1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሜርክል እና የዜሆፈር ስምምነት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 26 2010

እህትማማቾቹ ፓርቲዎች አዲስ ተገን ጠያቂዎች የሚስተናገዱባቸው መሸጋገሪያ የተባሉ ማዕከላትን ጀርመን ድንበር ላይ በማቋቋም  ለተገን ጥያቄአቸው ወዲያውኑ መልስ ለመስጠት ተስማምተዋል። በዚህ አሠራር ጥያቄአቸው ተቀባይነት የሚያገኘውን ለማስገባት ውድቅ የተደረገባቸውን ደግሞ በዚያው ለማባረር ነው የተስማሙት።

https://p.dw.com/p/30lRs
Fraktionssitzung Union Seehofer Merkel
ምስል picture alliance/dpa/K. Nietfeld

የሜርክል እና የዜሆፈር ስምምነት

እህትማማቾቹ የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ እና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ ለሳምንታት ሲያወዛግባቸው በቆየው የስደተኞች ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይሁን እና  ሁለቱ ፓርቲዎች የተስማሙበት ጉዳይ የጥምሩ መንግሥት አካል የሆነው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ከዚህ ቀደም የተቃወመው መሆኑ ውሉ ለተጣማሪው መንግሥት ሌላ ፈተና እንዳይሆን አስግቷል። የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው። ለቅንብሩ ኂሩት መለሰ
ውዝግቡ ሳምንታት ወስዷል። እንደ አጀማመሩ እና አካሄዱ እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ አይመስልም ነበር፤ የደቡብ ጀርመንዋን የባቫርያ ፌደራዊ ክፍለ ሀገር በሚመራው በክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ በምህጻሩ ሲ ኤስ ዩ እና በእህት ፓርቲው በክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ ሲ ዲ ዩ በተለይም በሁለቱ ፓርቲዎች መሪዎች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ። ውዝግቡ ትናንት በስምምነት መፈታቱ ከ3 ወር በፊት የቆመውን አዲሱን የጀርመን ጥምር መንግሥት የሚያረጋጋ ተብሏል። የውዝግቡ ዋነኛ ተዋናይ ለሆኑት የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ መሪ እና የጀርመን ፌደራል መንግሥት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኽርስት ዜሆፈር ደግሞ አስደሳች ሆኗል።  
« ስምምነት ላይ በመድረሳችን ደስተኛ ነኝ። ለቆሙለት ዓላማ መታገል ዋጋ እንደሚያስገኝ የሚያሳይ ነው። ስምምነታችን ወደፊትም የሚዘልቅ ስምምነት ነው። ይህ ግልጽ ስምምነት ከኔ አቋም ጋር አብሮ ይሄዳል፤በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርነት እንድቀጥልም ያስችለኛል።»
ዜሆፈር ችግሩ ከመፈታቱ በፊት የፓርቲያቸውን መሪነት እና አገር አስተዳደር ሚኒስትርነቱንም ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጠይቀው ነበር። ከስምምነቱ በኋላ ግን ስበውታል። የውዝግቡ መነሻ ወደ ጀርመን የሚመጡ ስደተኞች የሚስተናገዱበት መንገድ ይቀየር የሚል ነበር። ጥያቄውን ያነሱት ዜሆፈር ፣ በሌሎች የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት የተገን ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኘ  ወይም ከዚህ ቀደም ተገን እንዲሰጣቸው ጠይቀው የተከለከሉ ስደተኞች ወደ ጀርመን እንዳይገቡ ያወጡት እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዚህም ብቻ ሳያበቁ ይህ ገቢራዊ ካልሆነ ሥልጣናቸውን በመጠቀም የጀርመንን ድንበር ለስደተኞች ለመዝጋት ዝተው ነበር። የጀርመን መራሂተ መንግሥት እና የሲ ኤስ ዩ እህት ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ ሊቀመንበር  አንጌላ ሜርክል ደግሞ ችግሩ  ጀርመን በምትወስደው የተናጠል እርምጃ ሳይሆን በአውሮጳ አቀፍ ደረጃ መፈታት አለበት የሚል አቋም ነበር የያዙት ነበር። በዚሁ መሠረትም ሜርክል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከአባላት ጋር መክረው የተስማሙበትን መፍትሄ ይዘው ቢመለሱም ውዝግቡ ተካሮ ቀጠለ። የአውሮጳ ህብረት መሪዎቹ በዚሁ ጉባኤያቸው ወደ ህብረቱ የሚመጡ ስደተኞችን  በፈቃደኝነት ለመከፋፈል እና በህብረቱ ውስጥም የተገን ጠያቂዎችን ጉዳይ የሚከታለሉ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ማዕከላት ለማቋቋም ነበር የተስማሙት። በባህር ላይ ለአደጋ የሚጋለጡ ስደተኞችን በሚመለከትም ሃላፊነቱን ለመጋራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይሁንና አንዳንድ መገናኛ ብዙሀን «አማጺ» የሚል ስም የሰጧቸው ዜሆፈር የጋራው መፍትሄ ስላልተዋጠላቸው ውዝግቡ መካረሩ ብዙ ጀርመናውያንን አስፈርቶ አስቆጥቶም ነበር። የቦን ነዋሪዎች ለዶቼቬለ የሰጡት አስተያየት ይህንኑ የሚያመለክቱ ናቸው።
«አሁን የሚሆነው አስፈሪ እና አሳፋሪ ነው፤  በአጠቃላይ እንደ አውሮጳውያን ከማሰብ ይልቅ ሰዎች የግል አመለካከታቸውን ማንጸባረቃቸው። እኔ በጎ በጎውን የማስብ ሰው ነኝ ሆኖም ሁኔታውን ቀኞች ይጠቀሙበታል የሚል ስጋት አለኝ።ህዝቡ  እስካሁን አደባባይ አለመውጣቱ አስገርሞኛል። ከዚህ ቀደም ብዙ ሰልፎች ላይ ተካፍያለሁ እንደሚመስለኝ ይህ ባህል እንደገና መምጣት አለበት።
«ሲ ኤስ ዩ አማራጭ ለጀርመን በተሰኘው ቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ መርህ ምክንያት ወደ ቀኝ እያዘነበለ ነው። እናም የውጭ ዝርያ እንዳለው እንዳለው ሰው መንግሥት ሥራውን መሥራት ሲያቅተው እፈራለሁ። ለምሳሌ የአማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ሰዎች የሚያገኑት ድምጽ እየጨመረ ነው። እነርሱ የነጻ ዲሞክራሲ ስርዓቱን ለማራከስ ሲሞክሩ ያስፈራናል እኔም ከዚህ ተጎጂ ነው የምሆነው።»  
«ስለ ውዝግቡ ስሰማ ልክ እንደ መዋዕለ ህጻናት ነው ብዬ አሰብኩ። አንዱ የመከራከሪያ ነጥብ ሲያልቅበት አብሮ ሊሰራ አይችልም። ሀገራችንም የምትመራበት መንገድ በአጠቃላይ ያሳስበኛል። እናም አሁን በግሌ ወደ ማህበረሰቡ ራሱን ወደ ሚያደራጀው ማህበረሰብ መመለስ ነው የኔ ምርጫ። እዚያ መሳተፍ እና ውጤት ማየት እችላለሁ። በንጽጽር ሲታይም ግልጽ ነው ።»
ሁለቱም ፓርቲዎች በተናጠል በጉዳዩ ላይ ከመከሩ በኋላ ትናንት በጋራ ተሰብስበው እኩለ ለሊት ግድም ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል። ሜርክል ሁለቱ ፓርቲዎች አስቸጋሪ ካሉት ድርድር በኋላ የደረሱበትን ስምምነት  በጣም ጠቃሚ ብለውታል።
«በዚህ ዓይነት መንገድ ነው በአውሮጳ ህብረት ውስጥ ያለውን የአጋርነት መንፈስ ማቆየት የምንችለው። ሁለተኛ የሚባለውን ስደት በተደራጀ መልኩ ለመከታተል የምንችለውም ለዚህም ነው ከከባዱ ድርድር እና ከአስቸጋሪዎቹ ቀናት በኋላ ችሩ አስታራቂ ሀሳብ አግኝተናል ብዮ አስባለሁ።»
 ሁለቱ ፓርቲዎች ከተስማሙባቸው  ጉዳዮች አንዱ ከዚህ ቀደም በሌላ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገር ጥገኝነት ጠይቀው ወደ ጀርመን የሚመጡ ስደተኞችን ከጀርመን ድንበር መመለስ ነው። ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ የፖለቲካ ተንታኝ እና የህግ ምሁር የስምምነቱን ይዘት ያብራሩልናል
የሜርክል እና የዜሆፈር ፓርቲዎች የደረሱበት ስምምነት መጀመሪያ በገቡበት የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገር ጥገኝነት ከጠየቁ በኋላ ወደ ጀርመን የሚመጡ ስደተኞችን መጀመሪያ የረገጡት የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገር መመለስ የማይችሉ ከሆነ ስደተኞቹን ወደ ኦስትሪያ የመላክ እቅድንም ያካትታል።   ጀርመን እወስዳለሁ ያለችው ይህ እርምጃ በተለይ የህብረቱ ደቡባዊ ድንበር የሆኑት ሀገራትም ሆኑ ኦስትርያን የመሳሰሉት የጀርመን ጎረቤቶች ተመሳሳይ እንዲወስዱ ያደርጋል የሚል ስጋት አሳድሯል።እህትማማቾቹ ፓርቲዎች ከዚህ ሌላ አዲስ ተገን ጠያቂዎች የሚስተናገዱባቸው መሸጋገሪያ የተባሉ ማዕከላትን ጀርመን ድንበር ላይ በማቋቋም  ለተገን ጥያቄአቸው ወዲያውኑ መልስ ለመስጠት ተስማምተዋል። በዚህ አሠራር ጥያቄአቸው ተቀባይነት የሚያገኘውን ለማስገባት ውድቅ የተደረገባቸውን ደግሞ በዚያው ለማባረር ነው የተስማሙት። ከዚህ በተጨማሪም የውጭ የሚባሉትን የአውሮጳ ህብረት ድንበሮች ጥበቃ ማጠናከር ሌላው ከስምምነት ላይ የደረሱበት ጉዳይ ነው።  ሲ ኤስ ዩ እና ሴ ዴ ኡ ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል የጥምሩ መንግሥት አካል የሆነው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በምህጻሩ SPD ከዚህ ቀደም የተቃወማቸው ይገኙበታል። ፓርቲው በጉዳዩ ላይ መክሮ ዛሬ  ውሳኔውን ያሳውቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ዶክተር ለማ ግን SPD ስምምነቱን ይቃወማል ብለው አያስቡም። ምክንያታቸውንም አስረድተዋል።
የጀርመን ተጣማሪ መንግሥት አካል የሆኑት እህትማማች ፖርቲዎች ሲ ዲዩ እና ሲ ኤስ ዩ ከሳምንታት ጠንካራ ውዝግብ እና ከአስቸጋሪ ድርድር በኋላ ስምምነት ላይ ቢደርሱም ሂደቱ  በጀርመን ፖለቲካ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ቀላል እንዳይደለ ይነገራል። ውዝግቡ ጀርመን በአውሮጳ ህብረት ውስጥ ያላትን ተሰሚነትም አጠያያቂ የሚያደርግ መሆኑ እንደማይቀር ነው የተገለፀው። ዶክተር ለማም በዚህ ይስማማሉ። የዜሆፈር ፓርቲ የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፣በመጪው ጥቅምት በሚመራው በባቫርያ ፌደራል ግዛት ምርጫ ይጠብቀዋል። የዚህ ሁሉ ውዝግብ እና ጥድፍያ «አማራጭ ለጀርመን» የተባለውና ብዙ ደጋፊ እና መራጭ ያፈራው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ሊወስድ ይችላል የተባለውን ድምጽ ማስቀረት ነው። ይህን ሊያሳካ መቻሉ ግን አሁንም አጠያያቂ ነው። 

Horst Seehofer
ምስል picture-alliance/A.Hosbas
Berlin Asylstreit - Pk Merkel
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ