1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓይን የጤና ችግሮች

ማክሰኞ፣ ኅዳር 27 2015

በመላው ዓለም 2,2 ቢሊየን የሚሆን ህዝብ ከቅርብ ወይም ከርቀት የማየት ችግር እንዳለበት የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ነገር ግን ጤናማ የማየት አቅም እያለ ድንገት እክል የሚገጥመው በአብዛኛው ከ50 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ እንደሆነም የዓለም የጤና ድርጅት አጽንኦት ይሰጣል።

https://p.dw.com/p/4KYnv
Äthiopien Augenoperation in Bahir Dar Felege Hiwot Krankenhaus
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ጤና እና አካባቢ

 

በመላው ዓለም 2,2 ቢሊየን የሚሆን ህዝብ ከቅርብ ወይም ከርቀት የማየት ችግር እንዳለበት የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ድርጅቱ እንደሚለው ከሆነም ከእነዚህ ውስጥ ቢያንስ አንድ ቢሊየን የሚሆነው ህዝብ በቀላሉ ሊከላከሉት ወይም ደግሞ በህክምና ሊወገድ በሚችል የዓይን የጤና ችግር ምክንያት ነው የማየት እክል የገጠመው።

በዓይኔ መጣህ ወይም መጣሽ ይባላል፤ በማይቀለድ ነገር ሲቀለድ ወይም የማይደፈር ነገር ሲደፈር። ቅዱሱ መጽሐፍም «የሰውነት መብራት ዓይን ናት» ይላል። ብዙውን ጊዜ የማየት እክል የሚያጋጥመው አንድም አስቀድሞ ተገቢውን የህክምና ባለማግኘት አንድም በተለምዶ የዓይን ሞራ በሚባለው በህክምናው ካትራክት ተብሎ በሚታወቀው ችግር ምክንያት መሆኑን ነው የዓለም ጤና ድርጅት የሚያመለክተው።

የዓለም የጤና ድርጅት በመላው ዓለም 2,2 ቢሊየን የሚሆን ህዝብ ከቅርብ ወይም ከርቀት የማየት ችግር እንዳለበት ያመለክታል። የድርጅቱ መረጃ አክሎም ከእነዚህ ውስጥ ቢያንስ አንድ ቢሊየን የሚሆነው ህዝብ በቀላሉ ሊከላከሉት ወይም ደግሞ በህክምና ሊወገድ በሚችል የዓይን የጤና ችግር ምክንያት ነው የማየት እክል እንደገጠመውም ይገልጻል። የማየት እክል ባጋጠመው ግለሰብ ላይ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ፤ በማኅበረሰብ ብሎም በሀገር እና በዓለም ደረጃ የኤኮኖሚ ኪሳራን እንደሚያስከትልም አጽንኦት ይሰጣል።

Sehtest Symbolbild
የማየት አቅም ፈተናምስል McPHOTO/imago images

እርግጥ ነው ማየት ያለመቻል በየትኛውም ዕድሜ ሊያጋጥም ይችላል። በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ባለማግኘት የማየት እክል እንደሚያጋጥማቸው ከተገለጸው 1 ቢሊየን ሰዎች፤ 88,4 ሚሊየኑ መጠነኛ ሊባል በሚችል እንከን ከቅርብ ወይም ከርቀት ማየት እንደማይችሉ፤ 94 ሚሊየኑ ሊታከም በሚችለው የዓይን ሞራ ምክንያት፣ 8 ሚሊየኑ በዕድሜ ምክንያት ማኩላር የተባለው የዓይን ክፍል ላይ በሚያጋጥመው መዳከም፤ 7,7 ሚሊየኑ በግላኮማ ፤ 3,9 ሚሊየኑ ከስኳር ህመም ጋር በተገናኘ እክል፤ 826 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ የዓይን ብሌን የመለጠጥ አቅም ሲዳከም በሚከሰት ችግር ምክንያት የማየት አቅማቸው መዳከሙንም ይዘረዝራል።

ነገር ግን ጤናማ የማየት አቅም እያለ ድንገት እክል የሚገጥመው በአብዛኛው ከ50 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ እንደሆነም የዓለም የጤና ድርጅት አጽንኦት ይሰጣል።

Augentropfen Symbolbild
የዓይን ድርቀት ሲያጋጥም የሚደረግ የዓይን ጠብታ ምስል Shotshop/imago images

ስለዓይን ጤና ለመነጋገር መነሻ የሆኑን የዘወትር የዶቼ ቬለ አድማጭና ተሳታፊ የሆኑት የመቶ አለቃ ውቤ ታሪኩ ናቸው። አድማጫችን በግል እሳቸውም የተቸገሩበት መሆኑን ገልጸዋል። የላኩልን ጥያቄ፤

«ዓይኔ ላይ ተደጋጋሚ የሞራ ግርዶሽ ያጋጥመኛል በተደጋጋሚ ቀዶ ጥገና አድርጌ አለሁ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተመልሶ ሪከር ያደርጋል። በዓይን ላይ የሚከሰቱ ችግሮች ብዙ ናቸው ከነዚህም መካከል በሕክምናው አጠራር river blindness፣ cateract የሚባሉት ናቸው። የእነዚህ በሽታዎች መንሴአቸው ምንድን ነው። በዕድሜ ደረጃ የሚከሰቱ ናቸው ወይስ ዕድሜ ሳይለዩ ነው የሚያጋጥሙት።መድኃኒታቸውስ መደረግ ያለበት ጥንቃቄስ? ሕክምናውስ? ስለ ትብብራችሁ በቅድሚያ አመሰግናለሁ። ይህ ጥያቄ እኔም በግሌ የተቸገርኩበት ስለሆነ መልስ ትሰጡኛላችሁ ብየ ተሰፋ አለኝ።» የሚል ነው። የዘወትር አድማጫችን መቶ አለቃ ውቤን በቅድሚያ እናመሰግናለን። ጥያቄዎችዎን በመያዝ የዓይን ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑትን ዶክተር ትልቅሰው ተሾመን አነጋግረናል። ዶክተር ትልቅሰው፤ «የዓይን ሞራ አንዴ በኦፕሬሽን ከተወገደ በኋላ ተመልሶ አይመጣም። ነገር ግን ታካሚዎች ዕይታቸው ሲቀንስ ሞራ ተመልሶ መጣ የሚል እሳቤ ሊኖራቸው ይችላል።» ነው ያሉት የዓይን ህክምና ከፍተኛ ባለሙያው። በቀዶ ህክምና የዓይን ሞራ የተወገደላቸው ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች እይታቸው ሊቀንስ ይችል ካልሆነ በቀር የዓይን ሞራ ተደጋግሞ እንደማይከሰትም ደጋግመው ነው ያስረዱት።

Symbolbild Spionage
ዓይንምስል McPHOTO/blickwinkel/picture alliance

ሪቨርብላይንድነስ የተባለው የዓይን የጤና ችግር በጥገኛ ተሐዋሲ አማካኝነት በተለይም ጊኒዎርም በመባል የሚታወቀው ትል ጋር እንደሚገናኝ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በተወሰ አካባቢ እንደሚታይ ሆኖም ግን በአንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራትም በስፋት የሚገኝ መሆኑን ነው የገለጹት። ከዚህ የዓይን ችግር ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የሚያጋጥመው በህክምናው ትራኮማ ተብሎ የሚጠራው የዓይን ህመም እንደሆነም አስረድተዋል። ከዚህም ሌላ እንደ HIV እና TB ያሉ ተሐዋስያን በዓይን ውስጥ ቁስለትን በማስከተል ዕይታ ላይ እክል ሊያስከትሉ እንደሚችሉም ነው የዓይን ከፍተኛ ሀኪሙ የገለጹልን። ሰዎች የዓይን ጤናቸውን ለመጠበቅ በተለይም የስኳር ህመም፤ ወይም ከቤተሰብ የጤና ታሪክ ጋር የተያያዘ ነገር ካለ በየጊዜው ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግም መክረዋል።  

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ