1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የገምሹ በየነ ኩባንያ ሰራተኞች ከመርሐቤቴ መውጣት ጀመሩ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 18 2012

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መርሐቤቴ ወረዳ ባለፈው እሁድ ጥቃት የተፈጸመበት የግንባታ ኩባንያ ሰራተኞች በመከላከያ ሰራዊት ታጅበው መውጣት መጀመራቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ሰራተኞቹ ማሽኖች እና ቡልዶዘሮች ከተቃጠሉበት ጥቃት በኋላ ለቀው ለመውጣት ተቸግረው ነበር።

https://p.dw.com/p/3S9Z3
Karte Äthiopien Ethnien EN

በመርሐቤቴ የነበረው ኩባንያ ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር

የገምሹ በየነ የግንባታ ኩባንያ ሰራተኞች በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መርሐቤቴ ወረዳ ከሚገኝ የሥራ ቦታቸው ለቀው መውጣት ጀመሩ። ሰራተኞቹ ባለፈው እሁድ በኩባንያው ንብረቶች ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ከአካባቢው ለቀው እንዳይወጡ በአካባቢው ነዋሪዎች ታግደው እንደነበር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 
ከሰራተኞቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ እንዳልካቸው በላይ ወደ 300 ገደማ ይሆናሉ የተባሉት ሰራተኞች በመከላከያ ሰራዊት ታጅበው ከመረሐቤቴ መውጣታቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። 

አሁን ከአካባቢው ወጥተው በኦሮሚያ ክልል ደራ በተባለ ቦታ መድረሳቸውን የተናገሩት አቶ እንዳልካቸው ካለፈው እሁድ ጀምሮ ከአዲስ አበባ 180 ኪሎ ሜትር ገደማ ከምትርቀው ዓለም ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የኩባንያው ካምፕ ውስጥ ነበሩ። አቶ እንዳልካቸው በአካባቢው በቆዩበት ወቅት በሰራተኞች ዘንድ ለቆ የመውጣት ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበር አስረድተዋል። 

«ሰራተኛው መውጣት ፈልጎ ነበር። ሙሉ በሙሉ እዚያ አካባቢ ላይ ያሉት የካምፑ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ስለወደመ ሰራተኛው ወደ ቤተሰቡ እንሂድ ልቀቁን ነው የሚለው እነርሱ ደግሞ አንለቅም በማለት አሁንም ችግር አለ። ህዝቡ እየተለመነ ነው። እኛ ያለንበት አካባቢ እስካሁን ሰላም ነው፤ ግን እየተጠበቅን ነው ያለነው። በአካባቢው ሚሊሻ እና በፖሊሶች ብቻ ነው ፤ የደረሰልን የመከላከያ ሀይል የለም።  ሰራተኛው ውስጥ ደግሞ የፍራቻ ስሜት አለ»

ጌብኮን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የተባለው ድርጅት እና በአዲስ አበባ የሚገኘው ኢሊሊ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል ባለቤት አቶ ገምሹ በየነ በትናንትናው ዕለት በመርሐቤቴ ወረዳ በነበሩ ንብረቶች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። በጥቃቱ የወደሙ ንብረቶች ግምት ሊጣራ ይገባል ያሉት አቶ ገምሹ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል። ከኩባንያው ሰራተኞች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አመንሲሳ ዳባ ከአካባቢው ለቆ ለመውጣት መቸገራቸውን በካምፕ ውስጥ ሳሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ አመንሲሳ እንዳሉት በወቅቱ የገምሹ በየነ ሰራተኞች በቂ ምግብ ማግኘት ተቸግረው ቆይተዋል።

 «በዚህ ካምፕ ውስጥ በትንሹ ከሶስት መቶ ሰው በላይ ነው ያለነው፤ እንዴት አድርገን እንወጣለን? ወዴትስ እንወጣለን? አሁንኮ እዚያ የተቃጠለው ካምፕ አካባቢ ላይ የእኛ ሰራተኞች ከእሁድ ጀምሮ ምግብ ያልቀመሱ አሉ ። በመከላከያ ተጠብቀው ነው ያሉት ። ወዴት እንወጣለን? በእግር ለመሄድ የማይቻልበት አገር ነው። ወዴት እንውጣ እና ህይወታችንን አትርፈን ወደ ቤተሰቦቻችን መሄድ ነው የምንፈልገው»

የገምሹ በየነ የግንባታ ኩባንያ ሰራተኞች ለተፈጸመው ጥቃትም ሆነ ለጉዞ ክልከላው የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠያቂ ያደርጋሉ። ሰራተኞች እንደሚሉት ከኩባንያው ንብረቶች በተጨማሪ ልብሶቻቸውን ጭምር አጥተዋል። «የአለም ከተማ ካምፕ ላይ የድርጅቱን ንብረት ጨምሮ ሰራተኛው ሙሉ በሙሉ ልብሱንና ንብረቱን ያገኘው ነገር የለም። ምንም አላገኘንም። እና ንብረታችን ሙሉ በሙሉ ተዘርፏል። እና አለም ከተማ አካባቢ ያሉት ደግሞ ትልቅ ረሃብ ውስጥ ነው ያሉት ፤በረሃብ ጭምር እየተቀጡ ነው ያሉት»

የአማራ ክልል እስካሁን በመርሐቤቴ ስለተፈጠረው ነገር ማብራሪያ አልሰጠም። ለቃጠሎውም ሆነ በሰራተኞቹ ላይ ተደርጎ ስለነበረው ክልከላ ኃላፊነት የወሰደ ወገን አልተገኘም። በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ እና የወረዳው ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ያደረግንው ሙከራ አልተሳካም። 

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ