1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየካቲት 08 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 8 2013

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ፒየር ኤመሪክ አውባሜያንግ ሔትትሪክ በመሥራት አርሰናልን ለድል አብቅቷል። እንደ ማንቸስተር ሲቲ ሌስተር ሲቲም ሊቨርፑል ላይ በግብ ተምነሽንሾበታል። በሻምፒዮንስ ሊጉ ሊቨርፑል ነገ ማታ ከጀርመኑ ላይፕትሲሽ ጋር ይጋጠማል። በተመሳሳይ ሰአት የስፔኑ ባርሴሎና የፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ጃርሞን ይገጥማል።

https://p.dw.com/p/3pOGw
UEFA Champions League - Borussia Mönchengladbach - Manchester City FC
ምስል Jan Huebner/imago images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ፒየር ኤመሪክ አውባሜያንግ ሔትትሪክ በመሥራት አርሰናልን ለድል አብቅቷል። እንደ ማንቸስተር ሲቲ ሌስተር ሲቲም ሊቨርፑል ላይ በግብ ተምነሽንሾበታል። ሊቨርፑል የቊልቊለት ጉዞውን ተያይዞታል። በሻምፒዮንስ ሊጉ ሊቨርፑል ነገ ማታ ከጀርመኑ ላይፕትሲሽ ጋር ይጋጠማል። በተመሳሳይ ሰአት የስፔኑ ባርሴሎና የፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ጃርሞን ይገጥማል። ባርሴሎና በስፔን ላሊጋ ቅዳሜ ዕለት አላቬስን በሰፋ የግብ ልዩነት 5 ለ 1 ድል አድርጓል። በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድን ጨምሮ በርካታ ቡድኖች አቻ በመውጣት ነጥብ ጥለዋል። ባየርን ሙይንሽን ከታችኛው ዲቪዚዮን ካደገው አርሜኒያ ቢሌፌልድ ጋር ዛሬ ማታ ተስተካካይ ጨዋታውን ያደርጋል። በፈረንሳይ የቤት ውስጥ ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ እና አትሌት ጌትነት ዋለ አሸናፊ ኾነዋል። የዓለም ክብረ ወሰንን የሰበረችው አትሌት ጉዳፍ በውድድሩ ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያውያን ተይዞ የቆየውን ክብረ ወሰን መስበርም ችላለች። ስለ ውድድሩ እና ድሉ ከዶይቸ ቬለ (DW)ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጋለች።

ሻምፒዮንስ ሊግ

በሻምፒዮንስ ሊግ የአውሮጳ እግር ኳስ ፉክክር ነገ ማታ ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት ይከናወናሉ። የጀርመኑ ኤርቤ ላይፕትሲሽ የእንግሊዙ አቻው ሊቨርፑልን ይገጥማል። ባርሴሎና እና ፓሪ ሳንጃርሞም ተቀጣጥረዋል። በበነጋታው ረቡዕ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ የስፔኑ ሴቪያን እንዲሁም የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ከፖርቹጋሉ ፖርቶ ጋር ይፋለማሉ።  ዘንድሮ 16 ቡድኖች በደርሶ መልስ በሚያደርጉት ግጥሚያ ጀርመንን ወክለው የሚጋጠሙ ተሳታፊ ቡድኖች፦ ላይፕትሲሽ፣ ቦሩስያ ዶርትሙንድ፣ ባየር ሙይንሽን እና ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባህ ናቸው።

ስድስት የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ዋንጫዎችን የሰበሰበው ባየርን ሙይንሽን አሰልጣኝ ሐንስ ዲተር ፍሊክ
ስድስት የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ዋንጫዎችን የሰበሰበው ባየርን ሙይንሽን አሰልጣኝ ሐንስ ዲተር ፍሊክምስል Frank Hoermann/SvenSimon/picture alliance

እንደ ጀርመን ስፔንም በተመሳሳይ አራት ቡድኖቿ ዘንድሮ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ 16 ቡድን ፉክክር ውስጥ ገብተዋል። በሻምፒዮንስ ሊግ ስፔንን የሚወክሉ ቡድኖች፦ ባርሴሎና፣ ሴቪያ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ማድሪድ ናቸው።

የፊታችን ማክሰኞ ሳምንት፦ የስፔኑ ኃያል አትሌቲኮ ማድሪድ ከእንግሊዙ ቸልሲ፤ የጣሊያኑ ላትሲዮ ከጀርመኑ ሌላኛው ኃያል ቡድን ባየርን ሙይንሽን ጋር ይጫወታሉ። በበነጋታው ረቡዕ ዕለት በሚከናወኑ ግጥሚያዎች ደግሞ፦ የጀርመኑ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ከእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ፤ እንዲሁም የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከጣሊያኑ አታላንታ ቤርጋሞ ጋር ይፋለማሉ።

ነገ በሻምፒዮንስ ሊግ ከሊቨርፑል ጋር በሚያደርጉት ግጥሚያ የላይፕትሲሹ አሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማን ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ዐስታወቊ። ምንም እንኳን የሀገራቸው ልጅ ዬርገን ክሎፕ የሚያሰለጥኑት ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ በተሰጋጋሚ ሽንፈት ቢገጥመውም በሻምፒዮንስ ሊግ የረዥም ጊዜ ልምድ ያለው ብርቱ ተፎካካሪ መሆኑን መስክረዋል። የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በበኩላቸው ቡድናቸው በላይስተር ሲቲ 3 ለ1 ከተሸነፈ በኋላ በሰጡት መግለጫ በፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫ የማግኘት እድላቸው የከሰመ መሆኑን ዐሳውቀዋል። ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለውን የ13 ነጥብ ልዩነት ማጥበብ እና ማሸነፍ የማይሆን ነገር መሆኑን ጠቊመዋል።

ሁለቱ ጀርመናውያን አሰልጣኞች፦ የሊቨፑሉ ዬርገን ክሎፕ እና የላይፕትሲሹ ወጣቱ አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን
ሁለቱ ጀርመናውያን አሰልጣኞች፦ የሊቨፑሉ ዬርገን ክሎፕ እና የላይፕትሲሹ ወጣቱ አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማንምስል Dave Thompson/AP/dpa/picture alliance

በተቃራኒው የላይፕትሲሹ ጀርመናዊ አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን፦ የሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊግ ደካማ ውጤት ቡዳፔስት ውስጥ ነገ በሚኖረው ግጥሚያ ቦታ እንደሌለው ገልጠዋል። «ቡድኔ የሚገጥመው ከቆሰለ ቡጢኛ ጋር ነው ብዬ ማስጠንቀቅ የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም» ሲሉ ዛሬ ተናግረዋል። «በሻምፒዮንስ ሊጉ የውጤት ቀውስ የለባቸውም፤ በፕሬሚየር ሊጉ እንጂ» ሲሉም ሊቨርፑልን በጥንቃቄ እንደሚመለከቱ ይፋ አድርገዋል። በፕሬሚየር ሊጉ ሊቨርፑሎች ዋንጫ የማንሳት ዕድላቸው በመጥበቡም ሙሉ ትኩረታቸውን ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ እንደሚያደርጉም አይጠፋኝም ብለዋል። የናግልስማን ላይፕትሲሽ ሊቨርፑልን ነገ ቡዳፔስት ሐንጋሪ በሚገኘው ፑሽካሽ አሬና ስታዲየም የሚገጥመው ያለ ስዊድናዊው ጨዋታ ፈጣሪ ኤሚል ፎርስቤርግ ነው። ኤሚል ከጉልበት ጉዳቱ አሁንም አላገገመም። በኤሚል ምትክ ዳኒ ኦልሞ የአማካይ አጥቂ ክፍሉን ከዩሱፍ ፖልሰን እና ክሪስቶፈር ንኩንኩ ጋር ይሸፍናሉ ተብሎ ይጠበቃል።   

በሊቨርፑል በኩል ወሳኝ ተጨዋቾቹ መጎዳታቸው በሻምፒዮንስ ሊጉ ላይም ተጽዕኖውን እንዳያሳርፍ አስግቷል። ዋናው ተከላካይ ቪርጂል ቫን ጂክ፣ ጆ ጎሜዝ እና ጆ ማቲፕ በጉዳት እየተሰለፉ አይደለም። ምናልባት ዬርገን ክሎፕ አዲስ ያስፈረሙት ኦዛን ካባክን በተከላካይ መስመር ያሰልፉ ይሆናል። ናት ፊሊፕስ ገብቶም አምበሉ ጆርዳን ሔንደርሰን ወደ አማካይ መስመሩ ሊመለስም ይችላል። ሁሉንም ነገ መመልከት ነው።

የአውሮጳ ሊግ 32 ቡድኖች የሚያከናውኗቸው ግጥሚያዎችም ሐሙስ ይጀምራሉ። አርሰናል ከቤኔፊካ፣ ሬድ ስታር ቤልግሬድ ከኤሲ ሚላን፣ ሪያል ሶይሴዳድ ከማንቸስተር ዩናይትድ እንዲሁም ሊል ከአያክስ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ።  ላይስተር ሲቲ ከስላቪያ ፕራህ፣ ባዬር ሌቨርኩሰን ከያንግ ቦይስ እንዲሁም ቶትንሃም ሆትስፐር ከቮልፍስበርግ ጋር የሚጫወቱት ሐሙስ ዕለት ነው።

Fußball | Premier League | Wolverhampton - Southampton
ምስል Actionplus/picture alliance

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ቸልሲ ዛሬ ማታ ከኒውካስል ጋር ይጋጠማል። ቸልሲ ጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኹልን ከፈረንሳይ ካስመጣ በኋላ ለተደጋጋሚ ድል በቅቷል። አፍሪቃዊ ደም ያላቸው ወላጆች ያሉት ጀርመናዊው አንቶኒዮ ሩዲገር በቶማስ ቱኁል መምጣት ቡድኑ መነቃቃቱን ከስካይ ስፖርት ጋር ዛሬ ባደረገው ቃለ መጠይቅ ተናግሯል። ቸልሲ በቶማስ ቱኁል ስር ሆኖ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አንድም ጊዜ አልተሸነፈም፤ አራት ጊዜ በተከታታይም ድል አድርጓል። ቸልሲ በፕሬሚየር ሊጉ ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ በ14 ነጥብ ተበልጦ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛልል። ከበላዩ ሊቨርፑል 40 ነጥብ ይዞ አራኛ ነው፤ ግን ቸልሲ እንደ ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ከዚያም ላይስተር ሲቲ በ46 ነጥብ ሦስተኛ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ በተመሳሳይ 46 ግን በግብ ክፍያ ተበልጦ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት ከዌስት ብሮሚች ጋር ባደረገው ግጥሚያ አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ ተጋርቷል። ማንቸስተር ሲቲ 53 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ተኮፍሷል።

ሌላው ትናንት በተከናወነ ግጥሚያ አርሰናል ሊድስ ዩናይትድን 4 ለ2 አንኮታኩቷል። አርሰናል ከታች ባደገው ሊድስ ዩናይትድ ለሁለት ጊዜያት መሸነፉን በበርካታ ግብ ተበቅሏል።  ፒየር ኤመሪክ አውባሜያንግ ሔትትሪክ በሠራበት ግጥሚያ ሁለቱን በፍጹም ቅጣት ምት ነበር ያገባው። አርሰናል 34 ነጥብ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ፉልሃም፣ ዌስት ብሮሚች እና ሼፊልድ ዩናይትድ ከ18ኛ እስከ 20ኛ የመጨረሻ ደረጃ ተደርድረዋል።  

1. Bundesliga | 1. FC Köln v Eintracht Frankfurt
ምስል Kai Pfaffenbach/REUTERS

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች በአብዛኛው በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቊት። ትናንት ፍራንክፉርት ኮሎንን 2 ለ0 እንዲሁም ዐርብ ዕለት ላይፕትሲሽ አውግስቡርግን 2 ለ1 ከማሸነፋቸው ውጪ አጠቃላይ ጨዋታዎቹ በአቻ ተጠናቀዋል።  ትናንት ቮልስፍቡርግ ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ያለምንም ግብ ተለያይቷል።  ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች፦ ዑኒዮን ቤርሊን ከሻልከ ጋር እንዲሁም ብሬመን ከፍራይቡርግ ጋር ዜሮ ለዜሮ ወጥተዋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከሆፈንሃይም ብሎም ባየር ሌቨርኩሰን ከማይንትስ ጋር በተመሳሳይ ሁለት እኩል አጠናቀዋል። ሽቱትጋርት ከኼርታ ቤርሊን ጋር ያደረገው ጨዋታም የተጠናቀቀው አንድ እኩል በሆነ ውጤት ነው። ቡንደስሊጋውን ባየር ሙይንሽን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ48 ነጥብ ይመራል። ላይፕትሲሽ በ44 ይከተላል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት እንደቮልፍስቡርግ 39 ነጥብ አለው በግብ ክፍያ ልዩነት ግን ደረጃው ሦስኛ ነው። ሻልከ፣ ማይንትስ እና አርሜኒያ ቢሌፌልድ 9፣ 14 እና 17 ነጥብ ብቻ ይዘው በደረጃ ሰንጠረዡ ከታች 18ኛ እስከ 16ኛ ላይ ይገኛሉ።

አትሌቲክስ

ፈረንሳይ ቫል ድ ሩይ ውስጥ በተከናወነው የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያውያን ድል ቀንቷቸዋል። በ1,500 ሜትር የወንዶች ውድድር ጌትነት ዋለ 3 ደቂቃ ከ35.54 ሰከንድ በመሮጥ አንደኛ ወጥቷል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ለሜቻ ግርማ በ6 ማይክሮ ሰከንዶች ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃን ይዟል። በሴቶች የ800 ሜትር የሩጫ ፉክክር ደግሞ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ በኢትዮጵያውያን ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በመስበር አሸንፋለች። ጉዳፍ ውድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 1 ደቂቃ ከ57.52 ሰከንድ ነው። አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬን ከድሉ በኋላ የፓሪስ ወኪላችን ሃያማኖት ጥሩነህ አነጋግራታለች።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ባለፈው ሳምንትም በአስደናቂ አጨራረስ የ1500 ሜትር የሩጫ ፉክክሯን ክብረወሰን በመስበር ነበር ያሸነፈችው። እንደ ጎርጎሪዮሱ 2019 ዓ.ም በዓለም ከቤት ውጪ ፉክክር በ1500 ሜትር ሩጫ የነሐስ ተሸላሚ የነበረችው ጉዳፍ፦ «ሳምንቱ ጥሩ ሆኗል» ስትል ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አክላ ተናግራለች። ከጥቂት ቀናት በፊት ተካሂዶ በነበረው የሊዮቫ የአዳርሽ ውስጥ የሦስት ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክር አትሌት ጌትነት ዋለም የዓለም ክብረ ወሰን ለመሰበር ለጥቂት ነበር ያመለጠው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ