1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዛሬው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ስብሰባ የግንባሩን ሊቀመንበር ለምን አገለለ?

እሑድ፣ ሐምሌ 19 2012

የዛሬው የጉለሌ ስብሰባ  በግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራ እና ከአርባ የጉሚ ሰባ የኮሚቴ አባላት አስራ አንዱን እንዲሁም ከጉሚ ሸኔ አባላት ደግሞ አምስቱን ብቻ በማሳተፍ አስራ ስድስት ሰዎች ብቻ እየተሳተፉበት ነው።

https://p.dw.com/p/3fwED
 Logo Oromo Liberation Front

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ አዲስ አበባ ጉለሌ በሚገኘው ጽ/ቤቱ እየተደረገ ያለው ስብሰባ ከግንባሩ መሪም ሆነ ከግንባሩ ጉባዔ እውቅና ውጭ መሆኑን አንድ የግንባሩ አመራር አባል ገለጹ። የዛሬው የጉለሌ ስብሰባ  በግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራ እና ከአርባ የጉሚ ሰባ የኮሚቴ አባላት አስራ አንዱን እንዲሁም ከጉሚ ሸኔ አባላት ደግሞ አምስቱን ብቻ በማሳተፍ አስራ ስድስት ሰዎች ብቻ እየተሳተፉበት  መሆኑንንም  የግንባሩ የፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በቴ ዑርጌሳ  ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። በግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር እየተመራ ነው የተባለው ይኸው ቡድን የግንባሩን ሊቀመንበር ጨምሮ ዋነኞቹ የግንባሩ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በሌሉበት የሚያደርገው ውይይት እና የሚወስናቸው ውሳኔዎች በእስር ላይ የሚገኙትን የግንባሩን አመራሮች የከእስር የሚያስለቅቅ እስካልሆነ እና አመራር ለመቀየር የሚደረግ ጥረት ከሆነ ተቀባይነት የለውም ብለዋል። የቡድኑ አባላት ስብሰባውን ለማካሄድ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ታግዘው ወደ ጽህፈት ቤቱ መምጣታቸው  መንግስት ግንባሩን  ለመቆጣጠር በሚያመቸው መንገድ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።«የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ከበቀደም ጀምረው ያንን አካባቢ ከበው ነበር ። ዛሬ ደግሞ የጽ/ቤት ጠባቂያችንን በግዴታ አስከፍተው ከመንግሥት ነው የተላክነው እዚህ ስብሰባ እንድናደርግ ተፈቅዶልናል። በሰላም ጉዳይ ላይም አብረን እንሰራለን ከፍታችሁ አስገቧቸው ብለው ጠባቂዎቻችንን አስገድደው አስገብተዋቸው አሁንስብሰባ እያደረጉ ነው።»የግንባሩ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመኖርያ ቤታቸው እንዳይወጡ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጥብቅ ጥበቃ ስር መውደቃቸውንም  አቶ በቴ ተናግረዋል። ቀደም ሲል የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎም ሆነ ከዚያ በፊት የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው የግንባሩ የስራ አስፈጻሚም ሆነ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የት እንደታሰሩ እና በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ እንማይታወቅ  አቶ በቴ አስረድተዋል።«እነዚህ አመራሮች ታሰሩ እንጂ የታሰሩበት ቦታ ፣ ለምን እንደታሰሩ ፣ ፍርድ ቤት መቼ እንደሚቀርቡ የሚታወቅ ነገር የለም። ቤተሰቦቻቸውም ሊጠይቋቸው አልቻሉም። በዚህም እኛም እንደ ድርጅት እነዚህን ሰዎች ስናፈላልግ ነበር። ለምን ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ የተለያዩ የፖሊስ ጣቢያዎችን ስናስስ ነበር። የፌዴራል ፣ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ፖሊስን ብንጠይቅም ልናገናቸው አልቻልንም። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ አጠቃላይ ጉባዔውን ሊያካሂድ  ከአራት እስከ አምስት ወራት ቀርተውት ነበር ያሉት አቶ በቴ አሁን በጥቂት ሰዎች አማካንነት የሚካሔደው ስብሰባ አላማው እና ግቡ እንደማይታወቅም ገልጸዋል። የግንባሩን ቀጣይ አቅጣጫ ለመናገር ግን ከስብሰባው በኋላ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ይወስናሉ ስሲሉም አቶ በቴ ዑርጌሳ ተናግረዋል።
ታምራት ዲንሳ