1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Shewaye Legesseሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2016

የሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዋና ዋና ዜናዎች፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል በህቡዕ ተጠርቷል በተባለው አድማ በአንዳንድ አካባቢዎች የመጓጓዣ እንቅስቃሴ ገደብ መኖሩ እየተነገረ ነው። ሱዳን ውስጥ በየቀኑ 20 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንደሚፈናቀሉ የተመድ አመለከተ። የኢራን እስራኤል ውዝግብ እንዳይባባስ ሃገራት እያሳሰቡ ነው። ኢራን በበኩሏ ውጥረቱ እንዲባባስ እንደማትፈልግ ስትገልጽ፤ የእስራኤል የጦር ካቢኔ ስብሰባ ማድረጉ ተዘግቧል። ኦማን ውስጥ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 14 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገለጸ።

https://p.dw.com/p/4eoTt

አዲስ አበባ፤ በኦሮሚያ በህቡዕ የተጠራው የእንቅስቃሴ ገደብ

 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል በህቡዕ ተጠርቷል በተባለው አድማ በአንዳንድ አካባቢዎች የመጓጓዣ እንቅስቃሴ ገደብ መኖሩ እየተነገረ ነው። ሰሞኑን ወደ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ ቤተሰብ ለመጠየቅ ከሄዱ ወገኖች አንዷዛሬ ወደ አዲስ አበላ ለመመለስ ቢፈልጉም መጓጓዣ ማጣታቸውን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

«ጠዋት አንድ መኪና ውስጥ  ገብተን ለመንቀሳቀስ ብናስብም አሽከርካሪው በስጋት አልሄድም ብሎ ስላስወረደን መሄድ አልቻልንም፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አሁን ከረፋድ አራት ሰዓት በኋላ መኪኖች ሰው ጭነው መውጣት ጀምረዋል የሚል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ ብታይ ስጋት አለ፤ ሰው በጊዜው ነው ወደ ቤት የሚገባው፡፡ እንደወትሮው ባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎችም በጠዋት ስወጡ አይስተዋልም” ብለዋል።»

በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ነቀምቴ ከተማ ውስጥ የባጃጅ እንቅስቃሴ መኖሩን የገለጹ ነዋሪዎችም እንዲሁ ከከተማ ወደ ከተማ ለመንቀሳቀስ ግን አስቸጋሪ መሆኑን አመልክተዋል። በአንጻሩ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥሪው ቀርቧል ከተባለበት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ወዳሉ ከተሞች እንዲሁም ወደ ሀሃዋሳ፤ ሞጆ፤ ባቱ እና ሻሸመኔ መስመሮች መደበኛው እንቅስቃሴ እንደቀጠለ መሆኑን እማኞች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ስለሁኔታው ከኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ከአዲስ አበባ ሥዩም ጌቱ በላከው ዜና አመልክቷል።  

 

ኻርቱም፤ ሱዳን ውስጥ በየቀኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ይፈናቀላሉ

ሱዳን ውስጥ በየቀኑ 20 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንደሚፈናቀሉ የተመድ አመለከተ። በሱዳን አንድ ዓመት ያስቆጠረውን ውጊያ አስመልክቶ የመንግሥታቱ ድርጅት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ተቋም (IOM) ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ ከሚፈናቀሉት ከግማሽ በላይ ሕጻናት እና ወጣቶች እንደሆኑ ገልጿል። እንደ ድርጅቱ መረጃ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ጀምሮ ሱዳን ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ከ8,6 ሚሊየን በልጠዋል። ከእነዚህም ሁለት ሚሊየን የሚሆኑት ድንበር አልፈው ወደ ቻድ፤ ደቡብ ሱዳን እና ግብፅ መሰደዳቸውንም ጠቅሷል። የIOM ዳይሬክተር ጀነራል አሚ ፖፕ «ሱዳን በሚያሳዝን መልኩ በአስርት ዓመታት ውስጥ የዓለም ግዙፍ የሰብአዊ ቀውስ ከተከሰተባቸው ሃገራት አንዷ ሆናለች» ማለታቸውን የጀርመን የዜና ወኪል ዲፒኤ ዘግቧል።  የሱዳኑ ግጭትም በአካባቢው ጫና መፍጠሩንም አመልክተዋል። ፖፕ አያይዘው ሚሊየኖች መፈናቀላቸውን፤ ለረሀብና ለብዝበዛ እንዲሁም ለጥቃት የተጋለጡ መሆናቸውን በማመልከትም፤ ስቃያቸው ግን ችላ እንደተባለ ገልጸዋል። ለአንድ ዓመት በጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ሱዳን እርዳታ ለማሰባሰብ ያለመ ጉባኤ ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ዛሬ ተጀምሯል።

 

ለንደን፤ ብሪታንያ በሱዳን ግጭት የተሳተፉ ባለቻቸው ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣሏ

ብሪታንያ ከሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለቻቸው የንግድ ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣሏን ዛሬ አስታወቀች። የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ከሱዳን ጦር እና ከተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ትስስር ያላቸው ኩባንያዎች ላይ እስከ ንብረት ማገድ የሚደርስ «ጠንካራ እርምጃ» ያለውን ማዕቀብ መጣሉን አመልክቷል። በዚሁ መሠረት ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል አልካሊል ባንክ፣ አልፋኪር አድቫንስድ ዎርክስ፤ እንዲሁም ሬድ ሮክ የማዕድን አውጪ ኩባንያዎች ተጠቅሰዋል። የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቩድ ካሜሩን ኩባንያዎቹ ሱዳን ውስጥ ለየሚደግፏቸው ቡድኖች ባደረጉት አስተዋጽኦ እና ለጦርነቱ መባባስ ተጠያቂዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። የእርዳታ ሠራተኞች ለአንድ ዓመት የዘለቀው የሱዳን ጀነራሎች የለኮሱት ጦርነት በርካታ ሲቪል ዜጎችን ለረሀብ፤ ለጾታዊ ጥቃት፤ ለመጠነ ሰፊ ጎሳ ተኮር ግድያ እና ስደት መዳረጉን ይፋ አድርገዋል።  

 

መካከለኛው ምሥራቅ፤ ሃገራት የኢራን እስራኤል ውዝግብ እንዳይባባስ ማሳሰባቸው

 

የኢራን እስራኤል ውዝግብ እንዳይባባስ ሃገራት እያሳሰቡ ነው። ፈረንሳይ የሁለቱ ሃገራት ቁርቁስ እንዳይቀጥል የምትችለውን ለማድረግ ጥረት እንደምታደርግ ስትገልጽ፤ ብሪታንያ በበኩሏ እስራኤል የአጸፋ እርምጃ እንዳትወስድ ተማጽናለች። ከኢራን የተተተኮሱባትን ሚሳኤሎች በተሳካ ሁኔታ ማክሸፏን ያመለከቱት የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስም እንዲሁ ውጥረቱ እንዲረግብ እስራኤል የመልስ ጥቃት ከማድረግ እንድትቆጠብ ጠይቀዋል። ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረው ውጥረት እጅግ እንዳሳሰባት ዛሬ አስታውቃለች። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የውጥረቱን መባባስ ማንም እንደማይፈልግ በማመልከት ሞስኮ አለመግባባቶች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሄ ማግኘት እንደሚኖርባቸው ታምናለች ብለዋል።  

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም እንዲሁ ሀገራቸው በመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት እንዲባባስ አትፈልግም ነው ያሉት። ናስር ካናኒ የእስራኤል ደጋፊ ሃገራት ኢራን የተመጠነ ያሉትን እርምጃ በመውሰዷ እንዲያደንቁም ጠይቀዋል።  

«ለወንጀለኛው ጽዮናዊ አገዛዝ ደጋፊዎች ሁሉ ምክራችን፤ ስለኢራን ተገቢያ ያልሆኑ ቃላትን ከመናገር ይልቅ፤ ኢራን የወሰደችውን ጥንቃቄ የተሞላበትና የተመጠነ እርምጃ በማድነቅ፤ ከማንም በላይ ያልተገመተ መዘዝ በራሱ ላይ የሚያስከትል ተጨማሪ መጥፎ ድርጊቶችን ከመፈጸም እንዲቆጠብ የጽዮናዊው አገዛዝን እንዲመክሩ ነው።»

በአንጻሩ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በዛሬው ዕለት የጦር ካቢኔያቸውን መሰብሰባቸው ነው የተነገረው። ካቢኔው በኢራን ለተሰነዘረው ጥቃት ምላሽ ምን ይሁን የሚለውን የሚወስን ነው። በጦር ካቢኔው ኔታንያሁን ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት፤ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋኔትዝ እንዲሁም በርካታ ታዛቢዎች የተሰባሰቡት ነው። ትናንት ማምሻውንም ተሰብስቦ እንደነበር ምንጮች ለሮይተርስ ገልጸዋል።

 

ሙስካት፤ ኦማን ውስጥ በጎርፍ አደጋ 14 ሰዎች ሞቱ  

ኦማን ውስጥ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 14 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ባለሥልጣናት ዛሬ አስታወቁ። ከሟቾች አብዛኞቹ ተማሪዎች ናቸው። የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ነው የተገለጸው። በትናንትናው ዕለት ተማሪዎች ያሳፈረ ተሽከርካሪ በጎርፍ በመወሰዱ ዘጠኝ ተማሪ ልጆች እንዲሁ ሦስት አዋቂዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው በሀገሪቱ የዜና ወኪል መዘገቡን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ጠቅሷል። በዛሬው ዕለት ግን የተገኘው አስከሬን 14 መድረሱን አመልክቷል። በሀገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት አካባቢ ከባድ ወጀብና ንፋስ ያጀበው ኃይለኛ ዝናብ ትናንት መዝነቡን፤ በምሥራቅ እና ሰሜን የሀገሪቱ ክፍሎች ጎርፍ ማስከተሉ ነው የተገለጸው። የኦማን የትምህርት ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት አብዛኞቹ ግዛቶች ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ አድርጓል። በጎርፍ ምክንያት መንገድ ያጡ ወገኖችን በአየር ለማንሳት ጥረት መደረጉም ተገልጿል። በተመሳሳይ ኃይለኛው ወጀብ ባህሪን እና አረብ ኤሜሬትን ጨምሮ የባሕረ ሰላጤውን ሃገራት ሊያዳርስ እንደሚችል ይጠበቃል።  

 

 

መቃዲሹ፤ በሶማሊያ ወደብ አቅራቢያ የተያዘች መርከብ መለቀቋ

 

በሶማሊያ የባሕር ወደብ አቅራቢያ በባሕር ላይ ወንበዴዎች ተይዛ የቆየችው መርከብ መለቀቋን የአውሮጳ ሕብረት የባሕር ደህንነት ኃይል ዛሬ አስታወቀ። የባንግላዴሽ ሰንደቅ አላማ ታውለበልብ እንደነበር የተገለጸው መርከብ ከ23 የመርከቧ ሠራተኞች ጋር ከተያዘች ከአንድ ወር በላይ ቆይታለች። እንዲያም ሆኖ መርከቧ የተለቀቀችበት ቅድመ ሁኔታ ምን እንደሆነ አልተገለጸም። በምህጻሩ ዘመቻ አትላንታ የተሰኘው ተልዕኮ ከሶማሊያ የባሕር ወደብ 1,100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መርከቧ ከታገተችበት ጊዜ አንስቶ ሲከታተል መቆየቱ መገለጹን አሶሲየትድ ፕረስ በዘገባው ጠቅሷል። መርከቧ ከማፑቶ ወደ ወደ አረብ ኤሜሬት በመጓዝ ላይ ሳለች ነበር 20 የሚሆኑ የታጠቁ የባሕር ላይ ወንበዴዎች እጅ የወደቀችው።  

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
Mittelmeer | Asylreform in der EU
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።