1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ቴክኒክአፍሪቃ

የዓለም የራዲዮ ቀን

ቅዳሜ፣ የካቲት 6 2013

የዓለም የራዲዮ ቀን ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ10ኛ ጊዜ “New World, New Radio” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው፡፡ ቀኑን ምክንያት በማድረግ ዶይቼ ቬለ አንድ የጣቢያውን የረጅም ጊዜ ደንበኛ አነጋግሯል፣ ደንበኛው የቀድሞ ትዝታቸውንና ተሳትፏቸውን እያነሱ ያጫውቱናል፡፡ 

https://p.dw.com/p/3pK7F
BdTD - Deutschland Kürbisausstellung in Ludwigsburg
ምስል picture-alliance/dpa/C. Schmidt

የዓለም ራዲዮ ቀን

የዓለም ራዲዮ ቀን እንዲከበር በስፔን የራዲዮ አካዳሚ አነሳሽነት ጥያቄው እ ኤ አ በ2010 ለዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) የስራ አመራር ከቀረበ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ጉዳዩን ተቀብሎ ዓለም አቀፍ የራዲ ቀን በየዓመቱ እ ኤ አ February 13 (የካቲት 6) እንዲከበር ወስኗል፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያው የራዲዮ ቀን የካቲት 6/2004 ዓ ም የተከበረ ሲሆን ዛሬ ለ10ኛ ጊዜ New World, New Radio በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው፡፡

የጀርመን የራዲዮ ጣቢያ (ዶይቼ ቬለ DW) አማርኛው ክፍል  ከዓመታት በፊት የስርጭት ቦታው፣ የመተላለፊያ ሰዓቱና የጣቢያ መክፈቻ ድምፅ እንደዛሬው አልንበረም፡፡ ዶይቼ ቬለ ዘወትር ከቀኑ 11 ሰዓት ከኮሎኝ ከተማ ነበር የሚተላለፈው፡፡ በወቅቱ ሰዎች እየተሰባሰቡ መረጃዎችን ከጣቢያው ሲያዳምጡ ከነበሩ አድማጭና ተሳታፊ መካከል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ አንዲት ሱቅ ይሰራ የነበረው ዓለምሸት ምህረቴ አንዱ ነው፡፡ ዓለምሸት ዛሬ ነዋሪነቱ ባሕር ዳር ሲሆን በአንዲት አነስተኛ ሱቅ ከሰፈር ሰዎች ጋር ተሳባስበው የጀርመን ራዲዮን ያዳምጡ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ 
ጣቢያው በሚያስተላልፋቸው ፕሮግራሞችም ይሳተፍ ፣ ጥቆማ በመስጠት፣ አጫጭር ፅሁፎችን በመላክና በሌሎች ጉዳዮችም ይሳተፍ እንደነበር ዓለምሸት ከዶይቼ ቬለ ጋር በነበረው ቆይታ ነግሮናል፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት ጣቢያው ከሚያዘጋጃቸው የተሳትፎ ጥያቄዎች መካከል ምላሽ ሰጥቶ የግሩንዲግ ራዲዮ ተሸልሟል፡፡ 
በወቅቱ ፕሮግራሞቻቸውን በልዩ ስሜት ከሚከታተልላቸው የጣቢያው ጋዜጠኞች መካከል የቀድሞዎቹ ጌታቸው ተድላ፣ ዘውዱ ታደሰና ጌታቸው ደስታን እንደሚያደንቅ አመልክቷል፡፡ 
ከዛሬዎቹ የጣቢያው ጋዜጠኞች ደግሞ ነጋሽ መሐመድ ጎላ ብሎ እንደሚታየውና አነባቡና አቀራረቡ እንደሚስበው ዓለምሸት ይገልፃል፡፡ 
ዓለምሸት ያን ብቻ አይደለም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩ የጀርመን ራዲዮ ጣቢያ አድማጮች ጋር ጓደኝነት በመፍጠር ተሳትፏቸው የጎላ እንደነበርም ይገልፃል፡፡ 
ለመሆኑ በጀርመን ራዲዮ ጣቢያ ለመሳተፍና አገር ውስጥ ካሉ ጓደኞች ጋር በየጊዜው በደብዳቤ ለመገናኘት ልጅ ሆኖ ወጪ አይጠይቅም? የሚል ጥያቄ አቅርቤለት ነበር፡፡ በጊዜው “ኤሮግራም” የሚባል በጣም አነስተኛ በሆነ ዋጋ የሚሸጥ የመልዕክት መላላኪያ ፖስታ ስለነበር ብዙም ከባድ እንዳልነበር ምለሽ ሰጥቷል፡፡ አሁንም ዶይቼ ቬሌን በተለያዩ አማራጮች እየተከታተለ እንደሆነ ነግሮኛል፡፡ 
 
ዓለምነው መኮንን 

ልደት አበበ