1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ ከሥልጣኔ ለማፈናቀል ሙከራ ተደረገብኝ ሲሉ ከሰሱ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6 2011

የድሬዳዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መሐዲ ጊሬ የአስተዳደሩ ካቢኔና የሶዴፓ አመራሮች ከሥልጣን ሊያፈናቅሉኝ ሞከሩ ሲሉ ወነጀሉ። አቶ መሐዲ ከሽፏል ላሉት ሙከራ «በጎሳ ግፊት ወደ ሥልጣን የተመለሱ» ያሏቸውን አካላት ተጠያቂ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/3M2SP
Dire Dawa Stadt Äthiopien wählte einen neuen Bürgermeister
ምስል DW/Messay Teklu

የድሬዳዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መሐዲ ጊሬ የአስተዳደሩ ካቢኔ እና የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) አመራሮች ከሥልጣን ሊያፈናቅሉኝ ሞከሩ ሲሉ ወነጀሉ። «እኔ ለሥራ ጉዳይ ከሐገር በወጣሁበት ማግሥት ከሌሎች አካላት ድጋፍ ያገኙ የድርጅታችን አመራሮች የድርጅቱን ውስጠ ደንብ ባልተከተለ መልኩ እኔን ለማፈናቀል ሞክረዋል» ሲሉ ተናግረዋል።  አቶ መሐዲ ከሽፏል ላሉት ሙከራ «በጎሳ ግፊት ወደ ሥልጣን የተመለሱ» ያሏቸውን አካላት ተጠያቂ አድርገዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ግን ምክትል ከንቲባው ከሥራቸው አለመነሳታቸውን እና አለመታገዳቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ እስቅያስ እንደሚሉት የአስተዳደሩ ካቢኔ የምክትል ከንቲባውን ጨምሮ የአስተዳደሩ የሥራ አፈፃጸም እንዲገመገም ጠይቋል።

አቶ መሐዲ ጊሬ የቀድሞውን ከንቲባ አቶ ኢብራሒም ኡስማንን በመተካት ድሬዳዋን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ እንዲመሩ የተሾሙት ባለፈው መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር።

አቶ መሐዲ እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት ለሥራ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ውጪ በተጓዙበት ወቅት እርሳቸው አባል የሆኑበት የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች እና የከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት ከሥልጣን ሊያወርዷቸው ሞክረዋል። «የመሻርም የመሾምም ሥልጣን የሌለው አስፈፃሚ አካል ጋ ቀርቦ ውሳኔ እስከ ማስወሰን ድረስ» ደርሰዋል ሲሉ ከሰዋል።

ከሥልጣን ሊያወርዷቸው የሞከሩት «ከአሁን በፊት ከተማውን ሲያበጣብጡ የነበሩ ከጸጥታ ዘርፍ የተነሱ አካላት፤ በጎሳ ግፊት ወደ ሥልጣን የተመለሱ፣ የከንቲባ ወንበር ይገባኛል የሚሉ እንዲሁም በአመራር ላይ ያሉ ሰዎች» ናቸው ብለዋል።

አቶ መሐዲ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቻርተር እና የፓርቲያቸውን ውስጠ ደንብ በመጣስ «ያለውን አስተዳደር ለመፈንቀል» ሙከራ ተደርጓል ሲሉ ከሰዋል። «እኔ በሌለሁበት አስፈፃሚውን አካል የመሰብሰብ ኃላፊነት ያለባቸው ክቡር ምክትል ከንቲባ ናቸው። የሰበሰቡትም እሳቸው ናቸው። እሳቸውም ከዚህ ጉዳይ ውስጥ እጃቸው አለበት» ብለዋል።  

አቶ መሐዲ ትናንት አርብ ከውጭ አገር ጉዞ ሲመለሱ የሚቀበለኝ መኪና ተከልክያለሁ፣ እንዳልንቀሳቀስ እየታገድኩ ነው ማለት ነው» ሲሉ ተናግረዋል።  

የሶዴፓ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አባስ ሐሰን ምክትል ከንቲባው የሚገለገሉበት ተሽከርካሪ መታገዱን ገልጸዋል። አቶ አባስ የምክትል ከንቲባው አሽከርካሪ «እንዳትንቀሳቀስ፣ መኪናው ለከንቲባው እንዳይሔድ ተብሎ ትናንትና ታግዷል። ይኸ ከቀጠለ የከንቲባው ደኅንነት አደጋ ላይ ነው» ብለዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ተሰብስቦ ነበር የሚሉት አቶ አባስ ከሁለት ቀናት በኋላ «ከከንቲባው ጋር አብረን መስራት አንችልም፤ ከንቲባው ላይ እርምጃ ለመውሰድ እኛ ተስማምተናል»  የሚል መልዕክት ከካቢኔው አባላት ተነግሮኛል ብለዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ ካቢኔው ተሰብስቦ ያሳለፈው ውሳኔ አዲስ የተዋቀረው የከተማ አመራር ሊገመገም ይገባል የሚል መሆኑን ተናግረዋል።

Äthiopien Eskiyas Tafese Leiter für Regierungskommunikation
ምስል Dire Dawa Government Communication Affairs Bureau/Facebook

 

አቶ እስቅያስ «ከተማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረገው ግምገማ በአዲስ የተዋቀረ አመራር ስለሆነ ያለው ፤ከንቲባውም ከተማውን በመምራት ደረጃ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ካቢኔውንም አስተባብረው የተለዩ ቁልፍ ችግሮችን እየለዩ፣ እያስተባበሩ ከመሔድ አኳያ ክፍተት ስላለ፤ አጠቃላይ ኹኔታው አሁን ባለበት ደረጃ ከተሔደ የሚጠበቅብንን ውጤት እያስመዘገቡ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎች እንዲሁም በከተማው አስተማማኝ ሰላም እያሰፈኑ ከመሔድ ጋ ችግር የሚፈጥር ስለሆነ ይኼ ጉዳይ መገምገም አለበት በሚል ነው ያነሳንው» ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ መሐዲ ከኃላፊነታቸው የማንሳትም ሆነ የማገድ ውሳኔ እንዳልተላለፈ አቶ እስቅያስ ተናግረዋል። ለምክትል ከንቲባው የተመደበ ተሽከርካሪ ግልጋሎት እንዳይሰጥ የተላለፈ ውሳኔ የለም የሚሉት አቶ እስቅያስ በድሬዳዋ «የካቢኔው ውሳኔ በተጨባጭ እሳቸው በአካል ባሉበት፤ በተገኙበት ግምገማ ተደርጎ፤ ፓርቲ ፅህፈት ቤቶች አገማግመውን ውሳኔ እንዲቀመጥ እንፈልጋለን የሚል ነው» ብለዋል። የኢሕአዴግ እና የሶዴፓ ፅህፈት ቤቶች ሐሳቡን ተቀብለው ምክትል ከንቲባው ከውጭ አገር ጉዟቸው ሲመለሱ ግምገማ እንዲደረግ ድምዳሜ ላይ መደረሱን ኃላፊው አስረድተዋል።

ስለጉዳዩ «እንደ ድርጅት የምናውቀው ነገር የለም» ያሉት አቶ አባስ «የድሬዳዋን ሶዴፓ አንገት የማስደፋት ሥራ ነው እየተሰራ ያለው» ሲሉ ተናግረዋል። አቶ መሐዲ እና አቶ አባስ እንደሚሉት በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ የሶዴፓ አመራሮች በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ወደ ጅግጅጋ ተጠርተዋል።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ