1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደብረጽዮን ነው የተባለ የድምፅ ቅጂ ይፋ ሆነ

ታትሟል እሑድ፣ ጥር 23 2013የመጨረሻ ማሻሻያ ሰኞ፣ ጥር 24 2013

ድምጺ ወያነ ይፋ ባደረገው የድምጽ ቅጂ  ደብረጽዮን ናቸው የተባሉት ተናጋሪ "የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሔዱ የዘር ማጥፋት እና ፍጅት ተከፍቶበታል" የሚል ውንጀላ አቅርበዋል። "አራት መንግስታት እና የክልሎች ልዩ ኃይሎች የተሳተፉበት ትግራይ ላይ የተፈጸመ ወረራና ጦርነት በመሆኑ የኃይል አለመመጣጠን አጋጥሟል" ብለዋል። 

https://p.dw.com/p/3odnK
Äthiopien Konflikt in Tigray | Debretsion Gebremichael
ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ንብረት የሆነው ድምጺ ወያነ የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል "የትግራይ ሕዝብ የጀመረውን ትግል እንዲቀጥል" ጥሪ አደረጉበት የተባለ የድምጽ ቅጂ ይፋ አደረገ።  

ደብረጽዮን "ትግል ከሚካሄድበት የትግራይ ሜዳ" መልዕክት አስተላለፉበት የተባለው ይኸው የድምጽ ቅጂ በድምጺ ወያነ የፌስቡክ ገፅ በኩል ይፋ የሆነው ትናንት ቅዳሜ ጥር 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን አስራ ሶስት ደቂቃዎች ገደማ ይረዝማል። 

በዚሁ የድምጽ ቅጂ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ናቸው የተባሉት ተናጋሪ "የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሔዱ የዘር ማጥፋት እና ፍጅት ተከፍቶበታል" የሚል ውንጀላ አቅርበዋል። 

ሬውተርስ እና የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በእርግጥ ይኸ የድምጽ ቅጂ በትክክል የህወሓት ሊቀ-መንበር እና የቀድሞው ትግራይ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረሚካል ለመሆኑ ማረጋገጥ እንዳልቻሉ በጉዳዩ ላይ በሠሯቸው ዘገባዎች ጠቁመዋል። ዶይቼ ቬለም የድምጽ ቅጂውን ትክክለኛነት ማረጋጋጥ አልቻለም።  

ይኸ የድምጽ ቅጂ በእርግጥ የደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከሆነ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ ያስተላለፉት የመጀመሪያው መልዕክት መሆኑ ነው። 

በትግራይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ የፌድራል መንግሥቱ እና ክልላዊው መስተዳድር ውጊያ ከገጠሙ በኋላ ደብረጽዮን ከመገናኛ ብዙኃን ጠፍተው ቆይተዋል። ይሁንና እስከ ሕዳር የመጨረሻ ሳምንት ድረስ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ከጋዜጠኞች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች የተመጠኑ መልሶች ይሰጡ ነበር። 

ድምጺ ወያነ ይፋ ባደረገው እና በሺሕዎች የሚቆጠሩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ባጋሩት የድምጽ ቅጂ  ደብረጽዮን ናቸው የተባሉት ተናጋሪ "አራት መንግስታት እና የክልሎች ልዩ ኃይሎች የተሳተፉበት ትግራይ ላይ የተፈጸመ ወረራና ጦርነት በመሆኑ የኃይል አለመመጣጠን አጋጥሟል" ብለዋል።  ጊዜያዊ ያሉትን "ወታደራዊ ብልጫ ለመለወጥ የመመከት ትግላችንን አጠናክረን እያስቀጠልን እንገኛለን" ሲሉ ይደመጣል። 

በንግግራቸው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩትን የኢትዮጵያ መንግሥት፣ "የህግደፍ ስርዓት" ያሉትን የኤርትራ መንግሥት እንዲሁም "የትምክሕት" ያሏቸውን ኃይሎች  ከሰዋል። 

"አዛውንት ነባር ታጋዮች በዚህ የወረራ ጦርነት በጠላት እጅ ተጎደትውብናል። ከባድ መስዋዕትነት ከፍለዋል። አሁንም እየከፈሉ ይገኛሉ" ያሉት ተናጋሪ በትግራይ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች "በከባድ ጦር መሳሪያዎች የማያቋርጥ ድብደባ" እየተፈጸመ ነው የሚል ክስ በድምጽ ቅጂው አሰምተዋል። 

ደብረጽዮን ናቸው የተባሉት ተናጋሪ በድምጽ ቅጂው እንደሚሉት በትግራይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤ መድሐኒቶችን ጨምሮ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ተፈጽሟል። 

ድምጺ ወያነ የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ናቸው ባለው የድምጽ ቅጂ ተናጋሪው "እኛ ከመሬታችን እና ከቀያችን ለቀን የምንሄድበት ሌላ ቦታ የለንምና የተሟላ ድል እስክንቀዳጅ ሕዝባዊ ጦርነት ከማፋፋም ወደ ኋላ እንደማንል ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው ይገባል" የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም "ለወንጀለኛው ቡድን የፌስቡክ ገጽ የተወዛገቡ ሐሳቦች መልስ አልሰጥም" ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።

በሬውተርስ ዘገባ መሠረት ህወሓት እና የውጪ ደጋፊዎቻቸው ከጥቅምት ጀምሮ የራሳቸውን "አስከፊ ወንጀሎች ለመሸፋፈን" የዘር ማጥፋት እየተፈጸመ ነው የሚል ያልተጨበጠ ወሬ እየነዙ ነው ያሉት ቢልለኔ የውጭ አገራት እና ብዙኃን መገናኛዎች እንዲያጋልጧቸው ጠይቀዋል። 

የትግራይ ክልልን ለሁለት ዓመታት ገደማ በምክትል ርዕሰ-መስተዳድርነት ሲመሩ የቆዩት የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ከተካሔደው ምርጫ በኋላ ርዕሰ-መስተዳድር ሆነዋል። ይሁንና የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ደብረጽዮን ርዕሰ-መስተዳድር የሆኑበትን የምርጫ ውጤት "ሕገ-ወጥ" በማለት ውድቅ አድርጎታል።

ደብረጽዮን በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ከሚፈለጉ የህወሓት አመራሮች እና የትግራይ ክልል የቀድሞ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ናቸው። ከትናንት በስቲያ አርብ የኢትዮጵያ ፌድራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ እንደተናገሩት 96 የህወሓት አመራሮችን ጨምሮ የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው 349 ተጠርጣሪዎች መካከል 124 በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የድምጽ ቅጂውን ይፋ ያደረገው ድምጺ ወያነ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የደርግ መንግሥትን ለመጣል ባደረገው ትግል ወቅት ይጠቀምበት የነበረ ራዲዮ ነው። ጣቢያው ከራዲዮ በተጨማሪ የቴሌቭዥን ሥርጭት የነበረው ቢሆንም ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ ተቋርጧል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ