1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድምፃዊ ሓጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተቃውሞ ቀሰቀሰ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 23 2012

ትናንት ምሽት ድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ አዲስ አበባ፣ አምቦ፣ ጅማ እና ሐረርን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ ተቀስቅሷል። የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ የአዲስ አበባ ስቱዲዮ ሰራተኞች መታሰራቸውን አስታውቋል። የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።

https://p.dw.com/p/3eZQh
Äthiopien Addis Ababa Odaa Award Zeremonie
ምስል Odaa Award

የድምፃዊ ሓጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ከተሞች ከባድ ተቃውሞ ቀሰቀሰ። ወደ አምቦ በመጓዝ ላይ የነበረው የሐጫሉ አስከሬን በተቃዋሚዎች ግፊት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ መደረጉ ተሰምቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ትናንት ለሊቱን ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት ማብራሪያ ድምፃዊ ሐጫሉ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ልዩ ስሙ ገላን ኮንደሚንየም አካባቢ በጥይት መገደሉን አረጋግጠዋል። "የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች" መያዛቸውንም ፖሊስ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ለግድያው "ታጣቂዎችን" ተጠያቂ አድርጓል። 

Ras Makonnens Statue wurde von Demonstranten abgerissen
በሐረር በተቃዋሚዎች የፈረሰው የራስ መኮንን ሐውልት ምስል Privat

ግድያው ለሊቱን ከቀሰቀሰው ቁጣ በኋላ ማክሰኞ ማለዳ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች እረጭ ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። ወደ አዲስ አበባ መግቢያ እና መውጪያ አውራ ጎዳዎች ውጥረት መንገሱን ዶይቼ ቬለ ለማረጋገጥ ችሏል። ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ሐጫሉ ተወልዶ ባደገባት በአምቦ፣ ሻሸመኔ እና ባሌ አካባቢዎች ወጣቶች አደባባይ በመውጣት ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።

በሐረር ከተማ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በከተማው ይገኝ የነበረ ሐውልት መፍረሱን የዶይቼ ቬለ ወኪል ከአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጧል። በከተማው የነበረው የራስ መኮንን ሐውልት ፈርሶ በተቃዋሚዎች ሲጎተት የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ድረ ገፆች ተሰራጭተዋል። የድሬዳዋ ከተማ በሥጋት ውስጥ ስትሆን በአካባቢው የተቃውሞ ፍንጮች ታይተዋል። የጥይት ተኩስ ድምፅም ተሰምቷል።

Äthiopien Addis Ababa Odaa Award Zeremonie
ሐጫሉ ሁንዴሳ በኦዳ ሽልማትምስል Odaa Award

በጅማ ከተማ ጎዳናዎች ተሽከርካሪዎች ተቃጥለው ሆቴሎች መሰባበራቸውን ዶይቼ ቬለ አረጋግጧል። በአዳማ የከንቲባ ጽህፈት ቤትን ጨምሮ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በግድያው የተቆጡ ሰልፈኞች የጥቃት ዒላማ ሆነዋል። በከተማዋ የሚገኘው እና የክልሉ መንግሥት የሚያስተዳድረው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ጽህፈት ቤት ላይ ጥቃት ተሞክሮ በጸጥታ አስከባሪዎች ከሽፏል ተብሏል።

የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ የአዲስ አበባ ስቱዲዮ ሰራተኞች በፌድራል የጸጥታ አስከባሪዎች መያዛቸውን በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፁ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ የሐጫሉ ግድያ ከተሰማበት ቅፅበት ጀምሮ በተከታታይ በኩነቱ ላይ አተኩሮ ሥርጭት ሲያከናውን ቆይቷል። 

የ36 አመቱ ሐጫሉ ባቀነቀናቸው ሙዚቃዎች ከፍተኛ ተቀባይነት እና ተደማጭነት የነበረው ድምጻዊ ነው። የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ሳለ በጸጥታ ኃይሎች ተይዞ አምስት አመታትን በእስር አሳልፏል። ሐጫሉ ባለ ትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ነበር።

Äthiopien Addis Ababa Odaa Award Zeremonie
ሐጫሉ ሁንዴሳ በኦዳ ሽልማትምስል Odaa Award

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት ለሊቱን በይፋ የፌስቡክ ገፃቸው «ውድ ሕይወት አጥተናል። የዚህ ድንቅና አንፀባራቂ ወጣት አርቲስት ሓጫሉ ሁንዴሳ ህይወት መቀጠፍ ከተሰማ ጀምሮ በከባድ ሀዘን ውስጥ ለምንገኝ  ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁ» ብለዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው «ማንም ይሁን ማን ሃጫሉን የገደለው ሰው ከህግ ማምለጥ አይችልም። የእኩይ እና አስነዋሪ ስራውን ዋጋ በህግ ያገኛል» የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት በተደጋጋሚ እየተቋረጠ ነው። ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ለሰዓታት በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ተቋርጦ የነበረው ኢንተርኔት ሥራ ጀምሮ ነበር። ዘግየት ብሎ እንደገና መቋረጡን ዶይቼ ቬለ ለማረጋገጥ ችሏል።  

የኢንተርኔት አገልግሎት አሰጣጥን የሚከታተለው ኔትብሎክስ መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ተዘግቷል። በመረጃው መሠረት በመደበኛ እና በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚቀርበው ግልጋሎት ተቋርጧል። ይኸ ከዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ግልጋሎት መቆራረጥም ሆነ ከቴክኒካዊ ዕክል ጋር የተገናኘ አይደለም። ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ገደማ የነበረው የኢንተርኔት ግንኙነት 1% እና 2% በመቶ ብቻ የተወሰነ ነው።