1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለምከተማና የፋተርሽቴትን ወዳጅነት

ሐሙስ፣ መስከረም 15 2012

«የጀርመን ጉብኝቴ ልዩ ስሜት ነዉ የፈጠረብኝ። በአደጉት ሃገሮች እና እንደኛ ተስፋ ባላት ሃገር ዉስጥ ያለዉን ልዩነት ነዉ ያየሁት። በጀርመንና በኢትዮጵያ መካከል ያለዉ  የእድገት ልዩነት የማይደረስ ነዉ ብዬ ባላስብም፤ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለን አይቻለሁ»

https://p.dw.com/p/3QJJE
25 Jahre Partnerschaft zwischen Alem Katem und Vaterstetten
ምስል Alexander Bestle

አድጅነቱን የታላቅዋ ኢትዮጵያ እና ጀርመን አድርገን እናሰፋዋለን

 

«የጀርመን ጉብኝቴ ልዩ ስሜት ነዉ የፈጠረብኝ። በአደጉት ሃገሮች እና እንደኛ ተስፋ ባላት ሃገር ዉስጥ ያለዉን ልዩነት ነዉ ያየሁት። በጀርመንና በኢትዮጵያ መካከል ያለዉ  የእድገት ልዩነት የማይደረስ ነዉ ብዬ ባላስብም፤ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለን አይቻለሁ» ከወደ ጀርመን በተደረገላቸዉ የክብር ግብዣ ሰባት ልዑካንን አስከትለዉ ለአስራ አምስት ቀናት ቆይታ አድርግዉና የተለያዩ ዓዉደ ጥናቶችን  አካሂደዉ የተመለሱት፤ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ ነበሩ።  በደቡባዊ ጀርመን የምትገኘዉ አነስተኛ ከተማ ፋተር ሽቴትን እና የዓለም ከተማን የእህትማማችንነት ወዳጅነት ግንኙነት 25ኛ ዓመት ምስረታን በማስመልከት እዚሁ ጀርመን ፋተርሽቴትን ከተማ ዉስጥ በደማቅ ተከብሮአል ። የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ በሚመራዉ ልዑክ ሁለት የሕጻናት መዋያ ሴት ሰራተኞች፤ የመረሃ-ቤቴ አስተዳዳሪ፤ የዓለም ከተማ ከንቲባ፤ እንዲሁም የቦርድ አባላትን ያካተተ ነዉ።

25 Jahre Partnerschaft zwischen Alem Katem und Vaterstetten
ምስል Alexander Bestle

 

የዓለም ከተማና የጀርመንዋ ከተማ ፋተርሽቴትን የወዳጅነት ማኅበር ሰዎች ለሰዎች የሰብዓዊ ርዳታ ድርጅት መስራች በኦስትርያዊዉ በካርልሃይንስ ቦም እና በቅድሞዉ የፋተር ሽቴትን ከንቲባ ፒተር ድርሊንገር ነበር። ማኅበሩ እስካሁን በዓለምከተማ ሁለት የሕጻናት መዋያዎችን አንድ ቤተ-መጽሐፍት እንዲሁም አንድ ቤተ-መዘክር ከፍቶአል። ማኅበሩ ሦስተኛ የሕጻናት መዋያን እንዲሁም የሞያ ስልጠና ማዕከልን ለመክፈት እቅድ ይዞአል። በጀርመን ማኅበሩ ከ600 በላይ አባላት አሉት። በጀርመን ፋተርሽቴትን የማኅበሩ የፕሮጀክትና የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ጀርመናዊዉ አሌክሳንደር ቤስትል እንደተናገሩት ባለፈዉ ከኢትዮጵያ ከመጡት ልዑካን ጋር የማኅበራችንን ምስረታ 25ኛ ዓመት በደማቅ አክብረናል ብለዋል።

25 Jahre Partnerschaft zwischen Alem Katem und Vaterstetten Alexander Bestle
ምስል Alexander Bestle

 

«የዓለምከተማ እና የፋተር ሽቴትን ከተሞች ወዳጅነት ምስረታ 25ኛ ዓመትን በማስመልከት ከዓለምከተማ ከመጡት የልዑካን ቡድን ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። በዝግጅቱ ላይ የፋተርሽቴትን ከተማ ነዋሪዎች፤ በተለይ ባለፉት ዓመታት የሁለቱን ከተማ ማኅበር ሲረዱ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች፤ የከተማዋን ከንቲባን ጨምሮ የጀርመን ፖለቲከኞች፤ የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የፓርላማ አባል፤ የከተማዋ የቀድሞ ከንቲባ ፤ እንዲሁም በሁለቱ ከተሞች ማኅበር ዉስጥ ምን እንደሚሰራ ለማወቅ የፈለጉ ብዙ ሰዎች በዝግጅቱ ላይ ታድመዋል።»

 

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ ለማኅበሩ ምስረታ 25 ኛ ዓመት ክብረ በዓል ተጋብዘን ብንመጣም፤ እግረ መንገዳችንን ያለምንም እረፍት ብዙ ሥራዎችን አከናዉነናል ሲሉ ነግረዉናል። በጀርመንዋ ፋተርሽቴትን ከተማ ዝግጅት ላይ በእንግድነት የነበሩት የዓለምከተማ ከንቲባ አቶ ጌቱ ቅጣዉ በበኩላቸዉ የጀርመንዋ ከተማ በፋተርሽቴትን እና በዓለም ከተማ መካከል የዛሬ 25 ዓመት ወዳጅነት ሲመሰረት በመካከላቸዉ ያለዉን ማኅበራዊ ኢኮኖምያዊ እና ባህላዊ ጉዳዮችን ለመለዋወጥ እና ማኅበረሰቡን ለማቀራረብ ያለመ ነበር ብለዋል።   

25 Jahre Partnerschaft zwischen Alem Katem und Vaterstetten Peter Dingler
ምስል Alexander Bestle

ጀርመንን አይተዉ መደነቃቸዉን የነገሩን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ እንደገለፁት የጀርመንን ተሞክሮ ለትንሽዋ አለም ከተማ አልያም ፋተርሽቴትን ብቻ ሳይሆን ለታላቅዋ ኢትዮጵያ አገር አቀፍ ልንወስድ ይገባናል ብለዋል።  የጀርመናዉያን የቆሻሻ አወጋገድ ስልትን ልንቀስም ይገባል ቆሻሻ ሌላ የኃብት ምንጭ መሆኑንም በጀርመን ጉብኝቴ አይቻለሁ ሲሉ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ ተናግረዋል።  

 

በጀርመን ፋተርሽቴትን የማኅበሩ የፕሮጀክትና የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ጀርመናዊዉ አሌክሳንደር ቤስትል በፋተር ሽቴትን የተከበረዉ የሁለቱ ከተሞች የእህትማማች ማኅበር ምስረታ ዓለም ከተማ ላይም ለማክበር ማኅበሩ ልዑካኑን ወደ ዓለም ከተማ እንደሚልክ ተናግረዋል። ጀርመናዉያኑ በዓለም ከተማ በተለይ በትምህርትና የሞያ ስልጠናን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጥሩ ድጋፍን እንደሚያገኙም ገልፀዋል። 

25 Jahre Partnerschaft zwischen Alem Katem und Vaterstetten
ምስል Alexander Bestle

 

«ዓለምከተማ ላይ ለምንሰራዉ የልማት ስራዎች ሁሉ ድጋፍ ስንፈልግ ከኢትዮጵያ መንግሥት እናገኛለን። ከኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋርም ግንኙነታችንን አጠናክረን ለመቀጠል ጥረት እያደረግን ነዉ። ወደ ኢትዮጵያ በተጓዝን ቁጥር ወደ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጎራ ብለን ከባለሥልጣናቱ ጋር እንነጋገራለን። በፍራንክፈርት ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን። በርሊን በሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከአዲስዋ የኢትዮጵያ አምባሳደርም ጋር በጣም ጥሩ ግንኙነት አለን።»  የዓለምከተማና የፋተርሽቴትን የእህትማማች ከተሞች ወዳጅነት ይበል እያልን ቃለ-ምልልስ የሰጡን ሁሉ በ«DW» ስም እያመሰገንን፤ ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ሙሉ መሰናዶዉን እንዲያደምጡ  እንጋብዛለን

 

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ