓህል/ ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ