1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶ/ር አብይ የአስታራቂነት ጉዞ

ዓርብ፣ የካቲት 29 2011

ዶ/ር አብይ አህመድ በኬንያና በሶማሊያ መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ወደ ኬንያ ማቅናታቸው፣ የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ ጉዳይ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ለሴቶች የሞባይል ስጦታ ማድረጉን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/3Egrs
Logos App Twitter Facebook Google
ምስል picture-alliance/xim.gs
Äthiopien Sozialwohnungen in Addis Abeba
ምስል Y. G/Egziabher

ባሳለፍነው ሳምንት ከተከናወኑት አብይ ጉዳዮች አንዱ በኬንያና በሶማሊያ መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያደጉት ጥረት ነው።   ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀጠናውን ሰላም ለማረጋጋት በሚል ወደ ኬንያ አቅንተው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀንቷቸው ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያታ እና ፕሬዝዳንት ሙሐመድ አብዱላሂን ፊት ለፊት እንዲነጋገሩ አድርገዋል። የኬንያና ሶማሊያ መሪዎችን ያጨባበጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ አድርገዋል በሚል ያወደሷቸው እንዳሉ ሁሉ የተቿቸውም አሉ። 
ሀፍቶም ኤ ዘብሄረ ናዝሬትዮ "ሀገር እየፈረሰች አህጉር ይገነባል እንዴ?" ሲሉ በትዊተር ጠይቀዋል። "አብይ አጼ ሃይለስላሴን እያስታወሰኝ ነው። የውስጥ ችግር ሲጠጥር አለምን እየዞሩ የሌላ ሰው ችግር ለመፍታት መሞከር ይሄ ምን ይባላል? ኢትዮጵያ ውስጥ እውነት የለውጡ ሂደት እየቀጠለ ነው ወይ? አለመስልህ እያለኝ ነው ከለማ ንግግር በሁዋላ" ሲሉ አያ ካሳ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በትዊተር ገጽ ጽሁፋቸው ጽፈዋል።
ራፍ 789 የሚል የትዊተር ስም ያላቸው ተጠቃሚ ደግሞ "ሙከራው ጥሩ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም" ይላሉ። "እንደ አማራና ትግራይ ያሉ የተለያዩ ክልሎች ጦርነት እያወጁ ኢትዮጵያ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ልትገባ ጫፍ ላይ ናት። ቅድሚያ ልትሰጣቸው የሚገባ ነገሮችን ቅድሚያ ስጥ። የራስዋ እያረረባት የሰው ታማስላለች አሉ" ሲሉ ተችተዋል።
ተስ ፋን የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ "መጀመሪያ የውስጡን ያጥራ። ለኖቤል ሽልማት ከሆነ እኛ እንሸልመዋለን። ዲፕሎማሲ ምናምን በሚል፣ አገር እንዴት እየታመሰች እንደሆነ እያወቃችሁ ዝም ፀጥ? ለነገሩ እኔ አልሰማሁም አላየሁም ውጭ ሀገር ነበርኩ ይባልልሀል። የመደመር ፍልስፍና" ሲሉ ጽፈዋል። ሰለሞን ነጋሽ በትዊተር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባራዊ እርምጃ እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል። "ህዝብ ራሱን ከጥቃት ለመከላከል የራሱን ጠባቂ ሚሊሺያ ካቆመ እንደሶማሊያ ጥቅም አልባ ጥገኛ መንግስት ከመሆን የዘለለ ዕጣ ፈንታ የለህም። አሁን ቆራጥ መሪ ያስፈልጋል" ብለዋል። 
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተሰጡትን አሉታዊ አስተያየቶች ማንበባቸው የገለጹት አቤስ የተባሉ ጸሀፊ በትዊተር "ኢትዮጵያውያን ፖለቲካ ፈጽሞ አይገባቸውም ብዬ እንዳስብ አድርገውኛል" ብለዋል። ኢትዮጵያውያን  "ፖለቲካን እነርሱ እንደፈጠሩት ሁሉ ያወራሉ። መጀመሪያ የእርሱን ዓላማ ለመረዳት ሞክሩ" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚደግፍ የሚመስል አስተያየት ሰጥተዋል። ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአስታራቂነት ጥረት አዎንታዊ አስተያየታቸውን ለግሰዋል።
በሳምንቱ ውስጥ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ለቀናት የዘለቀው በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር አማካኝነት የተካሄደው የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት ነው። የከተማይቱ መስተዳድር አመታትን ፈጅቶም ቢሆን የአዲስ አበባ ነዋሪን የቤት ችግር በጥቂቱ ያቃልላል የተባለለትን የ13ኛው ዙር የ20/80 እና የ2ኛ ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ድልድል አካሂዷል። በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መካከል ያለው ጉዳይ እልባት ሳይሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ መውጣቱ አወዛግቧል።
በሁለቱም ክልሎች መካከል ያለው የአስተዳደር የወሰን ጉዳይ መቋጫ ሳያገኝ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ መውጣቱ ተገቢ እንዳልሆነ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገልጿል።  የክልሉ መንግስት በአዲስ አበባን እና በዙሪያዋ የሚከናወኑት ስራዎች ከክልሉ መንግስትና ህዝብ እውቅና ውጪ ለመስራት መታቀዳቸው ህጋዊ ነው ብሎ እንደማያምንም አስታውቋል። የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእጣ መተላለፉ በመቃወም የተቃውሞ ሰልፎችም በተለያዩ ከተሞች ተደርገዋል። ሰልፈኞቹ ከአካባቢው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መደረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በግንባታ ምክንያት ከመሬት ይዞታቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ያለእጣ ቤት እንደሚሰጣቸው አስታውቋል።
ጸዳለ ለማ ሚደክሳ "ያልገባኝ ትልቅ ነገር አለ" ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው አስተያየታቸውን ይጀምራሉ። "ይህ የጋራ መኖሪያ ቤት \ኮንደሚኒየም\ ቤት የሌላቸው ዜጎች ተመዝግበው ተስፋ በማድረግ ሲቆጥቡ ቆይተዋል። ካልተሳሳትኩም መንግስትም ያንን ከህዝቡ ቁጠባ የሰበሰበውን ገንዘብ ሌላም ገንዘብ ከበጀቱ በመጨመር ገንብቶታል ስለዚህ ያው በእጣው ውስጥ ሁሉም ተመዝጋቢ ዜጎች ተካተው እድለኛው ይደርሰዋል አሰራሩ እንዲህ አይደለምን? መንግስት ደግሞ በልዩ ሁኔታ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ከእጣ ነጻ ቤት እሰጣለሁ ብሏል ታዲያ ይሄ ሁሉ ሁከት ምንድነው? የኦሮምያ ህዝብ ጥያቄ በርካታ ቁጥር የሞተለት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ መስተካከል አለበት ከሆነ እርግጥ ነው መስተካከል አለበት። መንግስት ቆፍጠን ያለ ምላሽ መስጠትም ይኖርበታል። አሁን እጣው የወጣባቸው ቤቶችም ከአዲስ አበባ ውጪ ኦሮሚያ ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ የአካባቢውን ሰው ልዩ ተጠቃሚ ማድረጉም ቃል ተገብቶ ከሆነ ቃልን ማክበር መልካም ነው። ለነገሩ እንደዚህ ችግር እንዳለበት የሚታወቅ ከሆነ እጣውን ከማውጣታቸው በፊት ችግሮቹን መፍታት ነበረባቸው" ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።  

Baustelle in Addis Abeba Äthiopien
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

ሀሚድ ኦሊ በፌስ ቡክ  "የመኖሪያ ቤት ገንብቶ ለነዋሪዎች ማስተላለፍ የተቀደሰ ተግባር ሆኖ ችግሩ ግን አርሶ አደሩን ከመሬቱ ላይ አፈናቅሎ ለችግር ዳርጎ መሆን የለበትም። ድንበርን አልፎ መሬት ተጋፍቶ መሆን የለበትም" ብለዋል። አንዱአለም ቡኪቶ ገዳ "ኦዴፓ/ኢሃዴግ በሚመራው መንግስት ውሳኔ የኦዴፓው ታከለ ኡማ የኮንደሚኒየም ቤቶች እጣ እንዲወጣ አደረጉ። ትንሽ ቆይቶ የኦዴፓው ለማ መገርሳ ቤቶቹ እንዳይተላለፉ መግለጫ አወጣ! ምንድነው ነገሩ!? ፌዴራሊዝም ምናምኑን ተውትና በኦዴፓ ውስጥ እንኳን መነጋገር የለም ወይ?! እንደማንኛውም የአፍሪካ ፓርቲ "ትንሽ ስራ እና ብዙ ወሬ" በሆነው ገዢው ፓርቲ አልፎ አልፎ የሚከሰት " ቤት ሰርቶ ማደል" ን አይነት ትልቅ ጉዳይ እንዴት ሳይወያዩበት እጣ ይወጣል ተብሎ ይገመታል?! በየትኛው ሌላ ጉዳይ ቢዚ ሆነው?! ነው። ነገሩን የሚወስነው ሌላ ሰው ነው?! መቼም ይሄ ድራማ ተብሎ የተከወነ ከሆነ ያለፍላጎታችን" ድራማስ ከህወሃት ጋር ድሮ ቀረ!" ለማለት እንገዳደለን" ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

ሞ ሃ በየተባሉ የፌስ ቡክ ገጽ ተጠቃሚ ''ከገበሬው ልጅ መሬት የገዙት በቡልዶዘር ቤታቸዉ ፈርሶ ተፈናቅለዋል። ሆኖም መሬቱን የሸጡት የገበሬዉ ልጆች ተለቃቅመዉ መያዝ ሲገባቸዉ ኮንደሚኒየም በነፃ ያለ እጣ እንደሚሰጣቸዉ ቃል ተገብቶላቸዋል። በህገ ወጥ መንገድ መሬቱን እንደ እህል ሸንሽኖ ለቸበቸበዉ ኮንደሚኒየም እየሰጡ ሌላዉን ደግሞ ህገ ወጥ ማለት የተበላበት የሁሉ አማረሽ እቁብ ነዉ። ህጋዊ ሌቦች የሚሸለሙበት፣ በህገወጥ ስም ተበዳዮች የሚገፋበት መንገድ ይቁም። በህገወጥ መንገድ ህጋዊ አይደላችሁም ተብለዉ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ኮንደሚኒየም የሚያገኙበት መንገድ ይመቻች። ሁለት አይነት ዜግነት የለም'' ብለዋል። 

የሳምንቱ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን መነጋገሪያ ሆኖ ወደቆየው ሌላኛው ጉዳይ ስናልፍ የዛሬውን ማርች 8 የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ስጦታ ማድረጉን እናገኛለን። ኢትዮቴሌኮም የቴሌኮም አገልግሎትን ለመጠቀም አቅም ለሌላቸው ሴቶች የሞባይል ቀፎዎችን ከሲም ካርድ ጋር በስጦታ ለማበርከት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ በትዊተር እና በድረ ገጹ ገልጿል። ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪው ድርጅት በ846 ወረዳዎች ለሚኖሩ ሴቶች 70ሺህ የሞባይል ቀፎዎች ከመጋቢት 1 ቀን 2011 ጀምሮ ለማበርከት ዝግጁ እንደሆነ ሲጠቅስ ''በምን መንገድ ሊከፋፈል ይችላል'' የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።
አቤል ሲሳይ ''በታማኝነት መንፈስ ካከፋፈላችሁ ጥሩ ነው። ስጋቴ ግን እስካሁን 20 ሺህ በውስጣ ውስጥ አልቋል። እስኪ በምን መልኩ እንደምታከፋፍሉ ንገሩኝ?'' ሲሉ ጥያቄያቸው በፌስ ቡክ ገጻቸው አስፍረዋል። በልዩ ኤክሰፕሽን የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ‘'ይህ ምን ዓይነት ሞኝነት ነው? ሴቶች ለፖለቲካዊ አጀንዳ መጠቀሚያ አይደሉም። ሴቶች ለቴክኖሎጂ ዕድል እንዲደርሱበት በእውነት የምትፈልጉ ከሆነ፤ ለትምህርት፣ ለጊዜ፣ ለትክክለኛ እና ለአስተሳሳብ ለውጥ እንደዚሁም ህልማቸውን ላይ ለመድረስ ከሚያስቡ ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ይሰሩ። እነሱ በራሳቸው መቆም ከቻሉ፤ ሞባይል ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም ለመግዛት ያስችላቸዋል። ከ 100ሚ ሊዮን ህዝብ ውስጥ 51 በመቶ ሴቶች ቁጥር ባለባት ሀገር ውስጥ 70ሺህ ሞባይል ማሰራጨት ምንም ማለት አይደለም። እና ለአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን መጠቀሚያ እንደሆነ አውቃለሁ። ማርች 8 ላይ ለማድረግ የምትሞክሩ ከሆነ፤ በአመት አንድ ቀን ብቻ አይደለም ማሰብ’’ ብለዋል።

ነጃት ኢብራሂም

ተስፋለም ወልደየስ