1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የባሕል ሳምንት

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2011

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የባሕል ሳምንት ለአራተኛ ጊዜ የተከበረው በወላይታ ሶዶ ከተማ ተከብሯል። ከአስራ አራት ዞኖች እና አራት ልዩ ወረዳዎች ወደ ሶዶ ከተማ ያቀኑ የኪነት ቡኖች የተለያዩ የሙዚቃ ሥራዎች አቅርበዋል። በበዓሉ አከባበር ላይ የክልሉ ነዋሪዎች ባሕላዊ የግጭት አፈታት ልምዶቻቸውን አንዳቸው ለሌላቸው እንዲያካፍሉ ተደርጓል።

https://p.dw.com/p/3KkwA
Äthiopien | Traditioneller Tanz in Wolita Sodo
ምስል DW/S. Wegayehu

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የባሕል ሳምንት

በኢትዮጵያ በየአካባቢው የሚስተዋሉት ጎሳ ተኮር ግጭቶችና እሰጥ አገባዎች ከተለመደው የፖለቲካዊ ርዕዮት ዓለም ፈትጊታ በእጅጉ የራቁ ስለመሆናቸው ብዙዎች ይስማማሉ ። ጥላቻ ፣ መፈናቀልና በማንነት ላይ የተኮሩ ጥቃቶች በቀደመው የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ታሪክ ውስጥ ብዙም ያልታዩና ያልተለመዱ ድርጊቶች አለመሆናቸው ብቻ አይደለም። በክስተቱ መሰረታዊ መንስኤ ላይ የጋራ መግባባት ላይ አለመደረሱ በራሱ ለችግሩ አመላካች መፍትሄዎች እንዳይኖሩት ምክንያት እየሆነ ይገኛል። 

በእርግጥ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ልሒቃን አሁን ለሚታዩት ጎሳ ተኮር ትንኮሳዎች መንስኤ የሚሏቸውን ሀሳቦች በየመድረኩ ከመሰንዘር ወደኋላ ያሉበት ጊዜ የለም ። 
በተለይም ህብረተሰቡ በረጅም ጊዜ ልምዱ ያካበታቸው ነባር ማህረሰባዊ እሴቶች እንደገደል አፈር አየተናዱ መምጣታቸው ህዝቡ አሁን ለገጠመው ችግር ተጋላጭ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ የሚሞግቱም በርካቶች ናቸው። በመሆኑም ህብረተሰቡ አለመግባባቶችን በራሱ መንገድ የሚፈታባቸውን ባህላዊ አሴቶችን መጠበቅና ማጎልበት አንደሚገባም በመፍትሄነት ይጠቁማሉ። 

Äthiopien | Traditioneller Tanz in Wolita Sodo
ምስል DW/S. Wegayehu

ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ሶዶ ከተማ የተካሄደው አራተኛው የደቡብ ክልል የባህል ሳምንት ዝግጅት ከልሒቃኑ ሀሳብ አንድ እርምጃ የቀደመ ይመስላል። በደቡብ ከልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያዘጋጀው የባህል ሳምንት የተካሄ ደው “ባህላችን ለሰላማችንና ለአብሮነታችን” የሚል ዓላማን በማንገብ ነው። በቢሮው የባህል ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታደሰ ለገሰ የዘንደሮ የባህል ሳምንት በክልሉ የሚገኙ ህዝቦች ያላቸውን ነባር ባህላዊ የግጭት አፈታት ልምዶቻቸውን የሚያስተዋውቁበትን እድል ፍጥሯል ይላሉ። 

በባህል ሳምንት ዝግጀቱ ላይ ከየብሄረሰቡ የታደሙ ተሳተፊዎች የየራሳቸውን ባህላዊ የግጭት አፈታት ልምዶቻቸውን በሙዚቃዊ ድራማና በጭውውት መልክ በማቅረብ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ይልቁንም በሌሎች ማህበረሰቦች በቀረቡት ላይም ሀሳባቸውን እንዲያጋሩ ፣ ልምዶቻቸውንም እንዲለዋወጡ ተደረጓል። ያነጋገርኳቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች አብዛኞቹ ባህላዊ ስርዓቶች አንዱ ከሌላው የሚቀራረብና ተወራራሽነት ያላቸው እንደሆኑ ለመገንዘብ መቻላቸውን ገልጸውልኛል። 

የሰው ልጅ በማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እስካለ ድረስ ግጭት አይቀሬና ተፈጥራዊም ጭምር ነው የሚሉት አቶ ታደሰ ለገሰ ነገር ግን አለመግባባቶችንና የሀሳብ ልዩነቶችን በአግባቡ መያዝና መፍታት እንደሚያሰፈልግ ጠቁመዋል። በዚህ ረገድ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ዘላቂ መፍትሄዎቸን ከማስገኘት አንዳር ከዘመናዊ የዳኝነት ስርዓት የተሻለ አቅምና ተቀባይነት እንዳላቸው ባለሙያው ተናግረዋል። በዚህ መነሻም እነኝህ ባህላዊ እሴቶች በባህል ሳምንት ዝግጀት ላይ መቅረባቸው ወጣቱ በባህሉ ዙሪያ የለውን ግንዛቤ ያጠናክራል የሚል እምነት እንዳላቸው ነው አቶ ታደሰ የገለፁት።በባህል ሳምንት ዝግጀት ላይ የተሳተፉ ወጣቶች በዓሉ ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ የማህበረሰብ አባላት ጋር ለመተዋወቅ እንዳስቻላቸው ይናገራሉ። በዝግጅቱ ላይ የቀረቡት ነባር ማሀበረሰባዊ እሴቶች በእነሱ ሳይወሰኑ ለትውልድ ሊተላለፉ ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

Äthiopien | SNNPR Kultur Woche
ምስል DW/S. Wegayehu

በእርግጥ ነባር ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ጠቃሚ ከሚባሉት ማሀበረሰባዊ እሴቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ቢሆኑም በሚመለከታቸው የባህል ተቋማት ተገቢውን ትኩረት ያገኙ አይመስልም ። ዘረፉን በቋሚነት የማስተዋወቅም ሆነ ተጨማሪ ጥናቶችን የማካሄድ ሰራዎች እምብዛም አይስተዋሉም ። የደቡብ ከልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ታደሰ ግን በቀጣይ የግጭት አፈታትን ጨምሮ ሌሎች አገር በቀል እውቀቶች ተኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይመክራሉ። 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ