1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶይቼ ቬለን ዘገባዎች የሚተች ሰላማዊ ሰልፍ በቦን ተደረገ

ዓርብ፣ ሐምሌ 30 2013

ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የትግራይ ተወላጆች ዶይቼ ቬሌ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት በትግራይ ክልል የሚደረገዉን ጦርነት አስመልክቶ የተዛባ መረጃ አሰራጭቷል በማለት ወቀሱ።  የትግራይን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ የተለያዩ መፈክሮች ያሰሙ ሰልፈኞች ቅሬታቸውን በደብዳቤ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ለሬዲዮ ጣቢያው የስራ ሃላፊዎች ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/3yepL
Protest gegen Berichterstattung des DW Amharic services
ምስል Tamirat Dinssa/DW

የዶይቼ ቬለን ዘገባዎች የሚተች ሰላማዊ ሰልፍ በቦን ተደረገ

ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የትግራይ ተወላጆች ዶይቼ ቬሌ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት በትግራይ ክልል የሚደረገዉን ጦርነት አስመልክቶ የተዛባ መረጃ አሰራጭቷል በማለት ወቀሱ። 
ቁጥራቸው አንድ መቶ የሚደርሱ ሰልፈኞች ቅሬታቸውን በደብዳቤ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ለሬዲዮ ጣቢያው የስራ ሃላፊዎች ሰጥተዋል። የትግራይ ክልል ባንዲራን የያዙት ሰልፈኞች «ዶይቼ ቬለ የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት ያቁም» ፣ «ዶይቼ ቬለ ከኢትዮጵያ መንግስት መወገኑን ያቁም» ፣ «ሚዛናዊ ዘገባዎችን  ያሰራጭ»  የሚሉ መፈክሮች ሲያሰሙ ነበር። 

ከሰልፈኞቹ አንዱ የሆኑት እና በዳርምሽታት ከተማ የሚኖሩት አቶ አታኸልቲ አበበ «የምንቃወመው የዶይቼ ቬለ የአማርኛው ስርጭት የሚያስተላልፋቸው ዜናዎች ትግራይ አካባቢዎች ይከሰት በነበረው ነገር አንዳንድ ስህተቶች አይተናል። ለምሳሌ የተከዜ ድልድይን ያወደመው ሌላ እንደሆነ እየታወቀ፤ ብዙ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ያወደመውን በትክክል የገለጹ ቢሆንም ዶይቼ ቬለ ከዚያ በተቃራኒ የትግራይ ኃይሎች አፈረሱት ነው ያለው» የሚል ክስ አቅርበዋል። «ትክክለኛን ዜና አንቃወምም» ያሉት አቶ አታኸልቲ ዶይቼ ቬለ በፍትሐዊነት እና ገለልተኝነት ዘገባዎች ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

ከቪስባደን ከተማ ለዚሁ ሰልፉ ተጉዘው ቦን የተገኙት ወይዘሮ ሙሉ አለማየሁ በበኩላቸው «እዚህ የመጣንበት ምክንያት ዶይቼ ቬለ እንደ ሚዲያ በተለይ የአማርኛው ክፍል በኢትዮጵያ የተፈጠረውን እውነታ ስላልዘገበ ነው። ምክንያቱም አንድ ወገን መሆኑን ስላየን ነው» የሚል ወቀሳ አቅርበዋል። 

Protest gegen Berichterstattung des DW Amharic services
የተቃውሞ ሰልፈኞች ከያዟቸው መፈክሮችምስል Tamirat Dinssa/DW

በደቡብ ጀርመን ባደን ቩርተምበርግ ግዛት ኡልም ከተማ በሚገኝ ዩኒቨሲቲ በመምህርነት እንደሚሰሩ የገለጹት መዳሃኔ አስመላሽ ሙላት «የእኛ ጥያቄ ትግራይ ያለውን ሁኔታ ደግፋችሁ ተናገሩ፤ የኢትዮጵያን መንግሥት አውግዙ አይደለም። ግን ያለውን ችግር ዓለም እንዲያውቀው ሌሎች ሚዲያዎች እንደሚያደርጉት በግልጽ ረሐብ እንዳለ፣ ችግር እንዳለ፣ በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት፤ አንዳንድ ችግሮችም ሲያጋጥሙ ለምሳሌ በቅርብ የምናስታውሰው የተከዜ ድልድይ ሲፈርስ በግልጽ ይኸ ነገር እንዲህ ሆኗል። ጉዳዩን እናጣራለን ተብሎ ወይ የራስ ምርምር ተደርጎ ማን እንዳፈረሰው አሳማኝ በሆነ መልክ የአንዱን ወገን ሳይያዝ ማስረጃ ማቅረብ" እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አቶ መዳሃኔ "እኛ ከአንድ ጋዜጠኛ ወይም የጋዜጠኝነት ሥራ ከሚያራምድ ተቋም የምንጠብቀው ራሱን ችሎ ወደ አንዱ ወገን ሳያዘነብል ሁኔታውን መግለጽ ነው" በማለት ጥያቄያቸውን አብራርተዋል።

በዶይቼ ቬሌ የአማርኛው ስርጭት ክፍል ጉዳዩን ከጣቢያዉ የበላይ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ተገቢና ዝርዝር መልስ እንደሚሰጥ አስታዉቋል። ይሁንና ጣቢያዉ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ዘዴ እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን የሚዘግብዉ ትክክለኛና ሚዛናዊነታቸዉን ጠብቆ፣ ተገቢ ምንጭ እየጠቀሰም ነዉ። 

ዳርምሽታት እና ቪስባደንን ጨምሮ በተለያዩ የጀርመን ከተሞች የሚኖሩት እና ዛሬ የዶይቼ ቬለ ዋና መሥሪያ ቤት አጠገብ ለተቃውሞ ከተሰበሰቡ ሰልፈኞች መካከል ሶስቱን እሸቴ በቀለ አነጋግሯቸዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ