1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሬዳዋ ነዋሪዎች ስለ መስተዳድሩ ሹምሽር ምን ይላሉ?

እሑድ፣ ጥር 5 2011

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት የሚያገለግሉ ሹማምንቱን እያነሳ በሌላ ተክቷል። የቀደመ የምጣኔ ሐብት እንቅስቃሴዋ ለተዳከመው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ግችት እና አለመረጋጋት ለተጫናት የድሬዳዋ ነዋሪዎች የተደረገው ሹም ሽር አመርቂ አይመስልም። ለመሆኑ በጉዳዩ ላይ ድሬዎች ምን ይላሉ?

https://p.dw.com/p/3BUVv
Stadt Dire Dawa in Äthiopien
ምስል Hailegzi Mehari

ድሬዳዋ መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎቿ መመለስ አለባቸው-ነዋሪዎች

ባለፈ ትዝታ ከመቆዘም ባለፈ ባረጀ ገፅታ እና ጊዜን ባልተከተለ የዕድገት ጉዞ ዛሬን በመኖር ላይ ላለችው ድሬደዋ ሁሉም ነገር ተስፋ እንጂ ከዚያ የዘለለ አይደለም ይላሉ በርካቶች። ላለፉት ዓመታት ከማዝገም  ወደ መጎተት የወረደው ዕድገቷ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቿን ሲያወሳስብ ጉዞዋንም የኃሊት አድርጎታል ፤ የሚሉቱ ነዋሪዎች ቁጥሩ እያደገ ያለውን ስራ አጥነት ፣መሰረተ ልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለአብነት ይጠቅሳሉ። 
አሁን አሁን እንዲያውም የነበራት የፍቅርና ሰላም እሴት መደፍረስ መጀመሩ የከተማዋን ችግር አወሳስቦታል። አስተዳደሩ እነዚህን በህዝብ ድምፅ የሚነሱ ችግሮች ከመፍታት ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ ገቢራዊ ማድረግና ማስቀጠል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በተለያየ መልኩ ከህብረተሰቡ ጋር አደረኩት ባለው የውይይት መድረኮች ሀሳብ መነሻነት የአመራር ለውጥ በየደረጃው አካሂዷል።
ከህብረተሰቡ ከቀረቡ መነሻ ሀሳቦች በተጨማሪ አስተዳደሩን በመምራት ላይ የሚገኙት የኢህዴግና ኢሶህዴፓ ጥምር ኮሚቴ ባስቀመጠው አቅጣጫ ላይ ተመስርቷል የተባለው ይህ የአመራር ሹም ሽር ግን "ጉልቻ የመቀየር" አይነት እንጂ ለውጥ አይደለም የሚል የተለያየ አስተያየት በመነሳት ላይ ይገኛል ፡፡ እነዘህን የህዝብ አስተያየቶች ማጠንጠኛ ባደረገው የዛሬው ወቅታዊ ዝግጅት ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ለውጡ በትክክለኛው መንገድ የተካሄደ አይደለም ብለዋል ፡፡አስተያየታቸውን ለDW ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች የህግ ባለሙያው አቶ ይትባረክ እንደሚሉት የለውጡ ሂደት የተካሄደበትን መሰረታዊ ሀሳብና ምክንያቱንም ህዝብ ሊያውቀውና ሂደቱም ህዝብን ያሳተፈ ሊሆን ይገባ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ 
በቀጣይ ለውጡ ህዝባዊ መሰረት ያለውና የከተማውን ችግር የሚፈታ እንዲሆን ለማስቻል አስተዳደሩን በመምራት ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊያተኩሩባቸው ይገባል ባላቸው ጉዳዮች ላይ ነዋሪዎቹ አስተያየት ሰጥተዋል ፡፡በአስተዳደሩ የተካሄደው የአመራር ለውጥ የህብረተሰቡን ጥያቄ መሰረት አድርጎ የተካሄደ ትልቅ ሪፎርም ነው የሚሉት የአስተዳደሩ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ችግሮች ካሉና አሁን በተካሄደው ለውጥ የቀሩ እና መጠየቅም ያለባቸው አካላት ካሉ ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገባል ብለዋል፡፡ በአስተዳደሩ የተከናወነው ለውጥ ከአንዳንድ የም/ቤት አባላት ጭምር የሀሳብ ተቃውሞ የገጠመው መሆኑ ይታወሳል ፡፡
መሳይ ተክሉ
እሸቴ በቀለ