1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድምፅ ይዘቶችን በበይነመረብ የማሰራጨት ጅምር

ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2015

ቴክኖሎጅ የሰዎችን የአኗኗር ዘይቬ ከማሻሻል ባሻገር መረጃ የማግኛ መንገድንም ቀይሯል። በቴሌቪዥን፣በሬዲዮ እና በጋዜጣ ላይ ብቻ የታጠረውን የሰዎች መረጃ የማግኘት ዕድል አሁን የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችሉ እንደ ፖድካስት ያሉ ዲጅታል የመገናኛ ዘዴዎች ተፈጥረዋል።

https://p.dw.com/p/4Rkd6
Äthiopien | Teraki Application

እያደገ የመጣው የበይነመረብ የድምፅ ይዘት ስርጭት


በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር በቀል መተግበሪያዎች አማካኝነት የተለያዩ የድምፅ ይዘቶችን  በበይነመረብ ዲጂታል በሆነ መንገድ ማሰራጨት እየተለመደ መጥቷል።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም በኢትዮጵ የድምፅ ይዘቶችን  በበይነመረብ የማሰራጨት  ጅምር  ላይ ያተኩራል።
ቴክኖሎጅ የሰዎችን የአኗኗር ዘይቬ ከማሻሻል  ባሻገር መረጃ የማግኛ መንገድንም ቀይሯል።በቴሌቪዥን፣በሬዲዮ እና በጋዜጣ ላይ ብቻ የታጠረውን የሰዎች መረጃ የማግኘት ዕድል አሁን የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችሉ እንደ ፖድካስት ያሉ ዲጅታል  የመገናኛ ዘዴዎች ተፈጥረዋል።
 ፖድካስቲንግ የድምፅ ይዘትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሰራጨት የታወቀ መገናኛ ዘዴ ነው። ይህ  ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ  በፍጥነት እያደገ ሲሆን በዓለም ዙሪያ 464.7 ሚሊዮን አድማጮች  እና ከ509 ሚሊዮን በላይ ፖድካስቶች በአፕል/Apple/ እና ስፖቲፋይ/Spotify/ በኩል ይቀርባሉ።

Spotify
ምስል Fabian Sommer/dpa/picture alliance

በኢትዮጵያም ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር በቀል መተግበሪያዎች አማካኝነት የተለያዩ የድምፅ ይዘቶችን  በበይነመረብ ዲጂታል በሆነ መንገድ ማሰራጨት እየተለመደ መጥቷል። ከነዚህም መካከል ተራኪ መተግበሪያ አንዱ ነው። የመተግበሪያው መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ናሆም ፀጋዬ እንደሚለው ይህ መተግበሪያ በኢትዮጵያ የድምፅ ይዘትን ዲጂታል በሆነ መንገድ በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን አድማጮች ያቀርባል።
ተራኪ ለወጣቶች እርስ በእርስ የሚያወሩበትን መንገድ ከፍቷል የሚለው ናሆም፤ከሁለት ዓመት ወዲህ መተግበሪያው በተለያዩ ጉዳዮች የሚያተኩሩ 95  የተለያዩ የድምፅ ይዘቶችን እያስተናገደ ይገኛል።ከነዚህም መካከል ጉጉት በሚል መጠሪያ የሚቀርበው ይዘት አንዱ ነው።ከይዘቱ ፈጣሪዎች  መካከል አንዱ የሆነው ብሩክ በልሁ እንደሚለው  ጉጉት ፖድካስት በተለያዩ መስኮች አርአያነት ያላቸው ሰዎችን እና ታሪኮችን በማቅረብ  አዝናኝ እና አስተማሪ  ዝግጅቶችን በዚሁ መተግበሪያ ያቀርባል።

Äthiopien | Team von Gugut Podcast
የጉጉት ፖድካስት አዘጋጆችምስል Biruk Belihu

በዚህ መልኩ ባለፉት ሁለት ዓመታት  ወደ 100 በሚጠጉ ክፍሎች የድምፅ ይዘቶችን  በማዘጋጄት  ከ2 ሚሊዮን በላይ እይታዎችን በማግኘት በአድማጭ ዘንድም ጥሩ ግብረ-መልስ እንዳለው ተናግሯል።
ብሩክ  እንደሚለው ከዚህ ቀደም  በተለያዩ ጉዳዮች ውይይቶችን የማቅረብ ሀሳብ ቢኖረውም ይህንን ፍላጎቱን የሚያስተናግድ አመቺ መድረክ አላገኘም ነበር።በመሆኑም መተግበሪው ለእሱና ለጓደኞቹ ያጡትን ዕድል ፈጥሯል። 
ነፃነት ፖድካስት ሌላው  በተራኪ መተግበሪያ የሚሰራጭ የድምፅ ይዘት ነው።አዘጋጇ ፅላተ ሰለሞን እንደምትገልፀው በእሷ እና በጓደኛዋ በፂዮን ብሩክ አማካኝነት ከዘጠኝ ወራት በፊት የተጀመረው ነፃነት ፖድካስት ከሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ያቀርባል። የዝግጅቱ ይዘትም  ወጣቶች ላይ የሚተኩር ነው።

Äthiopien | Netsanet Podcast
የነፃነት ፖድካስት አዘጋጆች ፅላተ ሰለሞን እና ፂዮን ብሩክ ምስል Tsilate Solomon

ፖድካስቲንግ ብዙ ጊዜ ለአድማጭ ቀረቤታ ያለው የመገናኛ ዘዴ ሲሆን፤በኢትዮጵያም  ከዓለም አቀፍ ይዘቶች ይልቅ  የሀገር ውስጥ ይዘት ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ወጣቶቹ ይገልፃሉ።ለዚህም ሰዎች ከእኩዮቻቸው ታሪኮችን ለመስማት እና ስለ ተሞክሯቸው ለማወቅ መፈለጋቸው ነው። ይህ አዝማሚያ  ከአካባቢው ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ይዘቶች  ተፈላጊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።እንደ ተራኪ ያሉ የሀገር ውስጥ ዲጅታል መድረኮች ደግሞ  ለይዘት ፈጣሪዎች እና ለአድማጮች በሀገር ውስጥ ቋንቋ የአካባቢ ጉዳዮችን በቀላሉ ለማቅረብ ያግዛል። በመደበኛው የራዲዮ እና የቴሌቪዥን ዝግጅቶች ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸውን ጉዳዮች ለመዳሰስም ፅላተ እንደምትለው ነፃነት ይሰጣል።
በሌላ በኩል ፖድካስት የተዘጋጁ የድምጽ ፋይሎችን ለተመዘገቡ ተጠቃሚዎች ዲጅታል በሆነ መንገድ ማሰራጨት ላይ ያተኮረ በመሆኑ፤ ፖድካስተሮች ወይም የይዘት አዘጋጆች  ይህንን አገልግሎት የሚገዙት  እንደ ሳውንድ ክላውድ ወይም ሊቢሲን ካሉ የፖድካስት ማስተናገጃ ኩባንያዎች ነው። አስተናጋጅ ኩባንያዎች እነዚህን የድምፅ ፋይሎች እንደ አፕል እና ስፖይቲፋይ ባሉ አገልግሎት ሰጪዎች አማካኝነት ለተጠቃሚዎች ይሰራጫል። ነገር ግን አገልግሎቱ ክፍያ የሚጠይቅ ሲሆን ክፍያው የሚፈፀመው ደግሞ  እንደ ፔይ ፓል እና ማስተር ካርድ ባሉ የክፍያ አማራጮች ነው።ይህ ደግሞ  በኢትዮጵያ ቀላል አይደለም። ከዚህ አንፃር ተራኪ መተግበሪያ  ለሀገር ውስጥ ይዘት ፈጣሪዎች ጥሩ መንገድ መሆኑን ወጣቶቹ ገልፀዋል።በሚቀርቡት ይዘቶች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችሉ መንገዶች እንዳሉ ናሆም ገልጿል።

Äthiopien | Nahom Tsegaye
ናሆም ፀጋዬ የተራኪ መተግበሪያ መስራች እና ስራ አስፈፃሚምስል privat

ፖድካስቶች በአብዛኛው ተጠቃሚው በነፃ በማውረድ የሚጠቀምባቸው በመሆናቸው፤ ገቢ የሚገኘው  በሚከፈል የደንበኝነት ምዝገባ፣ በማስታወቂያ እና በድርጅቶች ድጋፍ ነው።ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ  አንፃር አስቸጋሪ በመሆኑ ከገቢ አንፃር ያለው ፈተና ቀላል አለመሆኑን ብሩክ ገልጿል። የኢንተርኔት መቆራረጥ  ለዝግጅቱ የሚሆኑ የዲጅታል መሳሪያዎች  እና የስቱዲዮ ችግርም  ተግዳሮቶቹ ናቸው ።ዓለም አቀፍ ይዘቶችን ከሀገር በቀል  ባህል እና ልማድ ጋር አጣጥሞ ማቅረብም ፈተናዎች መሆናቸውን ሌላዋ አዘጋጅ  ፅላተ ሰለሞን ተናግራለች።ያም ሆኖ በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የድምፅ ይዘቶችን የማድመጥ ፍላጎት ከነችግሩም ቢሆን እያደገ መሆኑን ሁሉም ይስማሙበታል።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ