1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ጦርነት፣የኢራን የአረቦችና የአሜሪካኖች ዛቻ

ሰኞ፣ መስከረም 19 2012

የነዳጅ ዘይት ማጣሪያና ማከማቺያን ማጋየቱ ሰላም ለማዉረድ ለሚፈልግ ከምልክትነትም በላይ ግልፅ ማስጠንቀቂያ በሆነ ነበር። የሪያድ-አቡዳቢ ነገስታትን ግን ዛሬም በየደሩሱበት ኢራንን ከማዉገዝ ሌላ የማይችሉት ጦርነት ስለሚቆምበት ብልሐት መናገሩን አልፈቀዱም ወይም ከበላይ አዝዦቻቸዉ አልተፈቀደላቸዉም።

https://p.dw.com/p/3QWLZ
Jemen Huthi-Rebellen zeigen mutmaßliche Aufnahmen saudischer Gefangener
ምስል Reuters/TV/Al Masirah/Houthi Military Media Center

የመን፣ የኃያላን፣ የነዳጅ ቱጃሮች እብሪት ማብረጃ ትሆን?

የሪያድ-አቡዳቢ፣ የዋሽግተን-ቴል አቪቭ መሪዎች ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ንግግራቸዉ እስከ ጋዜጣዊ መግለጫቸዉ ለየመኑ ጦርነት ኢራንን ሲወነጅሉ፣ በኢራን ላይ ሲዝቱም ሰነበቱ። የቴሕራን መሪዎች በርግጥ ለአፀፋ ዛቻ አልሰነፉም። የኃያል-ቱጃሮቹ ሐገራት መሪዎች ኒዮርክ ላይ በቃላት ሲጠዛጠዙ፣ የሁቲ አማፂያን በሺሕ የሚቆጠሩ የሳዑዲ አረቢና በሳዑዲ አረቢያ የተቀጠሩ ወታደሮች መግደል-መማረካቸዉን፣ አሜሪካ ሰራሽ ምርጥ የጦር መሳሪያ-ማዉደም መያዛቸዉን አዉጁ።  እሁድ። እዉነት ሐሰትነቱ አልተረጋገጠም። የጉባኤ ንግግሩ ፣ የመገናኛ ዘዴ መግለጫ፣ ዛቻ ፉከራዉ፣ የቢሊነ-ቢሊዮናት ዶላሩ ዘመናይ ጦር መሳሪያም ኃያል ቱጃሮቹን መንግሥታት ከተራ አማፂያን ጥቃት አለማዳኑ ግን በርግጥ የገሐድ «ሐቅ» ለነሱ ግን «ሕቅታ» ነዉ። 
ኢትዮጵያዊዉ የፖለቲካ ተንታኝና ደራሲ ዩሱፍ ያሲን፣ «ሁለቱ ሐገራት ይቀራረባሉ» ይላሉ፣ ሶስት ሲሆኑ ደግሞ በመልከዓ ምድር፣ በሕዝብ አስተሳሰብ፣በታሪክም ይመሳሰላሉ።
ከታላቁ አሌክሳንደር እስከ ሕንዱ ማዉርያ፣ ከአረብ ኻሊፋዎች እስከ ሞንጎሎች፣ ከፋርሳች እስከ አዉሮጶች የተፈራረቁባት አፍቃኒስታን በፖለቲካ ጥበብ እንጂ በነፍጥ ኃይል እንደማትገዛ ያስመሰከረችዉ ገና በ1840ዎቹ ነበር (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።)
የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች በ1842 ያዘመቱት 16ሺሕ ጦር አፍቃኒስታን መቀበሪያቸዉ እንደሆነች ሲያረጋግጡ ሐገሪቱን ለቀዉ ለመዉጣት ተገድዋል።ይሁንና የሶቭየት ሕብረት ኮሚንስቶች ከብሪታንያ ብጤዎቻቸዉ ታሪክ የተማሩ አልመሰሉም። የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች 16ሺሕ ጦራቸዉን ለአፍቃኒስን ጋራ፣ ተራራ፣ጉጥ ስርጓጉጥ ገብረዉ በፈረጠጡ በ137ኛ ዓመት፣ በ1979 የሶቬየት ሕብረት ጦር አስቸጋሪዋ ምድር ተመሰገ። ተሸነፈም።
የኮሚንስታዊቱ ልዕለኃያል ሐገር ጦር ሽንፈት በቅጡ ተዘግቦ ሳያበቃ የምድራችን ልዕለ ኃያልነቱን መንበር ያለተቀናቃኝ የያዘችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ድፍን ዓለምን አስከትላ አፍቃኒስታን ዘመተች። አስራ-ስምንት ዓመት በፈጀዉ ጦርነት ብዙ ሺሕ ሕዝብ አልቋል። በአስር ሺሕ የሚቆጠር ወታደር ተገድሏል። በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ጠፍቷል። ደሐይቱ ሐገር ወድማለች። አሸናፊ ግን የለም።አሜሪካኖች ቢጨንቃቸዉ ሊያጠፋቸዉ ከዘመቱባቸዉ ታሊባኖች ጋር ይደራደሩ ይዘዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሳባዎች፣ ሮሞች፣ ቱርኮች፣ ግብፆች፣ ብሪታንያዎች፣ ሶቭየቶች የተፈራረቁባት የመንም ወራሪዎች ከቀዳሚዎቻቸዉ ጥፋት የማይመሩባት፣ በገንዘብ ኃይል፣ በወታደር ብዛት፣ በጦር መሳሪያ ብልጫ የሚታበዩባት ሐገር ናት።
የሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ገዢዎች አንሳር አላሕ የሚባሉትን የሁቲ አማፂያንን ለማጥፋት የካይሮ፣ የራባት፣ የካርቱም፣ የዳካር ታዛዦቻቸዉን አስከትለዉ ደኃይቱን አረባዊት ሐገር ከወረሩ እነሆ ዘንድሮ አራት ዓመት ከመንፈቅ አለፋቸዉ። ቢዘገይ  በወራት እድሜ ሁቲዎችን እንደሚያጠፋ የተፎከረለት ዘመቻ እነሆ ዛሬ የመንን ተሻግሮ የጦርነቱን ግንባር ቀደም ለኳሽ ሳዑዲ አረቢያን እየነደደ-ገዢዎችዋን በሐፍረት እያናደደ- ነዉ።
                              
በጦርነቱ ከሰባ ሺሕ በላይ የመናዊ አልቋል።አብዛኛዉ ሕዝብ ያለቀዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር በሚጥለዉ ቦምብና ሚሳዬል ነዉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ 25 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሐገሪቱ ሕዝብ 22 ሚሊዮኑ አንድም በረሐብ፣ሁለትም በበሽታ ይማቅቃል።እልቂት ጥፋቱ ሰላም ለማዉረድ ከበቂ በላይ ምልክት በሆነ ነበር።
ጦርነቱ እዚያዉ የመን ዉስጥ ከሚያደርሰዉ ጥፋት አልፎ የሳዑዲ አረቢያን አዉሮፕላን ማረፊያዎች፣ ከተሞች፣ የነዳጅ ዘይት መርከቦች፣ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያና ማከማቺያን ማጋየቱ ሰላም ለማዉረድ ለሚፈልግ ከምልክትነትም በላይ ግልፅ ማስጠንቀቂያ በሆነ ነበር።የሪያድ-አቡዳቢ ነገስታትን ግን ዛሬም በየደሩሱበት ኢራንን ከማዉገዝ ሌላ የማይችሉት ጦርነት ስለሚቆምበት ብልሐት መናገሩን አልፈቀዱም ወይም ከበላይ አዝዦቻቸዉ አልተፈቀደላቸዉም።የሳዑዲ አረቢያዉ አልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ኮሎምቢያ ብሮድ ካስቲንግ ሲስተም (CBS-በምሕፃሩ) ለተባለዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በአስተርጓሚ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ደግሞ ኢራንን ከማዉገዝ አልፈዉ ዓለም በኢራን ላይ እንዲዘምት ጠይቀዋል።
«የኢራንን እርምጃ ለመግታት ዓለም ጠንካራና ቁርጠኛ እርምጃ ካልወሰደ፣ ዓለምን  የሚያሰጋ የባሰ ቀዉስ ያጋጥመናል።የነዳጅ ዘይት አቅርቦት ይቋረጣል፣ የዳጅ ዘይት ዋጋ፣ በሕይወታችን አይተነዉ በማናቀዉ ደረጃ ያሻቅባል።»
ለሳዑዲ አረቢያና ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከምርጥ ተዋጊ ጀቶች እስከ ዘመናይ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች፣ ከረቂቅ ሚሳዬል እስከ ዘመናይ ሚሳዬል አክሻፊ ሚሳዬል የሚያስታጥቁት ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያና ፈረንሳይ ናቸዉ። የመንን የሚያወድመዉ የአረብ ሐገራት ጦርን የሚያሰለጥኑ፣መረጃ የሚሰጡት፣የሚያማክሩት የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ባለሙያዎች ናቸዉ።
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈዉ ሳምንት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ግን ልክ እንደ ሳዑዲ አረቢያዉ አልጋወራሽ ሁሉ ኢራንን ላይ ከመዛት ሌላ በመንግሥታቸዉ የሚደገፉት መንግሥታት የድርድርን አማራጭ እንዲያዩ አልመከሩም።
                                     
«ሠላም ወዳድ መንግስታትን ባሁኑ ወቅት በጣም የሚያሰጋዉ ጨቋኙ የኢራን ሥርዓት ነዉ።የሥርዓቱ የግድያ፣የጥፋት ታሪክ በሁላችንም ዘንድ በቅጡ የታወቀ ነዉ።ኢራን አሸባሪዎችን ከሚደግፉ የዓለም መንግስታት አንደኛ ብቻ ሳትሆን፣ የኢራን መሪዎች ሶሪያና የመን ዉስጥ የሚደረጉ አሳዛኝ ጦርነቶችን ያጋግማሉ።»

Mohammed bin Salman Kronprinz Saudi Arabien
ምስል Getty Images/AFP/M. Ngan
Jemen Huthi-Rebellen zeigen mutmaßliche Aufnahmen saudischer Gefangener
ምስል Reuters/TV/Al Masirah/Houthi Military Media Center

በየመኑ ጦርነት ኢራን ካለችበት አሜሪካም፣ብሪታንያም፣ፈረንሳይም በቀጥታ ይባል በተዘዋዋሪ የጦርነቱ ዘዋሪ መሆናቸዉ ብዙ ተንታኖች ብዙ ጊዜ እንዳሉት በርግጥ አያጠያይቅም ።የኢራን ገዢዎችም ለሪያድ-አቡዳቢ ዋሽግተን ተባባሪዎች የሰጡት መልስ ካፀፋ ዉግዘት-ዛቻ ሌላ ለሰላም ጭላንጭል የሚከፍት አይነት አይደለም።ፕሬዝደንት ሐሰን ሩሐኑ ለጠቅላላ ጉባኤዉ ባደረጉት ንግግር ለየመኑ ጦርነትም ሆነ ሳዑዲ ላይ ለደረሰዉ ጥቃት የጦርነቱን ዘዋሪዎች ወንጅለዋል።
«የመንን የሚያነደዉ እሳት ወላፈን ዛሬ ሂጃዝን ቢለበልብ፣የጦርነቱ አቀጣጣዮች መቀጣት አለባቸዉ እንጂ ንፁሐንን ሊወቀሱ አይገባም።የሳዑዲ አረቢያ ሰላምና ደሕንነት የሚከበረዉ ወረራዉን ሲቆም እንጂ የዉጪ ኃይላትን በመጋበዝ አይደለም።በአረቢያ ልሳነ-ምድር ሰላም የሚወርደዉ፣የፋርስ ባሕረ-ሰላጤ ደሕንነት የሚከበረዉ እና የመካከለኛዉ ምሥራቅ መረጋጋት የሚሰፍነዉ በአካባቢዉ እንጂ ዉጪ ባሉ (ኃይላት) አይደለም።»
በጦርነቱ ኢራን፣ዩናይትድ ስቴትስ ወይም ሌሎቹ ተሳተፉም አልተሳተፉ እስካሁን አሸናፊና ተሸናፊ አለመኖሩ እርግጥ ነዉ።ኢራንን ጨምሮ የጦርነቱ አራማጆች ወይም አራማጅ የሚባሉት ኃይላት  የማይደራደሩበት ምክንያት አንዱ ሌላዉን የመጣል ድብቅ ዓላማን ከግብ ከማድረስ ሴራ ሌላ-ሌላ ምክንያት ማግኘት ሲበዛ ከባድ ነዉ።
የዋሽግተን ሪያድ፣አቡዳቢ መሪዎች ከቴሕራን አቻዎቻቸዉ ጋር ሲዛዛቱ የየመን ሁቲ አማፂያን በሳዑዲ አረቢያ ጠላታቸዉ ላይ ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ሁለተኛ ከባድ ለበቃቸዉን ማሳረፋቸዉ ነዉ-ጉዱን የዘለቀዉ ጉድ።የአማፂያኑ አዛዦች ትናንት ንዳስታወቁት ጦራቸዉ ነጅራን በተባለዉ የሳዑዲ አረቢያ ግዛት አጠገብ በሰፈረዉ የሳዑዲ አረቢያ ጦር ላይ በከፈተዉ ጥቃት መቶዎችን ገድሏል።በሺሕ የሚቆጠሩ ማርኳል።የአማፂያኑ ጦር ቃል አቀባይ ብርጌድየር ጄኔራል ያሕያ ሳሪያ
 «የጠላትን ቅስም የሰበረዉ ዘመቻ በመጀመሪያዎቹ ሰዓታት በርካታ ቡድናት ያሉትን የጠላት ጦር በመክበብ በፅኑ የተገነባዉን ምሽጋቸዉን ማጥቃት ነበር።በመጀመሪያዉ ቀን ዉጊያ በጣላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰናል።በርካታ የጦር መሳሪያዎች፤ በሺሕ የሚቆጠሩ የጠላት ወታደሮችና ቅጥረኞችን ማርከናል።»
አማፂያኑ ያሰራጩት ቪዲዮ የሳዑዲ አረቢያ ጦር አርማ የተለጠፉባቸዉ አሜሪካ ሰራሽ፣ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ የጦር ሜዳ መኪኖች፣የጦር መሳሪያዎች ሲጋዩ፣ ቆመዉ ወይም ሲሽከረከሩ ያሳያል።በሰልፍ ከሚግተለተሉት ምርኮኛ ወታደሮችም መሐልም የሳዑዲ አረቢያ ጦርን መለዮ ወይም ዩኒፎርም ያጠለቁ አሉባቸዉ።
ቃል አቀባይ ያሕያ ሳርያ እንዳሉት ጦራቸዉ በከፈተዉ ድንገተኛ ጥቃት 200 የሳዑዲ አረቢያ ወይም በሳዑዲ አረቢያ የተቀጠሩ ወታደሮች ገድሏል።2000 ማርኳል።ከምርከኞቹ መካከል 280ዎቹ ቆስለዉ የተያዙ ናቸዉ።ቃል ቀባዩ የሟች፣ቁስለኛ ምርኮዎቹን ዜግነት በዝርዝር አልተነገሩም።የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን እንደሚገምቱት ከየመን ወይም ከሳዑዲ አረቢያ ዜጎች በተጨማሪ ሱዳናዊ፣ ኢትዮጵያዊም ሊኖር ይችላል።
                                            
የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ካለፈዉ ቅዳሜ ጀምሮ በዓለም ስለናኘዉ የሽንፈታቸዉ ዜና እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ ያሉት ነገር የለም።አዣንስ ፍራንስ ፕሬዝስ እንደዘገበዉ ግን ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ በስደት የሚኖሩት የየመን ፕሬዝደንት የአብድ ረቦ መንሱር ሐዲ ባለስልጣናት 200 ወታደሮቻቸዉ መገደላቸዉን አምነዋል።የምርኮኞቹ ቁጥር ግን ሁቲዎቹ ካሉት ያነሰ ነዉ ከማለት ሌላ ዝርዝሩን አልተናገሩም። 
ሁቲዎች ሺዎችን መማረካቸዉን ባስታወቁ ማግስት ዛሬ 290 ምሮኮኞችን ለቅዋል።ምርኮኞቹን የተረከበዉ የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ እንዳስታወቀዉ የሁቲዎች እርምጃ የየመን ተፋላሚ ኃይላት ምርኮኞችን ለመለዋወጥ ከዚሕ ቀደም ያደረጉት ስምምነትን ገቢራዊ ለማድረግ እንደ ጥሩ ጅምር የሚታይ ነዉ።
የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት ደግሞ የምርኮኞቹ መለቀቅ የተዳፈነዉ ድርድር እንዲያንሰራራ የሩቁም ቢሆን  ተስፋ ሰጪ ነዉ።አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚያምኑት ግን ከምርኮኞቹ መለቀቅ ይልቅ የሁቲዎቹ ድል የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሐገር ዉስጥ ከገጠማቸዉ ፖለቲካዊ ቅሌት ጋር ተዳምሮ ተፋላሚዎችን ወደ ድርድር ሊያመጣ ይችላል።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን የኑክሌር መርሐ ግብርን ያስቆመዉን ዓለም አቀፍ ስምምነት ያፈረሱት ስምምነቱን ከሳቸዉ በፊት የነበሩትን ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ስለፈረሙት ብቻ ነዉ።የፀጥታዉ ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ሕግ ያደረገዉን ዉል በመጣሳቸዉ የሚደርስባቸዉን ወቀሳና ትችት ለመመከት ግን ኢራንን በሰበብ አስባቡ ማሳጣቱን እንደጥሩ የፖለቲካ ስልት ይዘዉታል።
ትራምፕ በፖለቲካ ቅሌት ሰበብ ከሐገራቸዉ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች የገጠማቸዉ ተቃዉሞ ፊታቸዉን ወደ ሐገር ዉስጡ ፖለቲካ እንዲያዞሩ ማስገደዱ አይቀርም።የትራምፕ ተፅዕኖና ድጋፍ ከቀነሰ ደግሞ ዩሱፍ ያሲን እና ብጤዎቻቸዉ እንደሚገሙትን የሪያድ-አቡዳቢ ገዚዎች የመን ዉስጥ ከተዘፈቁበት ኪሳራ ሰላማዊ መዉጪያ የመፈለግን ሐቅ-ሕቅ እያላቸዉም ቢሆን መቀበል ግድ ይሆናባቸዋል።

Jemen Huthi-Rebellen zeigen mutmaßliche Aufnahmen saudischer Gefangener
ምስል Reuters/TV/Al Masirah/Houthi Military Media Center
USA Maryland Präsident Trump
ምስል Reuters/J. Ernst
USA Hassan Rohani spricht vor der UN-Vollversammlung
ምስል AFP/D. Angerer

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ