1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ-ውሳኔ ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች

እሑድ፣ መስከረም 9 2014

በደቡብ ክልል የሚገኙ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በመጪው መስከረም 20 ሕዝበ-ውሳኔ ያካሒዳሉ። የሕዝበ-ውሳኔው ውጤት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አስራ አንደኛው ክልል ይቋቋም እንደሁ ይወስናል። በዚህ የውይይት መሰናዶ ለሕዝበ-ውሳኔው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያደረጋቸውን ዝግጅቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ይዳስሳል።

https://p.dw.com/p/40T7h
Karte Äthiopien Ethnien EN

እንወያይ፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ-ውሳኔ ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች

የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮ እና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች በመጪው መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ያቀናሉ። መራጮች የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ የዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን "ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመሥረታቸውን እደግፋለሁ" እንዲሁም "የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠላቸውን እደግፋለሁ" የሚል ምርጫ የሰፈረበት የድምጽ መስጫ ወረቀት በምርጫ ጣቢያዎች ይጠብቃቸዋል። ሕዝበ-ውሳኔው እንዲካሔድ ከታቀደበት ካለፈው ሰኔ የተራዘመው በጸጥታ ችግር ምክንያት ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጸጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ መጠናቀቁን አስታውቋል።

የዚህ ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አዲስ ክልል ይቋቋም እንደሁ ይወስናል። ውጤቱ አምስቱ ዞኖች እና አንዱ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመሥረታቸውን የሚደግፍ ከሆነ ለኢትዮጵያ ፌድራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስራ አንደኛው ክልል ይቋቋማል።

ከዚህ ቀደም በደቡብ ክልል ሥር ይገኝ በነበረው የሲዳማ ዞን ከቀረበ ጥያቄ በኋላ ሕዝበ-ውሳኔ ተካሒዷል። ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሔደ ሕዝበ-ውሳኔ ድምፅ ከሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች ከ98 በመቶ በላይ የሲዳማ ክልል እንዲመሰረት ደግፈዋል። በውሳኔው መሠረት የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በይፋ ተመስርቶ አስረኛው ክልል በመሆን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ተቀላቅሏል። ዎላይታን ጨምሮ በደቡብ ክልል ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። 

ይኸ ውይይት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚካሔደው ሕዝበ- ውሳኔ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩንኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ ኩሌ ኩርሻ እና በጀርመን ኦስናብሩክ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓት፣ ዴሞክራሲ እና ብሔር ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የፒኤችዲ ጥናታቸውን በማከናወን ላይ የሚገኙት አቶ አምባቸው አዲሱ በውይይቱ ተሳትፈዋል።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ