1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የሕግ አገልግሎት ማዕከል

ዓርብ፣ ሚያዝያ 25 2011

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የሕግ አገልግሎት ማዕከል በአካባቢው በሚገኙ ሰባት ከተሞች አገልግሎት ይሰጣል። ተማሪዎቹ አቅም ለሌላቸው ሰዎች የሕግ አገልግሎት የሚሰጠው ይኸው ማዕከል ወጣት የህግ ተማሪዎች በንድፈ-ሐሳብ የተማሩትን በተግባር የሚፈትሹበት ነው።

https://p.dw.com/p/3HrKj
Äthiopien Rechtsberatung an der Universität Dilla | Sisay Girma
ምስል DW/Shewangizaw Wegayehu

ነፃ የሕግ አገልግሎት ማዕከል በዲላ ዩኒቨርሲቲ

በኢትዮጵያ በየአካባቢው የሚስተዋሉ የበጎ ፍቃድ አግልግሎቶች የአገሪቱ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ የመሳተፍ ልምዳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ አመላካች ተደርገው ሊጠቀሱ ይችላሉ። በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት በክረምት ወራት ብቻ ይከናወኑ የነበሩ የወጣት ተማሪዎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች አሁን አሁን በትምህርት መስጫ ወራቶችም ጭምር ሲከናወኑ ማየት እየተለመደ መጥቷል። ከእነኝህም መካከል በደቡብ ክልል በምትገኘው የዲላ ከተማና አካባቢዋ ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የማህበረሰብ አገልግሎት ማዕከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል። 

ከጥቂት ዓመታት በፊት በዲላ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት እንደተመሰረተ ይነገርለታል ፣ የዲላ ነፃ የህግ አገልግሎት ማዕከል።  ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት የዲላ ከተማን ጨምሮ በሰባት አነስተኛ ከተሞች ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። 

በማዕከሉ ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት እያበረከቱ የሚገኙት በአብዛኛው በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ወጣት ተማሪዎች ናቸው። 
በዲላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ብርቱካን በቀለ በነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑትና በማዕከሉ ቅጥር ገቢ ካገኘኋቸው ተጠቃሚዎች መካከል አንዷ ናቸው። 
ወይዘሮዋ በትዳራቸው ያጋጠማቸው አለመግባባት በፊቺ ቢደመደምም በንብረት ክፍፍል ረገድ ማግኘት የሚገባችውን ጥቅሞች ለማስጠበቅ በማዕከሉ የበጎ ፍቃድ አገልጋዮች ነፃ የህግ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ይናገራሉ። 

Symbolbild Justitia Justizia
ምስል Imago

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ለህብረተሰቡ እያበረከተ ከሚገኘው ፋይዳ በተጓዳኝ ከንድፈ ሀሳባዊ ይልቅ በተግባር የመማር ወይም በፈረንጆቹ አባባል ( Learning by doing ) የሚባለውን የትምህርት ስነ ዘዴ አንዲከተል በተለይም በአገልግሎቱ እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣቶች የመረጃዎች አቀራረብና የችሎት ክርክሮችን ጨምሮ ዘርፉ የሚጠይቀውን እውቀትና ልምድ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል የጎላ ጠቀሜታ እያበረከተ እንደሚገኝ የአገልግሎቱ አስተባባሪ አቶ አካለወልድ ይናገራሉ። 
የአቶ አካለወልድ አስተያየትን የሚጋራው የበጎ ፍቃድ አገልጋዩና የህግ ተማሪው ሲሳይ ግርማ በማዕከሉ የነጻ አገልግሎት መስጠቱ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ያገኘውን የንድፈ ሀሳበ ዕውቀት በስራ ላይ ለማዋል እድል ፈጥሮልኛል ይላል። 

በእርግጥ በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በበጎ ፍቃድ ላይ ያተኮሩ ማህበራዊ አገልግሎቶች እየተበራከቱ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ አገልግሎቶች ሰፊ የዘላቂነት ችግር ይስተዋልባቸዋል። 

በአንድ ወቅት የት ይደርሳሉ ተብለው በዘመቻ የተጀመሩ ፣ በመሀል ግን የተነሱበትን ግብ ሳያሳኩ ደበዛቸው የጠፋ የማህበራዊ አገልግሎቶች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። 
በዚህ ረገድ ማዕከሉ የሚያቀርባቸውን አገልግሎቶች በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከበጎ ፍቃደኛ ተማሪዎች ጎን ለጎን የሚያገለግሉ ቂሚ ሰራተኞችን የመቅጠርና የማደራጀት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስተባባሪው አቶ አካለወልድ አመልክተዋል። 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ