1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዕለተ ሰኞ የየካቲት 15/2013 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

ሰኞ፣ የካቲት 15 2013

የቻምፒየንስ ሊግ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት የሚደረጉ የመጀመርያ ዙር  በሳምንቱ የስራ ቀናት ይጠበቃሉ። ነገ ማክሰኞ የሚጀመሩ ቀሪ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት የሚደረጉ  ጫወታዎች ተጠባቂ ናቸው። በዚህም የስፔይኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ቼልሲን ሲያስተናግድ የጣልያኑ ላዚዮ የጀርመኑን ባየርን ሙንሽን በተመሳሳይ ሰዓት ያስተናግዳሉ።

https://p.dw.com/p/3pieu

ስፖርት

የቻምፒየንስ ሊግ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት የሚደረጉ የመጀመርያ ዙር  በሳምንቱ የሥራ ቀናት ይጠበቃሉ። ነገ ማክሰኞ የሚጀመሩ ቀሪ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት የሚደረጉ  ጫወታዎች ተጠባቂ ናቸው። በዚህም የስፔይኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ቼልሲን ሲያስተናግድ የጣልያኑ ላዚዮ የጀርመኑን ባየርን ሙንሽን በተመሳሳይ ሰዓት ያስተናግዳሉ። ረቡዕ ምሽት ደግሞ አትላንታ ሪያል ማድሪድን እንዲሁም ቦሩሽያ ሞንቼንግላድባህ ማንችስተር ሲቲን የሚያስተናግዱበት ተጠባቂ ጫወታዎች ናቸው ። በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 18 ጫወታዎችን በአሸናፊነት የመጣው ማንችስተር ሲቲ በሳምንቱ መጨረሻ በቡንደስሊጋው ጫወታ በሜዳው በማየንዝ ሽንፈት የቀመሰውን ሞንቼግላድባህን ሊያሸንፍ እንደሚችል ቅድመ ጫወታ ግምቶች  ያሳያሉ። ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው አራት ጫወታዎች ማንችስተር ሲቲ ሶስቱን ሲያሸንፍ አንዱን አቻ ተለያይተዋል። ሲቲ 11 ጎሎችን ከመረብ ሲያሳርፍ ሞንቼግላድባህ 4 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። ባሳለፍነው ሳምንት በአስራስድስተኛው ዙር የመጀመርያ ውድድሮች ፖርቶ ጁቬንቱስን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ሴቪያ በቦሩሽያ ዶርቱመንድ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት በሜዳው ተሸንፏል። ከዚያ ሁሉ ግን ምፓፔ ነግሶ ባመሸበት እና ፓሪሰን ዠርሜ ከሜዳው ውጭ ባርሴሎናን ገጥሞ በነበረው ጫወታ 4 ለ 1 ማሸነፉ አይዘነጋም ። በጫወታው ምፓፔ 3 ጎሎችን በማስቆጠር ሜሲን እና ባርሴሎናን አንገት አስደፍቷል። በእርግጥ ሻምፒየንስ ሊግ የመጀመርያው ዙር ውድድር ሊቀለበስ እንደሚችል በርካታ ተዓምራዊ ክስተቶችን አሳይቶናል። ለዚህም ባርሴሎና ከፈረንሳዩ ፓሪሰን ዠርሜ ጋር 2017 ላይ አድርገውት የነበረው የደርሶ መልስ ጫወታ አይረሴ አጋጣሚ ነበር ። ባርሴሎና ከሜዳው ውጭ 4 ለ 0 ተሸንፎ በሜዳው 6 ለ 1 በማሸነፍ በድምር ውጤት 6ለ5 በሆነ ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ በርካቶች በክስተትነቱ ዛሬም ድረስ ያስታውሱታል። ነገር ግን ባርሴሎና አሁን የተሸነፈው በሜዳው መሆኑ ከሜዳው ውጭ እንዴት ይቀለብሰዋል። በቀጣዩ ሳምንት የምናየው ይሆናል።

Fußball Champions League Barcelona Paris Mbappe  Tor
ምስል David Ramos/Getty Images
Fußball Champions League FC Sevilla - Borussia Dortmund Haaland
ምስል Angel Fernandez/AP Photo/picture alliance
Schweiz Nyon | Champions League | Auslosung Achtelfinale
ምስል UEFA/dpa/picture alliance

በሌላ በኩል አአውሮጳ ሊግ የዙር የጥሎ መለፍ ውድድሮች በያዝነው ሳምንት ይከናወናሉ። ከሜዳው ውጭ ፔሌትስን ገጥሞ 4 ለ 1 አሸንፎ የተመለሰው ቶተንሃም ሆትስፐር በሜዳው ሁለተኛውን ዙር ጫወታ ረቡዕ ምሽት ሲያስተናግድ ሆዜ ሞሪኒዮ ጫወታውን በቀላሉ አሸንፈው ወደ አስራ ስድስቱ ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ ተገምቷል። ሐሙስ ዕለት ከሚደረጉ በርካታ ጫወታዎች ውስጥ አርሴናል በሜዳው የሚያደርገው ጫወታ ተጠባቂ ነው። ከሜዳው ውጭ ቤኔፊካን የገጠመው አርሰናል አንድ አቻ ተለያይቶ መመለሱ በሜዳው ማሸነፍ አልያም 0ለ0 አቻ መውጣት አማራጮችን ይዞ ይገባል።  

ፕሪሚየር ሊግ

በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጠባቂ ጫዎታዎች ተከናውነዋል። ሊጉን በ10 ንጹህ ነጥቦች እየመራ የሚገኘው ማንችስተር የነጥብ ልዩነቱን አስጠብቆ የወጣበትን ጫወታ ትናንት ከአርሰናል ጋር አድርጎ በጠባብ የጎል ልዩነት አሸንፎ መውጣት ችሏል። የውድድር ዓመቱን በድንቅ ብቃት ተጋጣሚዎቹን እያንበረከከ ወደ ፊት በመጓዝ ላይ ያለው ሲቲ ከፕሪሚየር ሊጉ ውጭ ሌሎች ሶስት ዋንጫዎችን እያለመ ጉዞውን አጠናክሯል። በትናንቱ የኢሜሬትስ ጫወታ በመጀመርያዎቹ ሁለት ደቂቃዎች ስተርሊንግ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል አርሴናልን እንደተጠበቀው አሸንፎ የተመለሰው ሲቲ 18 ጫወታዎችን በተከታታይ ማሸነፍ የቻለበት ሆኖ ተመዝግቦለታል። ፕሪሚየር ሊጉን በስኬት እያስኬደ የሚገኘው ሲቲ በአመቱ በአጠቃላይ አራት ዋንጫዎችን እያሰበ ግስጋሴውን ተያይዞታል። የትናንቱ ተጋጣሚው እና ዘንድሮ ከምንግዜውም ይልቅ ወርዶ የታየው የሰሜን ለንደኑ አርሴናል ባልተጠበቀ አሰላለፉ በጠባብ የጎል ልዩነት መሸነፉ እንደ ዕድል ሲወሰድለት ምናልባትም በአቋራጭ ወደ ቻምፒየንስ ሊግ የሚወስደውን እና  ከፊቱ ለሚጠብቀው የአውሮጳ ሊግ ፍልሚያ ትኩረት ሳይሰጥ እንዳልቀረ ተገምቷል። አርሰናል ባለፈው ሐሙስ ከሜዳው ውጭ ቤኔፊካን ገጥሞ አንድ አቻ ተለያይተው ነበር ። አሁን በሜዳው የሚያደርገውን ጫወታ በአሸናፊነት መወጣት ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የግድ ይለዋል። በፕሪሚየር ሊጉ አራት ተከታታይ ጫወታዎችን  በመሸነፍ የውጤት ቀውስ የገባው ሊቨርፑል ከመሪው ማንችስተር ሲቲ በ19 ነጥቦች ርቆ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል። ኒው ካስትል ዩናይትድን አስተናግዶ 3:1 ያሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ ሁለተኛነቱን ሲያስጠብቅ፤ ከሜዳው ውች አስቶን ቪላን የገጠመው ሌይስተር ሲቲ 2:1 አሸንፎ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አቋሙን እያሳመረ የመጣው የዳቪስ ሞዬሱ ዌስትሃም ቶተንሃም ሆትስፐርን አስተናግዶ 2:1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ ማድረግ ችሏል። ቅዳሜ ዕለት በተደረጉ የሊጉ ጫወታዎች ሳውዝ ሀምፕተን ከቼልሲ አንድ አቻ ሲለያዩ ኤቨርተን ሊቨርፑልን በሜዳው ሁለት ለዜሮ አሸንፏል።  ፉልሀም ሼፊልድ ዩናይትድን አስተናግዶ 1:0 ሲያሸንፍ በርንሌይ ከዌስትብሮሚች አልብዮን ያለግብ አቻ ተለያይተዋል። ሊጉን ማንችስተር ሲቲ በ59 ነጥቦች ሲመራ ሼፊልድ ዩናይትድ በ11 ፣ ዌስት ብሮሚች አልብዮን በ14 እና ፉልሃም በ22 ነጥቦች ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ።

Fußball | Premier League | Manchester City - Crystal Palace
ምስል Clive Brunskill/PA Images/imago images

ቡንደስሊጋ

በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተጠባቂ የጀርመን ቡንደስሊጋ ጫወታዎች ተከናውነው መሪው መሪው ባየር ሙንሽን ሽንፈት ሲያስተናግድ ሶስቱ ተከታዮቹ ላይፕሲች ዎልስበርግ እና ኤይትራህት ፍራንክፈርት ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃቸውን አስጠብቀው ወጥተዋል። በሳምንቱ ተጠባቂ ከነበሩት ጫወታዎች ኤንትራህት ፍራንክፈርት በሜዳው መሪው ባየርን ሙንሽንን ያስተናገደበት ጫወታው ሲሆን 2:1 በማሸነፍ ባየር ሙኑሽን በስምንት ነጥቦች ሊጉን እንዲመራ የሚያደርገውን ዕድል አምክኖበታል። ባየር ሙንሽን ሁለቱን ጎሎች ከእረፍት በፊት በማስተናገዱ ሁለተኛውን 45 አክብዶበታል። የባየር ሙንሺኑ አጥቂ ሮበርት ልዋንዶውስኪ በዓመቱ በሊጉ 26ኛ እና ክለቡን ከሽንፈት መታደግ ያልቻለ ጎል አስቆጥሯል። ቅዳሜ ዕለት ተደርገው በነበሩ የቡንደስሊጋ ጫወታዎች ከሜዳው ውጭ የከተማ ደርቢው ሻልከ 04ን የገጠመው ቦሩሽያ ዶርትሙንድ ከእረፍት በፊት ሁለት ከእረፍት በኋላ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ በአጠቃላይ 4:0 በሆነ ሰፊ ውጤት ሲያሸንፍ ብራውት ሃላንድ በስሙ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። ዶርቱመንድ ከመሪው ባየርን ሙንሽን  በአስራሶስት ነጥቦች ዝቅ ብሎ በ36 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዕለቱ ስቱትጋርት ኮሎንን እንዲሁም ዩኒየን በርሊን ፍራይበርግን ከሜዳቸው ውጭ ተጉዘው በተመሳሳይ አንድ ለዜሮ አሸንፈዋል። በሌላ በኩል  ሜይንዝ 05 ቦሪሺያ ሞንቸግልድባህን በሜዳው 2:0 ድል አድርጎታል።

Fussball Bundesliga I Borussia Moenchengladbach - Mainz 05
ምስል Laci Perenyi/dpa/picture alliance
TSG Hoffenheim v SV Werder Bremen - Bundesliga
ምስል Alex Grimm/Getty Images

ትናንት እሁድ በተደረጉ ግጥሚያዎች ደግሞ ሆፈንሄም ቨርደርብሬመንን በሜዳው አስተናግዶ አራት ለምንም ሲሸኘው ላይፕሲች ሄርታ በርሊንን ከሜዳው ውጭ ገጥሞ ሶስት ለዜሮ በሆነ ሰፊ ጎል አሸንፎ ተመልሷል። ክለብ አውግስበርግ ከባየር ሊቨርኩሰን ጋር ያደረጉት ጫወታ አንድ አቻ ተጠናቋል ።ሊጉን ባየርን ሙንሽን በ49 ነጥቦች ሲመራ ላይፕሲች በ47 ይከተላል። ቮልስበርግ እና ኤይትራህት ፍራንክፈርት በእኩል 42 ነጥቦች በጎል ተበላልጠው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሻልከ 04 ፣ ማይንዝ 05 እና አርሚኒያ ቢሌፌልድ በሊጉ የወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ።

ሙዚቃ

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስራሁለተኛ ሳምንት ጫወታዎች ከሁለት ሳምንታት እረፍት በኋላ በተረኛ አስተናጋጇ የባህርዳር ከተማ ተጀምሯል። ሊጉን በሰባት ነጥብ ልዩነት መምራት የጀመረው ፋሲል ከነማ  ሐዋሳን 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። የሳምንቱ ጫወታዎች በባህርዳር ስቴዲየም ሲጀመሩ ባህር ዳር ከተማ ከወላይታ ዲቻ ያለ ግብ ሲለያዩ እስካሁን ምንም ጫወታ ሳያሸንፍ በሊጉ ግርጌ ላይ የነበረው ጅማ አባጅፋር ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፎ ነጥቡን 10 ማድረስ ችሏል። ሊጉን ፋሲል ከነማ በ25 ነጥቦች ሲመራ ኢትዮጵያ ቡና ሀዲያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ይከተላሉ። ጅማ አባ ጅፋር ፣ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛሉ።

ቴኒስ

ሰርቢያዊው የሜዳ ቴኒስ ንጉስ ኖቫክ ጆኮቪች 9ኛውን አውስትራሊያ ኦፕን ውድድር በማሸነፍ የውድድሩ ኮከብነቱን አስመስክሯል።  የ34 ዓመቱ ጆኮቪች ከዳኒል ሜድቬዴቭ ጋር በሜልቦርን የተደገውን ውድድር 7-5 6-2 6-2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።  ጆኮቪች ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት ደርሶበት የነበረው የሆድ ጡንቻ መሳሳብ  ለውድድሩ ሲያደርገው በነበረው ዝግጅት ላይ ችግር ፈጥሮበት  እንደነበር ገልጿል። በዚህም በውድድር ዘመኑ ገጥሞት የማያውቅ ከባዱን የውድድር ጊዜ ወይም ቶርናመንት ማሳለፉን ገልጿል። ጆኮቪች ውድድሩን በማሸነፍ 18ኛውን የግራንድ ስላም ዋንጫ ሲያነሳ ቁጥር አንድነቱን ማስጠበቅ ችሏል።

Tennis | Australian Open | Daniil Medvedev - Novak Djokovic
ምስል Daniel Pockett/Getty Images

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ