1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፦ መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም.

Hirut Melesseዓርብ፣ መጋቢት 20 2016

የመጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና ለስምንት ወራት በእሥር ላይ የቆዩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ። ደቡብ ሱዳን በጎረቤት ሱዳን በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት ዋነኛው የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ መስመር መዘጋት የኤኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ እንዳያስከትልባት አስግቷል። ሩስያ ትናንት ለሊቱን ዩክሬን በሚገኙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሰበብ በሦስት ግዛቶች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ዩክሬን አስታወቀች ።

https://p.dw.com/p/4eGFf

 

አዲስ አበባ     አቶ ክርስቲያን ታደለና አቶ ዮሐንስ ቧያለው ፍርድ ቤት ቀረቡ

 

ለስምንት ወራት በእሥር ላይ የቆዩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ። በዚሁ መዝገብ የተከሰሱ ሌሎች 14 ተጠርጣሪዎችም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገ መንግስት እና የሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ቀርበው የክስ መዝገባቸውን መቀበላቸውን ጠበቃቸው ሰለሞን ገዛኸኝ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። የተከሳሽ ጠበቆች ተከሳሾችን ያገኟቸው ዛሬ መሆኑን በመጥቀስ የክስ ፍሬ ነገሩን ማንበብም ሆነ ሌሎች ሂደቶችን በተመለከተ አቤቱታ በማቅረባቸው ፍርድ ቤቱ  አቤቱታውን ተቀብሎ ሂደቱ በቀጣዩ ሳምንት አርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ . ም እንዲታይ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ ሰለሞን ተናግረዋል። ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች ወደ ፌዴራል ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ለፍርድ ቤቱ አቅርቦት የነበረው አቤቱታ ውድቅ መደረጉንም ጠበቃቸው አረጋግጠዋል። ተከሳሾቹ በተወካያቸው አቶ ዮሃንስ ቧያሌው በኩል ሁለት ሰብዓዊ መብትን የተመለከቱ አስቸኳይ አቤቱታዎችን ማቅረባቸውን ጠበቃው ለዶቼቬለ ተናግረዋል።ተከሳሾቹ ባለፈው ሳምንት እሥር ቤት ውስጥ ሆነው በፃፉት ደብዳቤ "ማንነትን መሠረት ያደረገ ስድብ፣ ዘለፋ ፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ ፣ ድብደባ እና ዝርፊያ" እንደተፈፀመባቸው ተናግረው ነበር።

 

 

ዘሄግ   እስራኤል ወደ ጋዛ ተጨማሪ የየብስ መተላለፊያ እንድትከፍት ታዘዘች

 

ዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት በምህጻሩ ICJ እስራኤል ወደ ጋዛ የሚያስገባ ተጨማሪ የየብስ መተላለፊያ እንድትከፍት ማዘዙን በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን አወደሱ ። ፍልስጤማውያኑ ትዕዛዝ መሰጠቱ ቢያስደስታቸውም የእሥራኤል መንግሥት ትዕዛዙን ተግባራዊ ማድረጉን ግን ተጠራጥረዋል። እስራኤል ወደ ጋዛ ተጨማሪ መተላለፊያ ክፍት በማድረግ ምግብ ውኃ ነዳጅ እና ሌሎች ግብአቶች እንዲገቡ እንድታደርግ ነው ፍርድ ቤቱ ትናንት ትዕዛዝ የሰጠው ። ICJ በዚህ አስገዳጅ በተባለ ትዕዛዝ እስራኤል እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ አገልግሎቶችና ሰብአዊ ርዳታዎች ሳይዘገዩ ጋዛ መድረሳቸውን የሚያረጋግጡ ርምጃዎችን  እንድትወስድ ነግሯል። እኚህ ፍልስጤማዊ እስራኤል ፍርድ ቤቱ ያሳለፈውን ትዕዛዙን ማክበሯን ከሚጠራጠሩት አንዱ ናቸው።

« ይህ የዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት ውሳኔ ጽናት የታየበትና ጥሩ ውሳኔ ነው። ግን እስራኤል ለውሳኔው ተገዥ ትሆናለች? እስራኤል ከሁሉም በላይ እና ከሕግም በላይ ናት።» 

ፍርድ ቤቱ  ትናንት ሐሙስ ትዕዛዙን ያስተላለፈው እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ስትል የከሰሰችው ደቡብ አፍሪቃ ፍርድ ቤቱ በእስራኤል ላይ ተኩስ ማቆምን ጨምሮ ሕጋዊ ርምጃዎችን እንዲወስድ በጠየቀችው መሠረት ነው። ስለ ትዕዛዙ የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወዲያውኑ መልስ አልሰጠም። ሆኖም በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ደቡብ አፍሪቃ በእስራኤል ላይ ተጨማሪ ርምጃዎች እንዲወሰዱ ደቡብ አፍሪቃ ላቀረበችው ጥያቄ በሰጠው መልስ የደቡብ አፍሪቃን ክስ መሰረተ ቢስ ሲል አጣጥሏል።

 

 

ጁባ     ደቡብ ሱዳን በነዳጅ ዘይት ቧንባ ብልሽት ምክንያት የኤኮኖሚ ችግሮች ያሰጓታል

ዋነኛ የገቢ ምንጭዋ ነዳጅ ዘይት የሆነው ደቡብ ሱዳን በጎረቤት ሱዳን በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት ዋነኛው የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ መስመር መዘጋት የኤኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ እንዳያስከትል ባለሞያዎች አስጠነቀቁ።ይህ ሀገሪቱ የተጋረጠባት ችግርም የደቡብ ሱዳን ምርጫ እንደገና ለሌላ ጊዜ እንዲገፋ ሳያስገድድ አይቀርም የሚል ስጋት አሳድሯል። የሱዳን የኃይል ሚኒስትር ከአንድ ሳምንት በፊት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ከደቡብ ሱዳን ፣ቀይ ባህር ጠረፍ ላይ ወደምትገኘው ወደ ፖርት ሱዳን የሚያስተላልፈው ቧንቧ ከባድ መሰንጠቅ እንዳጋጠመው በደብዳቤ አሳውቀዋል። ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው ችግሩ በየካቲት ወር በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። የደቡብ ሱዳን ምክር ቤት የነዳጅ ዘይት ንዑስ ኮሚቴ ኃላፊ ቡትሮስ ማጋያ ችግሩ በደቡብ ሱዳናውያን ሕይወትና ደኅንነት ላይ ከበድ መዘዞችን ሊያስከትል እንደሚችል የሀገሬቱን ኤኮኖሚም ለቀውስ እንደሚያጋልጥ አስጠንቅቀዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት ከደቡብ ሱዳን ህዝብ 12.4 ሚሊዮኑ ርዳታ ጠባቂ ነው። ከብሔራዊ ገቢዋ 90 በመቶውን ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ የምታገኘው ደቡብ ሱዳን አሁን በተፈጠረው ችግር ምክንያት በየወሩ 100 ሚሊዮን ዶላር ልትከስር እንደምትችል ማጋያ አስጠንቅቀዋል።

 

ካምፓላ   የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ልጅ ሙስናን ለመዋጋት ቃል ገቡ

 

የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ልጅ ጄነራል ሙሁዚ ካይነሩጋባ በዩጋንዳ ጦር ኃይሎች ሙስናን ለመዋጋት ቃል ገቡ። ትናንት በዩጋንዳ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምነት በይፋ ስልጣኑን የተረከቡት ሙሁዚ ካይነሩጋባ የወታደሮችን ይዞታ ለማሻሻል፣ ሙስናናን ለመዋጋት የተበላሸ የሀብት አስተዳደርን ለማስተካከል ቃል ገብተዋል። ዩጋንዳን ለ38 ዓመት የመሩት የ79 ዓመቱ ዩዌሪ ሙሴቬኒ የ49 ዓመቱ ልጃቸውን ካይነሩጋባን አዲሱ የዩጋንዳ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም አድርገው የሰየሙት ባለፈው ሳምንት ነበር። የዩጋንዳ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካይነሩጋባ ሲሾሙ ሙሴቬኒ ልጃቸውን ለፖለቲካ ሥልጣን እያዘጋጁ ነው ሲሉ ተቃውመዋል። ይህ ብዙዎች የሚጠብቁት እንደሆነም ይናገራሉ። ዩዌሪ ሙሴቬኒ ግን ልጃቸውን ለፕሬዝዳንትነት እያመቻቹ እንዳልሆነ አስተባብለዋል። የዩጋንዳ ጦር በአካባቢ ሀገራት ሰላም ለማስፈን ትልቅ ሚና ይጫወታል። ኡጋንዳ ሶማሊያና ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ውስጥ ወታደሮቿን ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ አሰማርታለች። ሙሁዚ ካይነሩጋባ በጎርጎሮሳዊው 2022 የዩጋንዳ እግረኛ ጦር አዛዥ በነበሩበት ወቅት በቀድሞ መጠሪያው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ጎረቤት ኬንያን ለመውረር ከዛቱ በኋላ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ነበር። ቆይት ብለው ግን ዛቻው ቀልድ ነበር በማለት አስተባብለዋል።

 

ዋሽንግተን   ሩስያ ተጨማሪ የዩክሬን መሬት ይዛለች

 

ሩስያ ከዩክሬን ጋር በምታካሂደው ጦርነት ተጨማሪ የዩክሬን ግዛቶችን መያዟን አንድ የዩናይትድ ስቴትስ የጥናት ተቋም አረጋገጠ። በጦርነት ላይ ጥናት የሚያካሂደው በምህጻሩ ISW የተባለው ተቋም እንዳስታወቀው ሩስያ በጥቅምት ወር ከከፈተችው የጥቃት ዘመቻ በኋላ ብቻ 505 ስኬውር ኪሎሜትር የዩክሬንን መሬት ተቆጣጥራለች።ዩክሬን አሁንም ሩስያ በሁሉም የውጊያ ግንባሮች ከፍተኛ ስልታዊ ድል እንዳታገኝ እየተከላከለች ነው ያለው ተቋሙ፣ሆኖም የዩክሬን የቁሳቁስ እጥረት ከቀጠለና ለሰው ኃይል እጥረትም መፍትሄ ካላገኘች ሩስያ የዩክሬንን ተጋላጭነት የመጠቀም እድል እንዳላት አስጠንቅቋል። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ሩስያ በመጪ የአውሮጳ በጋ ወቅት ሩስያ አዲስ ከፍተኛ የጥቃት ዘመቻ ልትከፍት ትችላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ተቋሙ እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ የአየር ንብረቱ አስቸጋሪ ቢሆንም ሩስያ በአሁኑ የጥቃት ዘመቻ ኃይል ትቀጥላለች ተብሎ ይታመናል።ለዚህም የISW ተመራማሪዎች የሩስያን ግስጋሴ ለመግታት ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚሰጡት ርዳታ አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተውታል።ምሁራኑ የዩክሬን የአየር ጥቃት መከላከያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከመ በመሄድ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌኒስኪ የዩክሬን የአየር ክልላቸውን ለመከላከል ተጨማሪ ፓትርየት የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ ፀረ ሚሳይል እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

ክየቭ           በሦስት የዩክሬን ግዛቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋረጠ

 

ሩስያ ትናንት ለሊቱን ዩክሬን በሚገኙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሰበብ በሦስት ግዛቶች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ዩክሬን አስታወቀች ።ዩክሬን እንዳለችው ሩስያ ለሊቱን በጣቢያዎቹ ላይ በርካታ ሚሳይሎችን ተኩሳለች ፤የድሮን ጥቃቶችም ፈጽማለች። ሩስያ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ዩክሬን በሩስያ ድንበር ላይ ለፈጸመችው ጥቃት አጸፋ የዩክሬን የኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን እየፈጸመች ነው። የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደተናገሩት በድኒፕሮፔትሮቪስክ በዛፖሪዝህዝያ እና በኪሮቮግራድ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቋረጥ ተገደዋል።በዋና ዋናዎቹ ከተሞች በካራኪቭ እና ክሪቪም የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም ገደቦች መጣላቸውንም አስታውቃለች። በሌሎች ግዛቶች የሚገኙ ሰዎችም የኤሌክትሪክ ኃይልን በቁጠባና በጥንቃቄ እንዲጠቀሙ ተጠይቀዋል።የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳሉት ጥቃቶቹ ከመደጋገማቸው በተጨማሪ መጠነ ሰፊም በመሆናቸው የዩክሬን የኃይል ደኅንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ እያደረጉ ነው። ሚኒስትር ዴኒስ ሺግማል ዩክሬን የወሳኝ መሠረተ ልማቶቿን ደኅንነት ለማስጠበቅ እና ህዝቧንም ከጥቃት ለመከላከል ተጨማሪ የአየር ጥቃት መከላከያ ስርዓቶች ያስፈልጓታል ብለዋል። ጥቃቶቹ በዩክሬን ላይ የተበራከቱት ዩክሬን የአየር ጥቃት መከላከያዎች እጥረት ስለገጠማት ነው ተብሏል።

 

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።