1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዎላይታ ፖለቲከኞች የዋስትና መብት መታገድ 

ማክሰኞ፣ መስከረም 19 2013

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፦ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓትን በመናድና በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ያላቸው ስድስት የዎላይታ ዞን አመራር እና ፖለቲከኞች ቀደም ሲል በእስር ፍርድ ቤት የተሰጣቸው የዋስትና መብት እንዲታገድ ወሰነ።

https://p.dw.com/p/3jAst
Äthiopien SNNPR-Oberster Gerichtshof
ምስል Shewangizaw Wegayehu

ፍርድ ቤቱ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ወስኗል

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፦ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓትን በመናድና በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ያላቸው ስድስት የዎላይታ ዞን አመራር እና ፖለቲከኞች ቀደም ሲል በእስር ፍርድ ቤት የተሰጣቸው የዋስትና መብት እንዲታገድ ወሰነ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ በሀዋሣ ከተማ በዋለው ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ቀደም ሲል በዎላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያገኙትን የዋስትና መብት በመሻር በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ወስኗል።

በዛሬው ችሎት ከቀረቡት ስድስት ተጠርጣሪዎች መካከል ባለፈው የነሀሴ ወር ከሥልጣን የተነሱት የቀድሞው የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩንቤ ፣ የወላይታ ዞን የብልጽግና ፖርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥበቡ ዮሃንስና የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ / ዎብን / ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጎበዜ አበራ ይገኙበታል፡፡

የፌዴራል መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ባቀረበው አቤቱታ በእነ ዳጋቶ ኩምቤ መዝገብ ከተካተቱት ሃያ ተጠርጣሪዎች መካከል 3ኛ ፣ 9ኛ ፣ 13ኛ እና 19ኛ ተጠርጣሪዎች በአድራሻቸው ሊገኙ አልቻሉም ብሏል።

እንዲሁም ዋስትና ተፍቅዶላቸው ከማረሚያ ቤት ውጪ የሚገኙት 20ኛ ተጠርጣሪ መጥሪያ ቢደርሳቸውም በቀጠሮ ሊቀርቡ አንዳልቻሉ መርማሪ ፖሊስ ግልጿል፡፡

በአድራሻው ያልተገኙት ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ተፈልገው እንዲያዙ ፣ መጥሪያ ደርሷቸው በችሎት ያልቀረቡት ተጠርጣሪ ደግሞ በዞን ፍርድ ቤት ያስያዙት የዋስትና ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ እንዲደረኛ ተጠርጣሪውም በፖሊስ ተፈልገው እንዲያዙ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ እንዲሰጥለት መርማሪ ፖሊስ ጠይቋል፡፡

በዛሬው ችሎት የቀረቡት ስድስቱ ተጠርጣሪዎችም በከፍተኛ የመንግሥት አመራር ላይ የነበሩ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ የምርመራ ሥራዎችን ሊያደናቅፉ ሥለሚችሉ ፣ እንዲሁም የተጠረጠሩበት ወንጀል በከባድ የሙስናና ሕገ መንግሥታዊ ስረዓትን የመናድ ድርጊት በመሆኑ ዋስትናቸው ይታገድልኝ ሲል ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ሕገ መንግሥታዊ ስረዓትን የመናድና የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በደንበኞቻቸው ላይ ያቀረበው አቤቱታ በበቂ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ላይ ያልተመሠረተ ነው ሲሉ ተከራክረዋል ፡፡

መርመሪ ፖሊስ  በአንድ በኩል ተጠርጣሪዎቹ በወላይታ ሶዶ ከተማ ጉተራ አዳራሽ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ እንደያዛቸው እየገለፀ በሌላ በኩል ደግሞ ላለፉት አንድ ወር ከሃያ አምስት ቀናት ምርመራ እያካሄድኩ ነው የሚለው በራሱ አቤቱታው እርግጠኛነትና ተጨባጭነት እንደጎደለው ያመለክታል ብለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ከመሆናቸውም በላይ በአሁን ወቅት በሥልጣን ላይ የሌሉ በመሆናቸው በምርመራ ሥራ ላይ ተዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚለው አሳማኝ አለመሆኑን የጠቀሱት ጠበቆቹ ፍርድ ቤቱ በዞን ፍርድ ቤት የተወሰነላቸውን የዋስተና መብት እንዲያፀናላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የተጠርጣሪ ጠበቆችና የመርማሪ ፖሊስ ያቀረቡትን ሀሣብ ካዳመጠ በኋላ የክርክር ብይንና የተለያዩ ውሳኔዎች ሰጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት አቶ ዳጋቶ ኩምቤን ጨምሮ ዛሬ በችሎት የቀረቡት ስድስቱ ተጠርጣሪዎች በዞን ፍርድ ቤት የተሰጣቸውን የዋስትና መብት በመሻር ጉዳያቸውን በዎላይታ ሶዶ ማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ሲል ብይን ተሰጥቷል፡፡

በአድራሻቸው ሊገኙ አልቻሉም የተባሉት 3ኛ ፣ 9ኛ ፣ 13ኛ እና 19ኛ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተም ባሉበት ተፈልገው እንዲያዙ ለደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትዕዛዝ ደብዳቤ እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

እንዲሁም መጥሪያ ተልኮላቸው ያልቀረቡት  20ኛ ተጠርጣሪ በዞን ፍርድ ቤት ያስያዙት የአንድ መቶ ሺህ ብር ዋስትና ለመንግሥት ገቢ ሆኖ ተጠርጣሪው ካሉበት ተይዘው እንዲቀርቡ በማዘዝ ቀጣይ ቀጠሮውን ለመስከረም 21 ቀን 2ዐ13 ዓ.ም. አድርጓል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማንተጋፍቶትስ ስለሺ
ኂሩት መለሰ