1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደምቢዶሎ ወጣት ግድያ የቤተሰቦች አስተያየትና የመንግስት ምላሽ

ዓርብ፣ ግንቦት 6 2013

“ልጃችን የምርጫ ካርድ ለመውሰድ በሚል ለእናቱ ተናግሮ ወጥቶ ከሰዓታት በኋላ እኔና እናቱን ወስደውን አስከሬኑን ካሳዩን በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን” “ተመልሰን አስከሬኑን በምንወስድበት ወቅት በፖሊስ ተደብድበን ባዶ እጃችን ገብተን አልቅሰናል” የሟች ወላጅ አባት

https://p.dw.com/p/3tPQe
Äthiopien Binishangul Gumuz  Region Metekel Zone Gilgel
ምስል DW/Negassa Desalegn

«አስከሬኑን በምንወስድበት ወቅትም በፖሊስ ተደብድበናል» ቤተሰብ


ማክሰኞ ግንቦት 03 ቀን 2013 ዓ.ም. በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ በአደባባይ ተገድሏል ስለ ተባለው ወጣት አማኑኤል ወንዲሙ የሚናገሩት ወላጅ አባቱ አቶ ወንዲሙ ከበደ ልጃቸው “ጧት ከቤት ወጥቶ ከሰዓታት በኋላ አደባባይ ላይ ተገድሎ መጣሉን” ነው፡፡አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ያጋሩት አቶ ወንዲሙ “ልጃችን የምርጫ ካርድ ለመውሰድ በሚል ለእናቱ ተናግሮ ወጥቶ ከሰዓታት በኋላ እኔና እናቱን ወስደውን አስከሬኑን ካሳዩን በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን” ብለዋል፡፡ “ተመልሰን አስከሬኑን በምንወስድበት ወቅትም በፖሊስ ድብደባ ደርሶብን ባዶ እጃችን ገብተን አልቅሰናል” ያሉት የሟች ወላጅ አባት፤ የኋላ ኋላ ግን በአከባቢው ሽማግሌ ጥረት የልጃቸውን አስከሬን ወስደው መቅበራቸውን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ግን በግድያው የተለየ ሪፖርት በአከባቢው ከተሰማሩት የጸጥታ አካላት እንደደረሳቸው ነው የሚገልጹት፡፡ “ወጣቱ ጥቃት ፈጽሞ ሲሸሽ መገደሉንና የአባቶርቤ አባል መሆኑን” መረጃው ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡ ይሁንና የወጣቱ ግድያ ላይ ተጨማሪ ምርመራዎች ተደርጎ ጥፋተኛ ካለ ይጠየቃልም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አማኑኤል ወንድሙ በአደባባይ በሰው ፊት መገደሉን በመግለጽ፤ መንግስት ግድያውን መርምሮ ‘ተገቢ’ ያለው እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል፡፡

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ