1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድምፃዊ ኮይሻ ሴታ አስተዋህፆ በወላይታ ባህል ላይ 

Merga Yonas Bula
ሐሙስ፣ ግንቦት 9 2010

በ1984 ዓ/ም ነበር  ኮይሻ የወላይታ ባህላዊ ሙዝቃዎችን ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮ ሙዚቃ ቤት አማካኝነት በካሴት በማሳተም ለአድማጮች ጆሮ ያደረሰዉ። ድምፃዊ ዓለማየሁ ዛሳ  ኮይሻ የመጀመርያ ካሴቱን ካሳተመበት ጀምሮ እስከ 2006 ዓ/ም የቅርብ የስራ ባልደረባዉ እንደነበር ይናገራል።

https://p.dw.com/p/2xpua
Karte Äthiopien englisch

የድምፃዊ ኮይሻ ሴታ አስተዋፅዖ በወላይታ ባህል ላይ 

የድምፃዊ ኮይሻ ሴታ የሙያዉ ጉዞ ብዙ ዉጣ ዉረዶች የነበረበት እንደነበረ የሚገልፀዉ የቅርብ የስራ ባልደረባዉ ኮይሻ ለረጅም ጊዜ ሲታመም እንደነበር ገልጿል። ባለፈዉ ዕሁድ በ50 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን አስታዉቋል።

የድምጻዊ ኮይሻ ሴታ የቀብር ስነ-ስረዓትም ሰኞ እለት ተወልዶ ባደገበት በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በዋላይታ ዞን በዳሞት-ዳሌ ወረዳ አደ-ዳሞት ቀበሌ መፈፀሙንም አክሎበታል። ድምጻዊ ዓለማየሁ የድምጻዊ ኮይሻን ስራ እንድህ ያስታዉሰዋል።

በኦሞቲክ የቋንቋ ቤተሰብ ዉስጥ የሚመደበዉ ወላይትኛ ባለፉት ፊዉዳላዊ ስረዓቶች፤ ከፍተኛ ጫና ደርሶበት እንደነበረ የባሕል ምሑራን ያመለክታሉ። የዋላይታን ባህልና ማንነት የሚያንፀባርቁ በተለይም የቋንቋና ታሪካዊ እውነታዎች ለሌላዉ ማህበረሰብ ለማድረስ ድምጻዊያን  እድል እንዳልነባራቸዉ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በወላይታ ዞን በባህል፤ ቱሪዝምና  ኮሙኒኬሼን ጉዳዮች መመርያ የባሕል፤ ታሪክና ቅርፅ ጥናትና ልማት የስራ ሒደት ቡድን መሪ አቶ አዳነ አይዛ ለዶይቼ ቬሌ ይናገራሉ። ድምፃዊ ኮይሻ ሴታ የዋላይታ ቋንቋ፤ ማንነትና ሌሎች የባሕል እሴቶችን በሙዚቃዉ ለህዝብ ያስተዋወቀ በመሆኑ  በሕዝቡ ልብ ዉስጥ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠር መቻሉን አቶ አዳነ አክለዉበታል።

አቶ አዳነ እንደሚሉት ድምፃዊ ኮይሻ ሴታ በዋናናት በሙዚቃዉ ያንፀባረቀዉ የባህል መገለጫዎች በሆነዉ በቋንቋ ነዉ። የኮይሻ የቅርብ  ባልደረባ ድምፃዊ ዓለማየሁ በበኩሉ የኮይሻ  በቋንቋዉ፤ በአለባበሱና በጭፈራዉ የማህበራዊ ትስስርን የሚያንፀባርቅ ሲሆን ሙዚቃዎቹ በይዘታቸዉ የታሪክ ጀግኖችን የሚወድሱ እንደሆነ ገልጿል።

የታታሪክ ና ቅርፅ ጥናትና ልማት ስራ ሂደት ቡድን መሪዉ አቶ አዳነ ድምፃዊ ኮይሻ በሙዝቃ ስራዎቹ የዋላይታን ባሕል ከማስተዋወቅ አልፎ ዛሬ እሱ ያዜማቸዉ ዘፈኖች በኢትዮጵያ ፕርምያር ሊግ የቡና እግር ኳስ ክለብ አንደ መዝሙር ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ድምፃዊ ኮይሻ ሴታ ያቀነቀናቸዉ ዘፈኖች ቀደም ስል የሕዝብ ዜማ እንደነበረ ድምጻዊ ዓለማየሁ  ይናገራል። ድምፃዊ ኮይሻ የራሱ ድርሰትና ዜማ ባይኖረዉም በጊዜዉ የሕዝብ የሆነዉን ድርሰትና ዜማ በራሱ ድምፅ አሳምሮ፣ መልክ አሲይዞ መዝፈኑ፤ በካሴት አሳትሞ ለአድማጮች ጆሮ ማድረስ መቻሉ እንደሚያስደንቀዉ ድምፃዊዉ ዓለማየሁ ይናገራል። ከዛም አልፎ ድምፃዊ ኮይሻ ለሌሎቹም ድምፅዊያን ምሳሌ መሆን እንደቻለም የታርክና ቅርፅ ጥናትና ልማት የስራ ሒደት ቡድን መሪ አቶ አዳነ ያክሉበታል።

ድምፃዊ ኮይሻ ሴታ  በድምፁ ብቻ ሳይሆን በመድረክ ላይ በሚያሳያቸዉ የወገብ በታች ጭፈራዎች እንደሚታወቅ አቶ አዳነ ይናገራሉ። ይህም በሃዘንና በደስታ ጊዜ እንደሚጨፈርም አክለዉበታል።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አሁን ያለዉ ከፍተኛ የቅጂ መብት ጥሰት የብዙ ድምጻዊያን ስራን ከንቱ ማድረጉ ይታወቃል። ድምፃዊ ኮይሽ ሴታ ተመሳሳይ እድል አጋጥሞት እንደ ነበረ የታርክና ቅርፅ ጥናትና ልማት ስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ አዳነ ይናገራሉ።

ኮይሻ የመጀመርያዉን አልበም ካሳተመ በዋላ ሌላ አልበም አለመስራቱን የሚናገረዉ የስራ ባልደረባዉ ድምፃዊ ዓለማየሁ ግን መኖርያዉን አዲስ አበባ በማድረግ ከተለያዩ ባንዶች ጋር በአገር ዉስጥና በባሕር-ማዶ በመጓዝ የዋላይታን ባሕል በስራዉ ለዓለም ማስተዋወቁን አክሎበታል። ድምፃዊ ኮይሻ በዚህ ስራ እያለ የመኪና አደጋ አጋጥሞት፤ ለሕክምናዉና ለእለት ኑሮዉ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር አጋጥሞት እንደነበረ ድምፃዊ ዓለማየሁ ያስታዉሳል።

ለኮይሻን ዕረፍት  ሐዘናቸዉን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  የገለፁ ነበሩ። ግሩም ተ/ሀይማኖት የሚል የፌስቡክ ስም ያለዉ «የማይታይ ክብር» በሚል ርዕስ በገፁ ላይ ካሰፈረዉ ግጥም እነዚህ ስንኞች ይገኙበታል።

ኡኡኡ አትበሉ..ከቶም አታልቅሱ
ወከባ አታንግሱ..ያልሆነ አታልብሱ
ከሞተ በኋላ ተዉ አታወድሱ
አትዘክሩት ይቅር ስራው ይዘክረው
መታሰቢያ ምሽት 
ሻማውስ ምኑ ነው?
ቢበራ ባይበራ ከሞት ላያስቀረው…

ሲል ይቀጥላል።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ